Wednesday, August 14, 2013

የወንደላጤውና የሰራተኛዋ ሜሞ ቁጥር-2


ቁጥር አንድ በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የታተመ ሲሆን በአንድ ወቅት፣ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት አብሮኝ ይሰራ ስለነበረ ወንደላጤ ባልደረባዬና ሰራተኛው የምንጨዋወትባት፣ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተች ወግ ናት…

ሜሞዎቹን ናሆም ቢሮ እያመጣ ያነብልን ነበር… በአሁን ሰዓት ናሆም ኢትዮጲያ ውስጥ ስለማይገኝ በአካል አገንቼ ሜሞዎቹን ልቀበለው አልቻልኩም… ስለዚህ፣ ከፊሎቹ ያኔ ናሆም ሲያነብልን አይምሮዬ ውስጥ የቀሩ ሲሆኑ፣ ገሚሶቹ ደግሞ በምናብ እንደ እነሱ ሆኜ የፃፍኳቸው ናቸው…

ቁጥር አንድን ላላነበባችሁ እንደ መግቢያ፡

ናሆም፡ እድሜው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ምርጥ ልጅ ነው፤ በቃ ሙድ የገባው የመንግስት ሰራተኛ፣ የአራዳ ልጅ የምትሉት አይነት… ተቆራርጣ የምትደርሰው የወር ደሞዙ ባለ አራት ዲጅት ልትሆን ትንሽ የቀራት… በዛችው ደሞዙ ቤት ተከራይቶ ተመላላሽ ሰራተኛ ቀጥሮ የሚኖር… ‘እቺን ደሞዝ በምን አይነት ብልሃት ነው የምታብቃቃት?' ሲባል ‘በአስማት' የሚል፣ ኑሮን ቀለል አድርጎ የሚኖር ምርጥ ልጅ…

ገበያነሽ(ጋቢ)፡ እንደ ናሆም ሁሉ ሙድ የገባት ስትሆን፤ ጎበዝ፣ የ10ኛ ክፍል የማታ ተማሪ ናት፡፡ ናሆምን ጨምሮ ወደ አምስት የሚደርሱ ወንደ-ላጤዎች ጋር በመስራት ራሷን የምታስተዳድር ሁለገብ ፍሪ-ላንሰርም ነች… ጋቢ በጠዋት ተነስታ የሁለት ወንደ-ላጤ ቤቶችን ስራ አቀለጣጥፋ ጨርሳ ናሆም ቤት ወደ አራት ሰዓት ገደማ ትደርሳለች፡፡ ናሆም ደግሞ ከእሁድ በስተቀር ከሁለት ሰዓት በፊት ከቤቱ ስለሚወጣ ከጋቢ ጋር የሚገናኙት በ‘ሜሞ' (አጭር የፅሁፍ ማስታወሻ) ነው፡፡

እነሆ የናሆምና ጋቢ ሜሞዎች፡

ቀን፡ 22/11/2003ዓ.ም
ይድረስ ለናሆም፡
ፒስ ነው ናሆሜ ይሄ ብርድ እንዴት ይዞሃል? ደሞ ክረምት መጣ… ያቺን ጃኬትህን ልትነቀሳት ነው… ቂቂቂቂ እረ! እንደምንም ብለህ አንድ ጃኬት ጨምር… ክረምት ክረምት ምን እንደምትመስለኝ ታውቃለህ? ተንቀሳቃሽ ሀውልት… አንዳንዴ እንደውም አንተን ሳይህ የአምናውና የዘንድሮ ክረምት አንድ ይመስሉኛል… ቂቂቂቂ.. ለኔ ግን ተመችቶኛል ለሶስት ወራት አንድ የማይታጠብ ልብስ አለ ማለት ነው... ቂቂቂቂ…
እኔ እምልህ ወሬዬን በነገር ጀመርኩ አይደል? ትላንት እኮ ጉንፋኑ ነው መሰለኝ ሀይለኛ ራስ ምታት ይዞኝ ከቤት ሁላ አልወጣሁም… sorry ለዛ የነው የቀረሁት… ቆይ ግን… አንድ ቀን መስሎኝ የቀረሁት… ወይስ የበረገገ በሬ ቤቱ ውስጥ ገብቶ ነበር…ምን ሆኖ ነው ቤቱ እንዲ ምስቅልቅል የወጣው?
ለማንኛውም ቀውጢ ጎመን ሰርቼልሃለው እግርህን ሰቅለህ ብላ… ያው በዚህ ሳምንት መጨረሻ ደሞዝ ስለምትቀበል የጎመን ምንቸት ውጣ፣ የቅንጥብጣቢ ምንቸት ግባ እንላለን… ቂቂቂ…

ይድረስ ለጋቢሻ፡
እረ ትረባ! አልቻልኩሽም… እኔ እምልሽ፣ ይሄ ይድረስ ለናሆም፣ ይድረስ ለጋቢ የምንባባለው ነገር ግን አይገባኝም… ሜሟችንን ሁል ጊዜ ኮሞዲኖው ላይ አይደል እንዴ የምናስቀምጠው፣ ለዛውም በር እንደሌለው ቤት ንፋስ እንዳይወስደው በሚል የሻማ ማስቀመጫውን እንጭንበታልን… ታዲያ የምን "ይድረስ" ነው… ከአሁን በኋላ እንደውም "ይቀመጥ ለጋቢ" ነው የምለው… ካካካካ…
ደሞ ምናባሽ ሆነሽ ነው በጃኬቴ የምትተርቢኝ… አንድ ጃኬት መግዛት አቅቶኝ መሰለሽ እንዴ? አንድም ጃኬቷ ልዩ የክረምት ትዝታ ስላላት ነው… ሌላም በክረምት አይዘነጥም ብዬ እንጂ… በክረምት አንድ አጥንት ምናምን የሚባለውን አባባል በክረምት አንድ ጃኬት በሚል ቀይሬው ነው… ካካካካ…
ለማንኛውም የሰራሽው ምግብ ተመችቶኛል… ገና ድስቱን ከፍቼ ጎመኑን ሳየው ጎመን በስጋ መስሎኝ ሰፍ ብዬ ነበር፤ ምን ዋጋ አለው… ጎመን በሚጥምጣዬን በልቼ ተኝሁ እንጂ… ለነገሩ ለብርዱ ጠቅሞኛል ሚጥሚጣው ሆዴን ሞቅ አድርጎልኛል… ያንቺን ትረባ ያህል ባያቃጥልም…
ጋቢቾ ልብሶቼ እንዳሉ ቆሽሸዋል… ኪሶቹ ውስጥ ብር ካገኘሽ አስቀምጪልኝ… ነገ ደግሞ ለይት ያለ ነገር ስሪልኝ… ቆስጣ ምናምን… ካካካካ…
ቻው በይ! ናሆም

ይቀመጥ ለናሆሜ (ቂቂቂ…)
አንተ ወሬኛ… ቅንጥብጣቢ መግዛት አቅቶህ ጃኬት ለመግዛት አንሼ መሰለሽ… ምና ምን… ጲጲጲ… ጲጲጲ… ትላልህ አይደል… "ፊሽካ!" አለ ባዮሎጂ ቲቸር…
ኡኡቴ… ደግሞ ኪሶቼ ውስጥ ብር ካገኝሽ ምና ምን ትላለህ እንዴ? ልብስህን ሳጥብ እንኳን ብር ላገኝ ከሚስጥር ኪስህ ውስጥ ወጥተው የማያውቁት ሳንቲሞች ዝገው ኪስህን በውስጥ በኩል ቡኒ አድርገውታል… እንደውም ሳንቲሞቹን ሰብስቤ በኪሎ ልሸጣቸው ነው… ዘንድሮ እኮ ብረት ወርቅ ሆኗል... ቂቂቂቂ…
ልብስ አጠባ ድሮ ቀረ እቴ… ድሮ ድሮ የሚለበሰው ሱሪ እራሱ ባለ ብዙ ኪስ ነው… ትዝ ይልሃል አንድ ሰሞን ፋሽን ሆኖ የነበረው ካኪ ሱሪ ከላይ እስከታች ኪስ በኪስ የሆነ… ከጉልበት በታች ሁላ ኪስ አለው… አስበው እስቲ… ቁጢጥ እያልክ ሁላ ኪስህ ውስጥ ትገባ ነበር… እና ያኔ ልብስ ስናጥብ ከአንዱ ኪስ ሃምሳ፣ ካአንዱ ኪስ አስር፣ ከሌላው አምስት፣ ከጉልበት በታች ካሉት ኪሶች ደግሞ የአገር አንድ ብሮች ነበር የምናገኘው… አንዳንዴ እንደውም ከልብስ ማስጣቱ ይልቅ የረጠቡ ብሮችን ማስጣቱ ያደክመን ነበር… ቂቂቂቂ… የዘንድሮ ሰው እኮ አይምሮው ኪሱ ውስጥ ያለ ነው የሚመስለው… ብሩን ኪሱ ውስጥ ከመርሳት ስሙን መርሳት ይቀለዋል… ቂቂቂቂ…
በል ለማንኛውም፣ ቲ-ሸርቶቹ ደርቀዋል፣ ሸሚዞቹን አልጋው ላይ ዘርሬያቸዋለው፣ ሱሪዎቹን መዘፍዘፊያው ውስጥ አድርጌያቸዋለው… ለለውጥ ብዬ ክሽን ያለች ሽሮና ቲማቲም ቆርጬልሃለው፤ ለቲማቲሙ ጨው፣ ሎሚ ምናምን እራስህ ቀላቅለህ ብላ…
ጉድ ናይት!

ለ ጋቢያንስ፡
ይቀመጥ ለናሆምን ወድጄዋለው… አንቺ ተቀማጭ! እኔ እኮ ደስ የምትለኝ እቺ ፍጥነትሽ ናት… አሁን እኔን የመሰለ ቦስ ባይኖርሽ እንዲ ባናና ትሆኚ ነበር? ያኔ ገና እኔ ጋር ስትቀጠሪ እኮ ነፈዝ ነገር ነበርሽ… እራሴው አሰልጥኜ እራሴው ላይ ሙድ ይያዝብኝ… ወይኔ ቶክቻው! ለማንኛውም ሞጥሟጣ ሆነሻል… ቆይ ግን… ስራውን ተውሽው እንዴ? የሰሞኑ ሜሞዎችሽ እየረዘሙብኝ ነው… ቁጭ ብለሽ ስትፅፊ ነው እንዴ የምትውይው? እኔ እምፈራው በቅርብ ቀን፣ በአንደኛው ሜሞሽ ላይ… "ይቅርታ ናሆሜ ከዛሬ ጀምሮ ስራ አቁሚያለው፤ ምክንያቱም… ለትዕዛዝ መቀባበያነት የጀመርናት ሜሞ በውስጤ የተደበቀውን እምቅ፣ የፀሃፊነት ችሎታ እንዳገኘው ስላደረገችኝ ከአሁን በኋላ ተመላላሽ ጋዜጠኛ ሆኛለው…" እንዳትይኝ ነው… ካካካካ…
በነገራችን ላይ ቤት ስገባ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ሽሮዋን ሳላሞቃት ነው የበላዋት…  እንደውም የላስኳት ነው የሚባለው… ማማሰያውን ከድስቱ ውስጥ ሳታወጪው ሄደሽ የሽሮ ጀላቲ ሆኖ ነው የጠበቀኝ… ካካካካ…




No comments:

Post a Comment