Tuesday, August 13, 2013

ፍቅርን ወደ ኋላ


ሁለተኛው አመት

ኤጭ… አቦ በቃ አትጨቅጭቂኝ… ነገርኩሽ አይደል እንዴ! ጓደኞቼን ላገኝ ነው… ቢያንስ በሳምንት አንዴ እንኳን ጓደኞቼን ማግኘት አልችም እንዴ? ሁሌ ካንቺ ጋር መሆን አለብኝ! ሶሻላ ላይፍ፣ ምን ምን የሚባል ነገር የለም?

ከመቼ ወዲህ ነው ጓደኞቼ፣ ሶሻል ላይፍ ምና ምን ያመጣኸው… ድሮ አንተው አልነበርክ አብሬሽ ውዬ አብሬሽ ካላደርኩ እያልክ የምታለቃቅሰው… ጓደኛዬም፣ ፍቅረኛዬም፣ እህቴም፣ እናቴም… ቅብርጥስ፣ ቅብርጥስ ትል የነበርከው… አሁን ምን ተገኝቶ ነው? ነው ወይስ… ፍቅርህ አለቀ… ሰለቸሁህ?

ያምሻል እንዴ! ምን ማለት ነው? እንደዛ ወጣኝ… ወይስ አንቺ እራስሽ ሰለቸሁሽ? አንደውም ልንገርሽ… ሳስበው፣ ሳስበው አንቺ ነሽ የሰለቸሽ የምትመስዪው… በነጋ በጠባ ቁጥር እንደ አሮጊት ጭቅጭቅ… ሰው ከበቃው እኮ በቃኝ ይላል… አስገድጄ እኮ አልያዝኩሽም… ከደበረሽ ለምን ደበረኝ አትይም… አሁኑኑ ካጠገብሽ እጠፋልሻለው… እንደውም አንቺ የፈራሽውን እኔ እራሴው ልበልልሽ… በቃ… በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማንችል… ላልተወሰነ ጊዜ ከራሴ ጋር መሆን እፈልጋለው… አንቺም ውስጥሽ ያለውን ስሜት ጊዜ ወስደሽ አስቢበት… በተገናኘን ቁጥር ሁሌ መነቋቆር፣ መሰዳደብ፣ መጨቃጨቅ ሰልችቶኛል…

ምን አልክ? ለቅሶ… እንፍፍፍ… ለቅሶ… በቃ… በቃ… ይሄው ነው… ለዚህ ነው ያ ሁሉ ማህላ እና ልምምጥ… ይሄ ነው ለኔ የሚገባኝ… ለቅሶ… እንለያይ ነው ያልከው… ለቅሶ

ሴትዮ አታካብጂ… እንደዛ አላልኩኝም… ብሬክ እንውሰድ ነው ያልኩት…

ሴትዮ! ለቅሶ… ጭራሽ… እነዚያ የፍቅር ዝማሬዎችህ ጠፍተው… ሴትዮ! ለቅሶ…

ኡፋ! ትሰሚኛለሽ… ተነስቼ ልሄድ ነው… ካፌ ውስጥ እኮ ነው ያለነው… ሰው ምን ይለናል? በጣም እያናደድሽኝ ነው… የሌለብኝን ጨጓራ ሁላ እያመመኝ ነው… ማልቀስሽን የማታቆሚ ከሆነ ተነስቼ ልሄድ ነው…

ጥርግ በል… አሁንስ አልሄድክም እንዴ! በቃ በአፍህ ካልከው በኋላ እንዳደረከው ነው የምቆጥረው… ወይኔ ቤቲ! ባፈቀርኩህ… ከነ ችግርህ በተቀበልኩህ…

ከነችግርህ! አሃ! ለካስ ችግርተኛ ስለሆንኩ ነው እስካሁን አብረሽኝ የሆንሽው… እንዲያውም ልንገርሽ… ሄጄልሻለው… ሁለተኛ አታይኝም… ካሁን ሰዓት ጀምሮ አላቅሽም፣ አታውቂኝም…

ሄድክ… አቤል! አቤል! ሄድክ… እህ አህ አህህህህህ… ለቅሶ….

አንደኛው አመት

ስንት ሰዓት እንደጎልተከኝ ታውቆሃል?

ባክሽ ስራ ቦታ አለቅም ብለውኝ ነው…

አንድ ሰዓት ተኩል እኮ ሆኗል… ትርፍ ሰዓት ይከፍሉሃል?

ባይከፍሉኝም ታቂው የለ የስራውን ፀባይ… አመሌን ካላስተካከልኩ…

አመልህን ካላስተካከልክ ምን… ፕሮፌሽናል አይደለህ እንዴ? ግርድና አይደል የተቀጠርከው… 

አግባብ ያልሆነን ነገር መቃወም ነው… ምክንያት ፈጥረው ቢያባርሩህ እንኳን በችሎታህ ሌላ ስራ ፈልገህ ትገባለህ…

አቃለው ማሬ… ግን አሪፍ የስራ ልምድ እያገኘሁበት ስለሆነ ነው የምለማመጣቸው… ይልቁንስ እናትሽ እንዴት ሆኑ? ተሸላቸው?

ደህና ናት… ሰሞኑን ምግብ በደንብ እየበላች ነው…

ፍቅር ነገ ከነኤርሚ ጋር ቀጠሮ አለኝ እሽ… ከነገ ወዲያ እንገናኝ?

እንዴ! ትላንት ከነሱ ጋር አልነበርክ እንዴ?

አዎ ግን የሆነ ለስራ ጉዳይ የሚያስተዋውቁኝ ሰው ስላለ… ፕሊስ… እንዳይደብርሽ

ምና አደርጋለው… ሰሞኑን ደግሞ አዲስ ሙደ አምጥተሃል… ለስራ ጉዳይ ምና ምን… እያበዛህ ነው…

በቃ እንውጣ አይደል… ሂሳብ ከፈልሽ?

እንዴ! ገና አሁን መምጣትህ አይደል እንዴ? አዎ ግን… ሰሞኑን ባክሽ ሼባው ከመሬት ተነስቶ እየተነጫነጨ ስለሆነ በጊዜ ብገባ ይሻለኛል…

ስድስተኛው ወር
ሄሎ…
ሄሎ…
እንዴት ነሽ የኔ ቆንጆ?
አለሁልህ የኔ ፍቅር! አንተ እንዴት ነህ? ምሳ በላህ?
አሁን በላሁ… ከቢሮ ልጆች ጋር ትኩስ ነገር ጠጥተን ወደ ቢሮ እየገባሁ ነው… በቃ በኋላ… ስራ ስጨርስ እንገናኛለን እደውልልሻለው…
ሄሎ…
ሄሎ…
ወዬ የኔ ማር… እኔ ከቢሮ ልወጣ ነው ስንት ሰዓት እንገናኝ…
በቃ እኔም እየጨረስኩ ነው… እዛው እንገናኝ?
እሺ የኔ ፍቅር… እወድሃለው…
እሺ ቻው…

አንደኛ ወር
ሄሎ…
ሄሎ…
የኔ ቆንጆ… የኔ ማር… የኔ ፍቅር… እንዲማ አትናፍቂኝም…

እሺ ባክህ… እኔም ንፍቅ ብለኸኛል የኔ ጌታ… እስከ አስራ አንድ ሰዓት ሳላገኝህ የምውል አይመስለኝም… ለምሳ አትመጣም?

ብለሽኝ ነው… በእውነት የኔ ፍቅር ከጠዋት ጀምሮ አንድ ስራ አልሰራሁም… አንዴ ፎቶሽን ሳይ… አንዴ ሜስጅሽን ሳነብ… ላንቺ እራሱ ስንት ጊዜ ነው አይ ላቭ ዩ፣ አይ ሚስ ዩ… እያልኩ ሜሴጅ የላኩልሽ?

እኔ ራሴ ነፍዤልሃለው… አለቃዬ የሰጠኝን የሚፃፍ ወረቀት ስንቴ ኤዲት አድርጎ እንደመለሰልኝ ታውቃለህ… በልቡ "እቺ ልጅማ የሆነ ነገር ሆናለች…" ሳይል አይቀርም… ቀኑን ሙሉ ምን ስዘፍን እንደዋልኩ ታውቃለህ? ፍቅር ይዞኛል… ምን ይሻለኛል…

እኔስ ብትይ… ቢሮ ውስጥ በገዛ ራሴ ለፍልፌ… ብታይ ያለወራሁለት ሰው የለም… ፎቶሽን አሳይቻቸው ወደውሻል… አሁን ላንቺ ከመደወሌ በፊት እራሱ ፎቶሽን እያየው ፈዝዤ ቁጭ ብዬ አይተውኝ ምን እያሉ ሲዘፍኑብኝ እንደዋሉ ታውቂያለሽ… አዲስ ፍቅር እኔን ይዞኛል… የማደርገው ሁሉ ጠፍቶኛል….

በል በቃ የኔ ማር አለቃዬ እየደወለልኝ ነው… ለምሳ ቢሮ እንድትመጣ… እወድሃለው…

እሺ የኔ ልዕልት… እመጣለው… አፈቅርሻለው…




No comments:

Post a Comment