Wednesday, August 14, 2013

ድሮ ቀረ!


1.  ጊዜ ድሮ ቀረ!
ይሄ የድሮ ቀረ አባዜ… አንዳንድ ጊዜ ትርጉም አያጣባችሁም? ለምሳሌ… አንዱ ጓደኛዬ አስፓልት ዳር መኪናውን አቁሞ ሻይ እየጠጣ… የፓርኪንግ ሰራተኛዋ ትመጣና ቲኬት መኪናው ላይ ታደርጋለች… ትንሽ ቆይታ እንደገና ትመጣለች… ብዙም አልቆየችም (ለሱ እንደመሰለው)… ሌላ ሁለተኛ ቲኬት ትደርብበታለች ይሄን ጊዜ ጓደኛዬ… "እንዴ! ሰላሳ ደቂቃ ሞላው እንዴ?" ቢላት "የዘንድሮ ሰላሳ ደቂቃ ምን አላት ብለህ ነው…" ብላው መሄድ…
"ጊዜ ድሮ ቀረ እቴ!" በሚል አይነት…
እውነትም ግን… አስተውላችሁት ከሆነ… ዘንድሮ እኮ ጊዜው እንደ ቦልት ነው የሚሮጠው… የግድግዳ አልያም የእጃችን ሰዓት ላይ ያለው የሰዓት ቆጣሪው ዘንግ የተሰበረበት ዘመን ላይ ያለን ነው የሚመስለው… ሰዓቱ በደቂቃ ፍጥነት ሆኗል የሚነጉደው… ከሁሉ ደግሞ… ብሽቅ የሚያደርገው… ጊዜውም ይሮጣል፣ እኛም እንሮጣለን ግን ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩ ነው… በቃ አንዱንም ሳንይዘው ይመሻል…
ጊዜ ድሮ ቀረ እቴ!
የድሮ ጊዜ እንደ ፊውዳል መሪ ጅንን ብሎ፣ ጎርደድ… ጎርደድ… ይል ነበር አሉ… አሉ ነው… የዘንድሮው ግን ልክ መድረኩን ለሌላዋ እንደምታስረከብ የፋሽን ሞዴል ነጠቅ… ነጠቅ እያለ ነው የሚነጉደው… ይሄ አሉ አይደለም… ነው! አይ ጊዜ… ጊዜ ድሮ ቀረ እቴ!

2.  መሳሳም ድሮ ቀረ!
ሌላው ያሳቀኝ የድሮ ቀረ አባዜ… በመሳሳም (ስሞሽ) ላይ አንድ የቦሌ ጎልማሳ ያጫወተኝ ነው…
"ድሮ ድሮ… በአባቶቻችን ጊዜ… በእኔም የአፍላ ዘመን… የከፈንፈር ወዳጅ የሚባል ነገር ነበር… የያኔው ትውልድ… ከሴት እስከ ወንዱ፣ ከልጃገረድ እስከ ጎልማሳው ከንፈር ወዳጅ ነበር… እንዲህ እንዳሁኑ ጀነሬሽን "ወደ ገደለው!" ሳይሆን ማለቴ ነው…"
"መሳም ድሮ ቀረ እቴ!"

"ያኔ ድሮ… ስሞሽ የሚወደደው በብዙ ነገሩ ነበር… አንድም ድብቅ (አሳቻ ስፍራና ቦታ ተፈልጎ የሚደረግ ስርቆሽ) በመሆኑ… ሌላም በጥፍጥናው (በጊዜው የነበረ የአፍ ጠረን ልዩ በመሆኑ) ነበር… በጊዜው የነበረውን የአፍ ጠረን አስረዳለው…"
የድሮ አፍ ጠረን ልዩ ነው… አሁን ለምሳሌ ልጃገረዷ ቡናዋን ስትጋት ትውልና አንተ ጋር ትመጣለች… ያኔ ጠጋ ብለህ ስታወራት ማዛጋት ትጀምራለህ… የአፏ ጠረን ታጥቦ የተቀሸረ፣ ትኩስ፣ የይርጋጨፌ፣ አቦል ብና ያህል ያምርሃል… ትወሰወሳለህ… ወሬዋን ማዳመጥ ትተህ አይንህን ጨፍነህ ከንፈሯ ላይ ግጥም ትላለህ… አንድም ወጣትነት… ሌላም የቡና ሱስ…"
"መሳሳም ድሮ ቀረ እቴ!"

"ሌላዋ ደግሞ አለችልህ… ይሄን የስንዴ ቆሎ… አሊያም የሱፍ… አልያም፣ የማሽላ… አልያም፣ የሽምብራ ቆሎ ስትከካ ትውልና አንተ ጋር ስትከንፍ ትመጣለች… እንደለመድከው አፍ ለአፍ ገጥመህ ስተሰልቅ ይሄን ወሬ… የአፏ ጠረን… የሽ-ን-ብ-ራ-ው ጥርጥር የ-ዛ-ፎ-ቹ ፍሬ… ዝፈን፣ ዝፈን ያሰኝሃል… በቃ ምን ታደርገዋለህ… አይንህን ጨፍነህ ከንፈሯ ላይ ግጥም ትላለህ… አንድም ወጣትነት… ሌላም የቆሎ ሱስ…"
መሳሳም ድሮ ቀረ እቴ!  

"አሉልህ ደግሞ… አንዳንድ ልጃገረዶች… ይሄን ወተት፣ እርጎና ቅቤ ሲንጡና ሲጠጡ ይውሉና አንተ ጋር ይመጣሉ… እናም አፍ ለአፍ ገጥመህ ስታወራ… በቃ ምን አለፋህ… ኤ-ል-ፎ-ራ! እንደ በሬም እሞቧ! ማለት ያምርሃል… በቃ የሆነ አንዳች ነገር ይፈታተንሃል… አይንህን ጨፍነህ ከንፈሯ ላይ ግጥም ትላለህ.. አንድም ወጣትነት… ሌላም ሱሰ-ወተት…"
መሳሳም ድሮ ቀረ እቴ!  
ከፈለክ ደግሞ አለችልህ… ይሄን የሽንብራ፣ አልያም፣ የአተር፣ አልያም፣ የባቄላ እሸት ጁስ በጥርሷ ስትፈጨው ትውልና… ስትበር ትመጣለች… አንተ… (የከንፈር ወዳጇ ጋር)… ይሄን ጊዜ… አንድም በናፍቆት… ሌላም የወጣትነት ትኩሳት ይዞህ… አልያም የተገኘችውን አጭር የስርቆሽ ጊዜ ለመጠቀም… ከንፈሯ ላይ ግጥም ትላለህ… ይሄኔ የአፏ ጠረን… በግድ ያዘፍንሃል… እሸት በ-ላ-ሁ-ኚ… እሸት በ-ላ-ሁ-ኚ… አንደገና… አይንህን ጨፍነህ ከንፈሯ ላይ ግጥም ትላለህ… አንድም ወጣትነት… ሌላም ሱሰ-እሸት…"

አሉልህ ደግሞ… የዚህ ዘመን ቺኮች… ለዛውም… ለመሳሳም ጊዜ ከተረፋት… እንደለመድከው አፍ ለአፍ ገጥመህ ስታወራት… ሽቶ ይሁን ዶድራንት… የሆነ ባዕድ ሽታ ይሸትሃል… ታዲያ ሱስ ነውና ከንፈር… አይንህን ጨፍነህ ከንፈሯ ላይ ግጥም ስትል… የሆነ ሽቶ፣ ሽቶ የሚል የጣፋጭ ስኳር ቃና… ያኔ… ከአንገትህ ብለህ ቀና… ስትላት… "ምንድነው የአፍሽ ቃና?" አንገትህን ዝቅ አድርጋ ከንፈርህ ላይ ጥብቅ ትልና… "ምነው? ትሪደንት ማስቲካ ነው… ሽሽሽ… ዶንት ስፒክ" ትልሃለች… እያንዳንዷ ቦሌ የሳምካት ቺክ::"
"መሳሳም ድሮ ቀረ እቴ!"



No comments:

Post a Comment