Monday, July 22, 2013

ለምን?

ቦሌ መስመር ላይ ነኝ… ጃፓን ኢምባሲ አካባቢ… ወደ ድልድይ የሚሄድ ታክሲ እየጠበቅኩ… እኔ በቆምኩበት ፊት ለፊት (ተሻግሮ) ባለው አስፓልት የታክሲ ግፊ ላይ ቀልቤ አረፈ…

ሰዉ አስፓልት ላይ ሳይሆን የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ያለ ነው የሚመስለው… ፋወል በየአይነቱ ነው… በሰዉ የግፊያና የብሎክ ስትራቲጄዎች ተደምሜ አይኔን ሳልነቅል ቀረሁ… ታደያ ይሄኔ… ድንገት… አይኔ አንዲት እንስት ላይ አረፈ… "ዊንታ!" እንዴ! "ዊ-ን-ታ! እኔ አላምንም!"…

ዊንታ… ድሮ የኤለመንታሪ ተማሪ እያለው የምወዳት ልጅ ነበረች… ከኤለመንተሪ ከወጣሁ ጀምሮ አግኝቻትም፣ አይቻትም አላውቅም… ያ የልጅነት ውበቷ ላይ አሁን ደግሞ ዝነጣና እራስን መጠበቁ ተጨምሮበት ቀውጢ ቺክ ሆናለች…

ወዲያውኑ ተሻግሬ ላናግራት ወሰንኩ… እናም መኪና አይቼ ልሻገር ስል የመሃል አካፋይ መስመሩ በአፈር መሞላቱን አስተዋልኩ… አይኔ በሚችለው ርቀት ወደ ላይም ወደ ታችም ባይ ዜብራ መስመር የሚባል ከየት ይምጣ… ምንም እንኳን መንገድ ስሻገር በአብዛኛውና በተቻለኝ አቅም ዜብራ ፈልጌ ቢሆንም አሁን ግን የፕሪንሲፕል ሰዓት አይደለም… በቃ በአፈሩ ላይ ለመውጣትና ለመሻገር ወሰንኩኝ… ነገር ግን የመንገድ አካፋይ ቦታው የጉልበቴን ቁመት በሚያህል ኮንክሪት ዳርና ዳሩ ታጥሯል… በዛ ላይ ዝናብ ጥሎ ስለነበር አፈሩ ጭቃ ሆኗል… አማራጭ አልነበረኝም ዝም ብዬ ወደ ላይ መውጣት ጀመርኩ ዜብራ መስመር ፍለጋ…

ዊንታን አሁንም እያየኋት ነው… እሷ አላየችኝም… ስልኳን እየጎረጎረች ነው… ታክሲ መጣ… ስልኳን ትታ ግፊያውን ተቀላቀለች… ጮኬ መጣራትም አማረኝ… ወዲያው ኸረ... ይ-ደ-ብ-ራ-ል ብዬ ተውኩት… ታክሲው ከለለኝ… ወይኔ! ገባች? ሺት! አትታየኝም… ኦልሞስት መሮጥ ጀመርኩ…

ዜብራ ላይን አየሁ… ትንሽ ነው የቀረኝ ልደርስ ነው…. ታክሲው ተንቀሳቀሰ… ቆምኩ… የስ!… የስ! አለች… እድል አልቀናትም…
ምን ሆኜ ነው ግን? ለምንድነው ይሄን ያህል ላናግራት የፈለኩት? ማን ያውቃል… እግዜር ምን አስቦልኝ እንደሆነ… ለምንስ ታክሲው ውስጥ አልገባችም? በግፊያው ተሸንፋ የሚለውን ማሰብ አልፈለኩም… በቃ እግዜር እንደ አዳም በቀላሉ ሄዋኔን ከጎኔ ሻጥ ሊያደርጋት አስቦ ይሆናል አልኩ…

ተሻገርኩ… አሁን ደግሞ ወደሷ እየወረድኩ ነው… እንደገና ወደ ታች… ሌላ ታክሲ… ሺት! ልጣራ ይሆን… "ዊ.." ወዲያው ተውኩት… ሺት! ኡፍፍፍ… አጎነበስኩ… ትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ እያለ ነው… ሺት! ዊንታ ታክሲው ውስጥ ገባች…

ቆምኩ… የወቀሳ፣ የስድብ፣ የማማረር ሰዓት… አንደኛ- የኢትዮጲያ መንገዶች (ኮሮኮንቾች) ባለስልጣን… ሁለተኛ- ቻይና…

ሶስተኛ-ታክሲ… አራተኛ- ወያላ… አምስተኛ-ዝናብ… ስድስተኛ- ጭቃ… ሁሉንም ለመፃፍ የሚከብድ ፀያፍ ስድቦችን ተሳደብኩ…

እግዜርስ ቢሆን… መጀመሪያ ለምን አሳየኝ … ለምንስ በመጀመሪያው ታክሲ እንድትሄድ አላደረጋትም… ለምን ተስፋ ሰጠኝ…

እኔስ ብሆን… ለምን አልተጣራሁም… ለምንስ በደንብ አልተራመድኩም… ለምንስ አልሮጥኩም…

እሷስ ብትሆን… ለምን ከፊቴ ቆመች… ለምን አላየችኝም… ለምን ስልኳን ትጎረጉራለች… ለምን ተጋፍታ ገባች…
ለምን… ለምን… ለምን…

ሰው በአፉ እንጂ በእጁ አያነሳህም

በከተማችን ውስጥ በጣም ከምወደው ስፍራዎች መካከል አንዱ ብሔራዊ አካባቢ ነው፡፡ ብሄራዊ ቲያትር አካባቢ… እነ ክሮኮዳይል፣ ናሽናል ካፌ መደዳ… ከወጣት እስከ አዛውንት፣ ከሰራተኛ እስከ ጡረተኛ እግሩን አነባብሩ፣ ቡና እየጠጣ ጋዜጣ የሚያነብበት መደዳ…

በጣም የሚገርመኝ ያ መደዳ ሁልጊዜም አንድ አይነት ምስል ነው ያለው… የተነባበሩ እግሮች፣ የተዘረጉ እጆች፣ የትኩስ ቡና ሽታ፣ የተዘረጉ ጋዜጦች…

ብሔራዊ አካባቢ ሰው ሲቀጥረኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ… በቃ እገሬን አነባብራለዋ፣ በጋዜጣ ቁመት ልክ እጄን እዘረጋለው፣ ከዛም ቡናዬን ፉት፣ ፉት እያልኩ አላፊ አግዳሚውን እገረምማለው፤ የዚያ የሚያምር ትዕይንት አካል መሆን አስደሳች ነገር ነው፡፡

ታዲያ ከትላንት በስቲያ ነው፣ አንድ ጓደኛዬ ብሔራዊ አካባቢ እንገናኝ ሲለኝ ፈነጠዝኩ… ቀድሜ ደረስኩና ጫማዬን አስጠረኩ፤ ምክንያቱም በቆሻሻ ጫማ እግር ማነባበር ይደብራላ! የውቡን ትዕይንት ቀለም ያጎድፋል፡፡

ጓደኛዬ እስኪመጣ ጋዜጣዬን ገዝቼ ናሽናል ካፌ በር ላይ ተሰየምኩ፤ በጋዜጣው ቁመት ልክ እጄን ዘረጋሁ (እጄን ስዘረጋ በቲሸርቴ በኩል ወደ ብብቴ የገባው ቀዝቃዛ አየር ምናምን አልላችሁም ያው ዲስከስቲነግ ስለሆነ ማለቴ ነው) ከዛም እግሬን አነባብሬ ቡና እንደወረደ አዘዝኩ… ቡናዬን ፉት እያልኩ አልፎ አልፎ በጋዜጣው አናት ወጪ ወራጁን እቃኛለሁ…

አንድ ፅሁፍ አንብቤ እንደጨረስኩ ለአፍታ እረፍት አይኔን በጋዜጣው አናት ሽቅብ ከፍ አድርጌ አላፊ አግዳሚውን ማጤን ጀመርኩ…

አንድ ወጣት ላይ አይኔ አረፈ ጥድፍ፣ ጥድፍ እያለ እየተራመደ ነው፤ በቅጡ ከፍ ዝቅ አድርጌ ሳላየው ከመቅፅፈት… የተፈታ የጫማ ማሰሪያው አደናቅፎት በእርምጃው ፍጥነት መሬት ላይ ተዘረገፈ… ይህን ጊዜ የሁሉም ጋዜጣ አንባቢዎች አይን ወጣቱ ላይ አረፉ… የተወሰኑት "አይዞህ!" ግማሾቹ "ወንድሜን!" ሌሎቹ "ተነስ! ተነስ!" ብለውት መልሰው አይኖቻቸውን ጋዜጦቻቸው ላይ ቸከሉ፡፡


ወጣቱም ፊቱ ላይ የአፍረት ፈገግታ እያሳየ ፍንጥር ብሎ ተነስቶ ሱሪውን ካረጋገፈ በኋላ የጫማ ማሰሪያውን አስሮ በፍጥነት ከፊታችን ተሰወረ… ከእኔ ህሊና ግን ሳይሰወር ቀረ… በወቅቱ የነበረውን ትዕይንት ሰፋ አድርጌ አሰብኩት…

በቃ! ህይወት ማለት እኮ እንዲህ ናት! አልኩ… ላይ፣ ታች ትላለህ፣ ትውተረተራለህ… በመሃል እንደ ወጣቱ ልጅ የራስ ጫማ ክር፣ አልያም በሰው ክር ተደናቅፈህ ትወድቃለህ፤ ታዲያ ወንድም ሆይ… ማንም አደናቀፈህ፣ ምን ሁሉም እግሩን አነባብሮ "አይዞህ!" "ተነስ!" ሊልህ ይችላል አንጂ እጁን አይሰጥህም (እሱንም ስበህ የምትጥለው ይመስል) ማንም አያነሳህም፤ በራስህ ሀይል ተነስተህ፣ አባራህን አራግፈህ፣ ያላላውን አጥብቀህ ጉዞህን መቀጠል ነው…

አይግረምህ… ህይወት እንደዚህ ናት፤ እግሩን ባነባበረ ታዛቢ ፊት የምትወድቅና የምትነሳባት፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ሆይ! አንድ ነገር ልምከርህ… በህይወት ሩጫህ ባንተም ይሁን በሰው ክር አደናቅፎህ ብትወድቅ፣ አንሺ አገኛለው ብለህ ወድቀህ እንዳትቀር! አወዳደቅህ ምንኛ ቢከፋ እንደምንም ብለህ ተፍጨርጭረህ ተነስ! ሰው በአፉ እንጂ በእጁ አያነሳህምና! "መሮጥ ቢያቅትህ፣ ተራመድ፣ መራመድ ቢያቅትህ፣ ዳህ፣ መዳህ ቢያቅትህ፣ ተንፏቀቅ…" ነገር ግን በፍፁም ወድቀህ እንዳትቀር ማንም ሊያነሳህ እጁን አይሰጥህምና!

ጉዞ አልባው የጉዞ ማስታወሻ

ይቺ የጉዞ ማስታወሻ ከሌሎች የጉዞ ማስታወሻዎች በእጅጉ ትለያለች፤ "እንዴት?" አትሉም…

ሲጢጢጥ…. በናታችሁ… ቆይ… አንዴ… ታይም አውት… ወደ ዋናው ፅሁፌ ከመግባቴ በፊት አንድ ነገር ልበላችሁ…

መቼም የመጀመሪያዋን አረፍተነገር ስታነቡ… "በምን ይሆን ይቺ የጉዞ ማስታወሻ የተለየችው?" ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም፤ ወይም ደግሞ… "እቺማ እንደ ዘንድሮ ማስታወቂያ አገባብ ማሳመሪያ ናት፣ ለሽያጭ ናት…" ብላችሁ ይሆናል፡፡ አትፍረዱብኝ… ዘንድሮ እኮ ሁሉ ነገር ውድድር ሆኗል፤ ሁሉ ነገር ሽያጭ ሆኗል…

ኢንፎርሜሽን እንኳን ሳትፈልግ በግድህ የምትጋትበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የቱን አንብበህ፣ የቱን መተው እንዳለብህ ለመምረጥ እንኳን ፋታ አታገኝም፤ ዞር ስትል ጋዜጣ ነው፣ ዞር ስትል መፅሄት ነው፣ ዞር ስትል እንትናዬ እቺን ፍላየር ነው፣ ግድግዳው፣ ታክሲው፣ ባሱ፣ ልብሱ… ሁሉ ነገር ማስታወቂያ ነው፣ መረጃ ነው፡፡

ታዲያ አንዳንዴ… ሁሉ ነገር ይሰለችህና የፅሁፍ ጋጋታ የሌለው ዕይታ ናፍቆህ ወደ ሰማይ ስታንጋጥጥ ሰማይ ላይ ተሰቅለው ሰማይ አላሳይ የሚሉ፣ ሰማይ ጠቀስ ቢልቦርዶች ያጋጥሙሃል… በቃ እንደለመደክው ሳትወድ በግድህ ወደ ሐበሻዊነትህ ትመለሳለህ… አንገትህን ትደፋለህ… ያለ ቅንነትህ ቅን ትመስላለህ፤ የወደቀ ዕቃ የምትፈልግ ይመስል በግድ አንገትህን ቀብረህ ትርመሰመሳለህ…

እናም ይህ ሁኔታ ባለበት፣ እንደ ፀሃፊ፣ ለምትፅፈው ፅሁፍ አንባቢ አገኝ ይሆን ብለህ መጠየቅህና መስጋትህ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው ምንግዜም ፅሁፌን ስጀምር፣ የመጀመሪያዋን አረፍተነገሬን ረጅም ሰዓት ወስጄ የማስበው፡፡ አስቤ፣ ሰርዤ፣ ደልዤ በቃ በምርጥ አረፍተነገር እገባለሁ… የዛሬው ግን እንደዛ አይደለም፣ በቃ ፅሁፉ እራሱ ለየት ያለ ነው… ብትፈልግ አንብብ ባትፈልግ ተወው! አልልህም… አንብበው… ገዳይ ወግ ነው፡፡

ስለዚህ ደግሜ እላችኋለው… "ይህች የጉዞ ማስታወሻ ከሌሎች የጉዞ ማስታዎሻዎች በእጅጉ ትለያለች" አሁን በቀጥታ ወደ ነገሬ ልገባ ስለሆነ… "እንዴት?" በሉ… ነገሩ እንዲህ ነው…

የጉዞ ማስታወሻ ሲባል አንድ ሰው ወደ አንድ ቦታ በሄደበት ወቀት ያጋጠመውን፣ ያስተዋለውን፣ የሰማውን፣ ያነበበውን… ሌላም ሌላም ነገሮችን አክሎ፣ ውብ ስነፅሁፋዊ ጥበብን አላብሶ የሚያቀርበው ፅሁፍ ነው፡፡ ይህች የጉዞ ማስታወሻዬ ግን እኔና ጓደኞቼ አንድ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለን፣ በምርቃና ባቡር ተሳፍረን፣ በሃሳብ ሰረገላ ተጉዘን፣ ያየናቸውን፣ የተገነዘብናቸውንና፣ የተዝናናንባቸውን፣ ግብብዳ የሳቅ እንባ ዘለላዎችን የተረጫጨንባቸውን ጉዳዮች ለናንተ የማጋራባት፣ ጉዞ አልባ የጉዞ ማስታወሻ ናት፤ ንሱማ… ዝለቁ…

ወደ ጉዟችን ከመዝለቃችን በፊት… አብረውኝ የሚጓዙትን ተሳፋሪዎች በጥቂቱ ላስተዋውቃችሁ…

ሼባው- ሼባው ‘‘እድሜው ትልቅ ነው…'' እያልን የምናማው ጓደኛችን ነው… የምር ግን… በቅንፍ ውስጥ… ድምፄን ዝቅ አድርጌ… ይቀቅመናል!

ሌላው ሰላ ነው፤ ሰላ በቃ መመርቀን የሚወድ፣ የግሩፓችን ዋና የቀልድ አከፋፋይና ብቸኛ አስመጪ ነው፡፡

ጎሹ ደግሞ እንደ ጎሽ ትከሻው ሰፊ እና በጭንቅላቱ ሳይሆን በቀንዱ የሚያስብ ብለን የምናሞካሸው ጓደኛችን ነው፡፡

አለችላችሁ ደግሞ ኤም.ፒ.ስሪ (mp3)፡- mp3 ሴት ጓደኛችን ስትሆን በቃ ነን እስቶፕ ቀዳጅ ናት፣ የወሬ ቋት…

ሌላዋ የግሩፑ አዝናኝ ደግሞ ግራ ናት፤ ግራ ወሬዋ ሁላ ግራ የገባውና የራሶችዋን ቃላቶች በመፍጠር የምትታወቅ ናት፤ በሷ አመርኛ መልሼ አማርኛዋን ስገልፀው… ‘አማርኛዋ የተንቦራደሰ ነው…'

ቀንዶ- ቀንዶ በተረበኛነቱና በአረቄ አፍቃሪነቱ የሚታወቅ ጓደኛችን ነው…

ፌዶ- ሃርደኛ ጀለሳችን ናት፣ ከመሬት ተነስታ ፊትዋን የምትፈጠፍጥ ወይም በኛ አገላለፅ ዝም ብላ ጓ! የምትል…

ሱፔ ደግሞ የራሱ ቋንቋ ያለው ወጣ ያለ ጓደኛችን ነው…

በሉ በሉ… እኔ ሃተታዬን ሳበዛ ጉዞው ሊጀምር ነው፤ እኔን ጨምሮ አስር ተጓዦች ባቡሩ ላይ ተሳፍረናል… እንደለመድኩት በመስኮት በኩል ተቀምጫለሁ… አብራችሁኝ ተጓዙ….

ሰላ፡ አያምርም? እስቲ እየው በናትህ! እንዴት አባቱ ለምለም ነው ባክህ… ደግሞ ዝንፍልፍል ማለቱስ የሚናቅ ነው? ካካካካ….

ጎሽ፡ ፐ! ምርጥ ነው… አንተ እስከ ዛሬ የት ሆነን ነው… እዚሁ አጠገባችን ሆኖ ሳናየው… ተሸውደናል! ሁለተኛ ከሉሉ በለጬ አንገዛም? እየው እስቲ፣ እጁ እራሱ… አንደኛ ነው… በዛ ላይ ቅላቱ…

ሱፔ፡ ኢግሩስ እራሱ…

ሁላችንም ካካካካካ… ሱፔ ከወሬው ይልቅ የአነጋገር ዘይቤው (አክሰንቱ) ሽንታችንን ነው የሚያስጨርሰን፡፡ አማርኞቹን እያንሻፈፈ ነው የሚያወራቸው፡፡

ቀንዶ፡ አቦ ሰዓት የለም… አምጣው ባክህ እንቃምበት… ዝም ብለህ አታሽሞንሙነው…
ኤም.ፒ.ስሪ (mp3)፡ ቀንጥሱልኝ?
ግራ፡ እኔ ልበጥስልሽ?
ባቡሩ በሳቅ ድብልቅልቁ ወጣ... ሰላ አልቻለም፣ መሬት ላይ እየተንከባለለ እየሳቀ ነው…

ሼባው፡ ሳቁን በአግባቡ ሳይጨርስ… አንቺ በጣሽ! አይሻልሽም እኔ ልሸልቅቅልሽ…
እንደገና ሌላ ረጅም ሳቅ…

ሱፔ፡ እቺ… ብጣሻም… ባሳቅ ፈረፈረችን እኮ…

ፌዶ እንደልማዷ ጓ! ብላለች፤ ሁላችንም ከልባችን እየሳቅን ነው፤ እሷ ግን አልፎ አልፎ ጥርሷን ብልጭ እያደረገች ተቆልላ ተቀምጣለች፡፡

ሰላ፡ አቦ ፌዶ ፈታ በይ… ቱታ ልበሺ… የምን ጓ! ማለት ነው…

ፌዶ መልስ አልሰጠችም፤ ከጥፊ ባልተናነስ ግልምጫ ገርምማው ሲጃራዋን ለኮሰች… ጉዞው ቀጥሏል… ባቡሩ በጭስና በወሬ ታፍኗል… mp3 እንደ ልማዷ ‘‘አንዴ ስሙኝማ…'' እያለች የተጓዡን ቀልብ ለመሳብ ትቅለበለባለች…

ጎሽ፡ አረ! ሽንቴን ወጠረኝ…
ይህን ጊዜ ሁላችንም እረፍት ለማድረግ ወሰንን… ሽንቱ የመጣበት ሽንት መሽኛ ፍለጋ… ትኩስ ነገር የሚፈልገው ሲኒ ማንኳኳት… ስልክ የሚደውለው ስልኩን ይዞ ጎምለል ጎምለል… እኔም የጉዞ ማስታወሻዬን በምስላዊ መረጃ ለማስደገፍ መቅረፀ-ምስሌን ብድግ አድርጌ… ቀጭ… ቀጭ… ቀጭ… ከደቂቃዎች በኋላ ተጓዦች ከየዕረፍቶቻችን ተመለስን… ወደ አንድ መንፈስ…

ቀንዶ፡ እስቲ የጉዞ ከፍታ አሳውቁ… ምርቃና ሌቭል ቼክ… ቼክ… ቼክ…
ግራ፡ እስውቅ
ሼባው፡ እኔ ክላውድ ናይን ላይ ነኝ…
ጎሹ፡ በሌቭል ከሆነ የኔ ሬድ ሌቭል ነው… ትንሽ ስቆይ ደግሞ ብላክ ሌቭል ይሆናል…

ካካካካ… ባቡሯ እንደገና የሳቅ ጭስ አፈናት… የጎሹ እንግሊዘኛዎች አድክም ናቸው… እንግሊዘኛና እሱ እጅና እግር ናቸው… አይገናኙም…

ሱፔ፡ እስቴኪኒ ያየ አለ?
ግራ፡ አ-ላ-የ-ን-ም እባካችሁ… መሃረቤን አያችሁ የሚለው ትዝ ብሎኝ ነው…
ፌዶ፡ አንቺ እብድ…
ቀንዶ፡ የምሳው ሽሮ ጥርስህ ውስጥ ተቀርቅሮ ነው?
ሱፔ፡ አይ! ቅድም ያጨስኩት ሲጋራ ጭስ ተቀርቅሮብኝ ነው…
እንደገና ሌላ ሳቅ…

mp3፡ ስሙኝማ…
ሰላ፡ አረ! ቆየን ከሰማን የሚጋግርብን አጣን እንጂ…
ካካካካ… ካካካካ… ካካካካ…

ወሬው ደርቷል… ይቀለዳል… ይሳቃል… በቃ ሙሉ መንገዱ አዝናኝ ነው… ሁሉም እብድ ናቸው፤ በቃ ጤነኛ ወሬ የሚያወራ የለም፡፡ mp3 በሰላ ትረባ ተናዳ ነው መሰለኝ ለተወሰነ ደቂቆች ‘ስሙኝማ' አላለችም… ኡፈይ ብለናል…

ግራ፡ አንተ ሰላ! mp3ን በቅድሙ ትረባህ mp0 (አም.ፒ.ዜሮ) አደረ‘ካት እኮ … አላወራም አለች…

ካካካካ… ካካካካ… ሰዓሊው እንደለመደው መሬት ላይ እየተንፈራፈረ ነው… ሼባው መሬት በእጁ እየደበደበ ይንከተከታል…

ምን አለፋችሁ… በቃ አንዲሁ በሳቅ አንጀታችን እንደቆሰለ፣ እንዲሁ ‘ስሙኝማ' እንደተባልን፣ እንዲሁ ጓ! እንደተባለብን፣ የጉዛችን መዳረሻ ተቃረበ…

ሱፔ፡ በሉ ደረስናል እንውረድ…
ጎሹ፡ እራት የሚበላ አለ? …ሁሉም ዝም…
ቀንዶ፡ በቃ ወደ አልጋችን ከመሄዳችን በፊት… አንዳንድ እንበል… ይህን ጊዜ ሁሉም እቃውን እየሸካከፈ፣ እየተጣደፈ ወረደ…

በሉ! ለዛሬው ይብቃን፤ እኔም ክፍሎቼን ዕቃዎቼ ውስጥ አስገብቼ… ምንድን ነው ያልኩት? እእእ… ዕቃዎቼን እክፍሌ አስገብቼ አንድ ሁለት ልል ነው… ማለቴ ነው… ‘መረቀንኩ እንዴ?'… በሉ በሉ… አፌ ተሳሰረ… ጉሮሮየም ደርቋል… ቀላል ጠምቶኛል… በሌላ የጉዞ ማስታወሻ እስክንገናኝ… ሰላም!

ከተቀማጭ ወደ ሯጭ ፕሬዝዳንት

የሆነ ሰሞን ከተማችን ላይ ኢንፎቴይመንት የምትል የፅሁፍ ውጤት ነበረች… በነገራችን ላይ ‘ኢንፎቴይመንት’ኢንፎርሜሽንን እና ኢንተርቴይመንትን በማዋሃድ የተፈጠረች ቃል ነች... እኔ ደግሞ ዛሬ የማጫውታችሁ ፖሊቴይመንት የምትባል ወግ ነው ፖለቲካን ከኢንተርቴይመንት አዋህጄ…

ዘንድሮ መቼም ጦቢያችን አልተቻለችም፣ በድል ላይ ድል፣ በሪከርድ ላይ ሪከርድ… አዳዲስ አስፓልቶች፣ አዳዲስ ካቢኔ፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስቴር… የአባይ ግድብ፣ የከተማ ባቡር… ሌላም፣ ሌላም…

አዲስ አበባማ አይናችን እያየ እንደ ስሟ አበባ ልትሆን ነው… ከጥቂት አመታት በኋላ ደግም አገራችን አራሷ የማናውቃት ኢትዬጲያ ልትሆንብን ነው…

በተለይ በዚህ አመት ልክ እንደ ዋልያዎቹ ማልያ፣ ‘ኢትዮጲያዊነቴ ኩራቴ’ የሚለው ቲ-ሸርት እንደ ጉድ እየተቸበቸበ ይመስለኛል…

ለምሳሌ… ይሄ የሰሞኑ የካቤኔ ሹም ሽረት… ሲቪሪ ሜሞሪ ሎስ ቢያጋጥመኝ እንኳን ስማቸውን የማልረሳውን የሚኒስቴሮች ስም ከዋናው መድረክ በስተጀርባ ያደረገበት ሁኔታ ነው ያለው… እውነቴን እኮ ነው! ለውጥም በሉት ልወጣ... የስንት ሚኒስቴሮችን ስም እንደ አዲስ እንደምንሸመድድ አስባችሁታል?

ድሮ፣ ድሮ "እገሌ የሚባል ሚኒስቴር መ/ቤት የት እንደሆነ ታውቃለህ?" ብሎ ሰው ሲጠይቀኝ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ስም ይልቅ የሚኒስቴሩ እና የሚኒስቴር ድኤታው ስም ነበር ቶሎ ወደ አይምሮይ ከች የሚለው… የሚኒስቴር ስምና የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስም ልክ እንደ አረፍተነገር የማይለያዩ ነገር ይመስሉኝ ነበር… ልክ "አበበ…" ሲባል "…በሶ በላ" የሚለው እንደሚመጣብኝ አይነት…

ይሄ… አዲስ ነገር በመፅሄት እንጂ በህይወቱ የናፈቀው ህዝብ በአሁኑ ሰዓት አዲስ፣ አዲስ ኢትዬጲያ እየሸተተችው ያለበት ሁኔታ ነው ያለው.. አስቡት እስቲ እቺን ጋዜጣ እንኳን ሳይቀር በባቡር ላይ ሆናችሁ የምታነቡበት ጊዜ እኮ እውን ሊሆን ነው…

መቼም… ያልሰማህ ስማ፣ የሰማህ አሰማ ነውና ብሂሉ… ከተማው ላይ የሚናፈሰውን አዲስ ወሬ ሰምታችኋል? ሰምታችሁ ካልሆነ… ቀጣዩ የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት የመሆን እጣ ፋንታ ሊደርሳቸው ከሚችሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ… እውቁ፣ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ መሆኑን በሰፊው እየተናፈሰ ነው…

ይህ ወሬ አሉባልታ ከመሆን አልፎ እውነት-ባልታ ከሆነ ለሀይሌም ይሁን ለአገራችን ትልቅ ስኬት ነው፤ እኛም ልክ እንደ አማሪካ ‘የስ ዊ ካን’ ወይም እንደ ሀይሌ ‘ይቻላል!’ የምንልበት ጊዜ ሊመጣ ነው ማለት ነው…

‘ዌል እንግዲክ’ እንደዛ ሊሆን ነው ብለን እናስብና… ምን አይነት ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ ወደሚለው እንሂድ…

እስከማስታውሰው ድረስ… ኢትዬጲያ ፓርሊያመንታሪ ስርዓት ተከታይ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዬጲያ ፕሬዘዳንት ስራ ምንድነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ… አንደኛ- አሪፍ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ለአዲስ አመት እንዲሁም ለህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማንበብ፤ ሲቀጥል፣ የምረቃና የሽልማት ፕሮግራሞች ላይ መሳትፍ ነው… እነዚህም ዝግጅቶች ላይ አጭር ንግግር አድርጎና ባስ ካለም ሪቫን ቆርጦ ቁጭ ማለት ነው… ባጭሩ በፓርላመንተሪያን አገራት ያለው የፕሬዝዳንት የስራ ሃላፊነት የአገር ተጠሪነት እንደመሆኑ ‘ቁጪያ’ እንጂ ያን ያህል ሩጫ አይበዛውም…

እንግዲክ… ሀይሌ ፕሬዝዳንት ሲሆን እንዴት አስችሎት ሊቀመጥ ነው? እስቲ አስቡት… ቤተ-መንግስቱ ውስጥ የመሮጫ ትራክ ሊሰራ ነው ማለት ነው… በቀን ሁለቴ ጠዋትና ማታ ትሬይኒንግ… ስራ ካልተደራረበ ደግሞ በሃይሌ ፅናት ቀኑን ሙሉ ግቢዋን ሊዞራት ነው…
እርግጠኛ ነኝ ሀይሌ የአዲስ አመት የመልካም ምኞት ሲሰጥ እንደ ቀደምት ፕሬዝዳንቶች አሪፍ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ሳይሆን… ልክ የመሮጫ ትራክ ላይ እንዳለው የሩጫው ‘የመጀመሪያ መስመር’ (start line) አለ አይደል፣ እሱ መስመር ላይ አሮጌው አመት የሚል ይፃፍበታል ከዛ ‘የመጨረሻው መስመር’ (finishing line) ላይ ደግሞ አዲሱ አመት የሚል ይፃፍበትና ‘ፕሬዝዳንት’ ሀይሌ ገብረስላሴ ከመጀመሪያው መስመር ተነስቶ ወደ መጨረሻው መስመር በመሮጥ ሪቫኑን ይበጥሰውና፣ በኩራት… የባንዲራ ዘንግ በአፉ ሳይሆን በእጁ ይዞ… "እንኳን ከአሬጌው አመት ወደ አዲሱ አመት በሩጫ አደረሳችሁ!" ይለናል ማለት ነው…

ሌላው ደግሞ… የሆነ የቦኖ ውሃ ወይም የአዲስ ትምህርት ቤት ምረቃ ላይ ሀይሌ ሪቫን እንዲቆርጥ መቀስ ሲሰጠው ያው እንደለመደው መቀሱን ጥሎ እየሮጠ ሄዶ ሪቫኑን በደረቱ ይበጥሰዋላ… ከዛ ስፖርት-ኮላ አሁን ገበያ ላይ ስለሌለ ኮካ-ኮላ በአንድ ትንፋሹ ይጨልጥና… እምምምም…. "ኢ-ት-ዮ-ጲ-ያ!" ይላል… (ኮካ-ኮላዎች፣ በዚህ አጋጣሚ ለማስታወቂያዋ ሰሞኑን ቢሯችሁ እመጣለው)

በቃ ምንአለፋችሁ… በአጭሩ… ኢንቨስተር፣ ሯጭ፣ አዝናኝ፣ የአገር ሽማግሌ… ሌላም ሌላም… የሆነ ፕሬዝዳንት ሊኖረን ነው… አልቸኮላችሁም? ቀላል ቸኩያለው!
ቆይ ግን ሀይሌ ፕሬዝዳንት ሲሆን ሱፍ ነው ወይስ የብሄራዊ ቡድኑን ቱታ የሚለብሰው? መቼም ሱፍ ከለበሰ አዲዳሶች (adidas Company) የሚቀየሙት ይመስለኛል… ያለበለዚያ ግን አዲዳሶች እራሳቸው ሱፍ ማምረት ሊጀምሩ ነው ማለት ነው… እርግጠኛ ነኝ ደግሞ እንደሚያደርጉት… ምክንያቱም እንኳንስ ፕሬዝዳንት ሆኖ ቀርቶ ድሮም ሀይሌያችን አለም አቀፍ ተፅኖ ፈጣሪ ነዋ!

እኔ እምለው… ሀይሌ ፕሬዝዳንት ሲሆን መሮጥ ያቆማል ማለት ነው? ቢያንስ በአለም አቀፍ ደረጃ እንኳን ባይወዳደር ታለቁ ሩጫ ላይ አይሮጥም? እንደኔ እንደኔ ግን በአለም አቀፍ መድረክ ቢያንስ አንዴ ሮጦ ‘ባለ ወርቅ መዳሊያው ፕሬዝዳንት’ ተብሎ ጊነስ ላይ ስሙን ማስመዝገብ አለበት…

ከዛ ወደ ኢትዬጲያ መጥቶ አቀባበል ሲደረግለት ማሰብ ነው… ክቡር፣ አትሌት፣ ‘ፕሬዘዳንት’ ሀይሌ ገብረስላሴ በምክትል ፕሬዝዳንትና እንትን ሚኒስቴሩ በአቶ እገሌ የአበባ ጉንጉንና ይሄን ያህል ሄክታር መሬት ስጦታ በሽልማት መልክ ተበረከተላቸው ምና ምን አይነት ዜና እንሰማለን… አሁንም… እንደኔ እንደኔ ሀይሌ ቢያንስ የጊነስ ቡኩ ሪከርድ ቀርቶበት ለመሬቷ ሲል ቢሮጥ አሪፍ ነው… ምክንያቱም የመጨረሻው ነዋ የምትሆነው… ኋላ ፕሬዝዳንት ሲኮኑ ሀብት ማስመዝገብ ምና ምን የሚባል ነገር ስላለ ማለቴ ነው…

እርግጠኛ ነኝ ሀይሌ ፕሬዝዳንት ሲሆን የቱሪስቶች ቁጥር እንደሚያሻቅብ… በቃ አገራችን ከታሪካዊ መስህቦቿ ባሻገር አዝናኝ የቱሪስት መስህብ ልትሆን ነው… ከነ ሉሲ ይበልጥ ቤተ መንግስቱ በበርካታ ቱሪስቶች ሊጎበኝ ነው… (Run with the president) ‘ከፕሬዝዳንቱ ጋር ሩጥ’ የሚል ፕሮግራም እያዘጋጁ ይሄን ዶላር መሰብሰብ ነው…

ሌላው ስፖርት ኮሚሽኑን በሚኒስቴርነት ደረጃ እንዲቋቋምም ሎቢ ሊያደርግ ይችላል የሚል ግምት አለኝ… እናም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አመታዊ የበጀት ድልድል ሲወጣ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለስፖርታዊ መሰረተ ልማቶች እንደሚመደብም ከወዲሁ መገመት አያዳግትም… ፓርላማው ባያፀድቀው እንኳን ሀይሌ ከግል አካውንቱ ፈሰስ ሊያደርግ ይችላል የሚል ግምት የለኝም… ምክንያቱም እሱ የቢዝነስ ሰው ነዋ! "ቀጥተኛ ትርፌ ምንድነው?" የሚል ጥያቄ መጠየቁ አይቀርም…

ዌል እንግዲክ… የዛሬውን ፖሊቴይመንቴን በዚሁ ላብቃ፤ ስለ ሀይሌ ፕሬዝዳንትነት ሳስብ የታዩኝ ጉዳዬች ለዛሬ እኒህ ናቸው፤ ሰንበት ብሎ አዳዲስ ሃሳብ ከመጣልኝ፤ እንደገና እመጣባችኋለው… ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር!
.....................
በነገራችን ይህች ፅሁፍ በቀጣዩ ማክሰኞ በኢትዮ-ምኀዳር ላይ ትወጣለች፤ በዚህ አጋጣሚ ጋዜጣውን ገዝታችሁ ሌሎችንም አሪፍ፣ አሪፍ ፅሁፎች እንድታነቡ እጋብዛችኋለው…