Tuesday, August 13, 2013

የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር!


"የዘንድሮ ክረምት እንዴት ነው? ብርዱ እንዴት ይዞሃል?" ብለው ሲጠይቁኝ…

የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር ብዬ እመልሳለው… የምር ግን ከዘንድሮው ክረምት የአምናው ይሞቅ ነበር… ብዬ እላለው… ስለ አምናው ክረምት ዘንድሮ አስባለው…

ያኔ… አምና… አብረን ባንሆን እንኳን… በስልክ ደውዬ "ፍቅር… ብርዱን አልቻልኩትም ልሞትብሸ ነው…" ስላት… "እኔን የኔ ጌታ… እኔ ልሙትልህ… እኔ እያለውማ አንተን አይበርድህም… አሁኑኑ መጥቼ እቅፍ አደርግሃለው…" ትለኝ ነበር… እናም ወዲያው… ይሞቀኝ ነበረ፡፡
የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

ሌላም… በአምናው ክረምት… ሽምብራ ዱቤ ገዝተን እንገባለን… ዱቤያችንን አስቆልተን፣ ለስላሳ እናስገዛና ቆሏችንን እየቆረጠምን በለስላሳው እናወራርዳለን… ከዛም… ብርድልብሳችን ውስጥ እንገባና ይሄን ፊልም እንከሰክሳለን… ፊልማችንን እያየን በመሃል፣ በመሃል… "የኔ ጌታ… ው-ድ-ድ-ድ-ድ… አደርግሃለው"  ብላ ከንፈሬን ስትስመኝ… ይሞቀኝ ነበረ፡፡
የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

የሷ አሳሳም ልዩ ነው… ከከንፈሯ እምዿ! የሚል ድምፅ አይወጣም… በስሱ ከንፈሯ ከንፈሬ ላይ እንደ ጭቃ ማግኔት ጥብቅ ትልብኛለች… ከንፈሯ አካሌን፣ ልቤንና መንፈሴን የሚያሞቅ የፍቅር ነበልባል ከውስጡ የሚተፋ ነው… የምራቋን ሙቀት አሁንም ድረስ ሳስበው እንደ አንዳች ነገር ይነዝረኛል… በትዝታ ዛሬም ይሞቀኛል፡፡
ብቻ… የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

እንደለመድኩት ደረቴን ገልብጬ ስሄድ ስታየኝ… "ፍቅርዬ አይበርድህም… ቆይ ና… አንዴ…" ትለኝና ሸሚዜን ቆልፋ ጃኬቴን ትዘጋልኛለች… ያኔ ከልብሱ ሙቀት ይልቅ፣ ሀሳቧ ይሞቀኛል… ቃላቶችው፣ ትህትናዋ፣ ቅላፄዋ… ሁለመናዬን ይነዝረኛል… የፍቅሯ ብርሃን በኔ ፊት ላይ ያበራል… እናም በቃ… ይሞቀኛል፡፡
የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

ደግሞም… ዝናቡ ጋብ ባለ ወቅት… "ወክ እናድርግ የኔ ማር" ትለኝና የተጠበሰ በቆሎ ታስገዛኛለች… ከዛም… በቆሎውን እየበላን ረጅም መንገድ ዎክ እናደርጋለን… እኔ እየፈለፈልኩ እበላለው… እሷ በጥርሷ ትግጣለች… ደግሞ… ሞልቃቃ ነገር ናት… ሙልቅቅናዋ ግን አይደብርም… የህፃን ልጅ አይነት ሙልቅቅና ነው ያለት… የሚጣፍጥ አይነት… ታዲያ በቆሎዋን እየጋጠች በመሃል፣ በመሃል…  "ጥርሴ ላይ ጥቁሩ ነገር አለ?" ትለኛለች… ከኪሴ እስቴኪኒ አውጥቼ የበቆሎውን ጥቁር ቅርፊት ከጥርሷ ላይ አወጣላትና… "አሁን ምንም የለብሽም የኔ ቆንጆ!" ስላት… በአንድ እጇ ጭንቅላቴን ወደ እርሷ ታዞረውና ከንፈሬ ላይ ግጥም ትላለች… ከዛም… "አመሰግናለው አባቴ… አፈቅርሃለው…" ትለኝለች… ያን ውብ፣ ጮራ ፈግታዋን ታጠግበኛለች… ኡፍፍፍፍ… ምን ልበላችሁ… ያኔ… አይሆኑ እሆናለው… እናም… ዝም ብሎ… ውስጤን ይሞቀኛል፡፡
የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

ደግሞ አንዳንዴ… ጋብዬን ተጠቅልዬ ሶፋዬ ላይ ቁጭ ብዬ፣ እግሬን ጠረጴዛ ላይ ሰቅዬ መፅሃፍ እያነበብኩ… ትመጣና እግሬ ላይ ቁጭ ትልብኛለች… ከዛም… "የኔ ጌታ… ጋቢህ ውስጥ አስገባና እቀፈኝ?" ትለኛለች… እኔም… እንዳለችው አደርጋለው… ወዲያው… "የምታነበውን መፅሃፍ አንብብልኝ?" ትለኛለች… እኔም አነብላታለው…

"ፀጥታን የሚፈራ አካባቢውን የማያውቅ ጨቅላ አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው… ፀጥ ካላሉ የቅጠላት ሿሿቴ፣ የወንዞች ፏፏቴ አይሰማም… ፀጥታ የገሃዱ አለም ቁልፍ መፍቻ ነው… በዚህ ሁካታ ግር ግርና ረብሻ በበዛበት አለም ምናለ ፀጥታም እንደዘፈን በካሴት ታትሞ ቢሸጥ ያሰኛል…" ይሄን ጊዜ… በአይኗ እየተለማመጠች፣ ጠቋሚ ጣትዋን ከንፈሮቼ ላይ ታሳርፍና… "ሽሽሽሽ… የኔ ፍቅር… አሁን ዝም ብለህ እቀፈኝ…" ትለኝና አንገቴ ውስጥ ፊቷን ቅብር ታደርጋለች… ይሄኔ… ከላይ እስከታች ይወረኛል… ይነዝረኛል… ባጭሩ… ይሞቀኛል፡፡
የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

ከሁሉ ከሁሉ እሷም፣ እኔም የምንወደው… ቤት ውስጥ ሆነን ዝናብ ሲዘንብ ነው… እንደለመድነው ሽምብራ ዱቤያችንን አስቆልተን፣ ፊልማችንን እየከሰከስን ዝናብ ከዘነበ… እኩል እንተያያለን… ወዲያው እቅፍ ታደርገኝና ከንፈሬ ላይ ግጥም ትላለች… እኔም ከንፈሯን እጎርስና… ሙቁ ምራቅዋን… ምጥጥ አደርገዋለው… ውስጤ ወዲያው ይሞቃል… ደም ስሮቼ በደም ይሞላሉ… ከዛም ከንፌሬን ከከንፈሯ ለአፍታ አነሳና… አንገቷን… ደረትዋን… እስማለው… ልብሶቻችን ይወልቃሉ… ከውጪ ዝናቡ ጣሪያው ላይ ዷ!ዷ!ዷ!ዷ! ከውስጥ እኔና እሷ እሳት በሆኑት አካላቶቻችን አለፍው ልቦቻችን ድው!ድው!ድው! ይላሉ… ታዲያ ይሄን ጊዜ… በቃ… ምን ልበላችሁ… እጅግ በጣም… ያልበኛል… ይነዝረኛል… ያንቀጠቅጠኛል… ይሞቀኛል…

የአምናው ክረምት ልዩ ነበር… የአምናው ክረምት ይሞቅ ነበር…

No comments:

Post a Comment