Thursday, June 13, 2013

የወንደ-ላጤውና የሰራተኛዋ ‘ሜሞ’

ይህች ፅሁፍ በአንድ ወቅት በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት አብሮኝ ይሰራ ስለነበር ናሆም ስለሚባል ወንደ-ላጤና ስለሰራተኛው ገበያነሽ (ጋቢ) የምንጨዋወትባት አሪፍ ወግ ናት፤ ዘና በሉ… 


ቅድመ-ወግ
ናሆም፡ እድሜው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ምርጥ ልጅ ነው፤ በቃ ሙድ የገባው፣ የአራዳ ልጅ የምትሉት አይነት… ተቆራርጣ የምትደርሰው የወር ደሞዙ ባለ አራት ዲጅት ልትሆን ትንሽ የቀራት… በዛችው ደሞዙ ቤት ተከራይቶ ተመላላሽ ሰራተኛ ቀጥሮ የሚኖር… ‘እቺን ደሞዝ በምን አይነት ብልሃት ነው የምታብቃቃት?' ሲባል ‘በአስማት' የሚል፣ ኑሮን ቀለል አድርጎ የሚኖር ምርጥ ልጅ…



ገበያነሽ፡ እንደ ናሆም ሁሉ ሙድ የገባት ስትሆን፤ ጎበዝ፣ የ10ኛ ክፍል የማታ ተማሪ ናት፡፡ ናሆምን ጨምሮ ወደ አምስት የሚደርሱ ወንደ-ላጤዎች ጋር በመስራት ራሷን የምታስተዳድር ሁለገብ ፍሪ-ላንሰርም ነች… ጋቢ በጠዋት ተነስታ የሁለት ወንደ-ላጤ ቤቶችን ስራ አቀለጣጥፋ ጨርሳ ናሆም ቤት ወደ አራት ሰዓት ገደማ ትደርሳለች፡፡ ናሆም ደግሞ ከእሁድ በስተቀር ከሁለት ሰዓት በፊት ከቤቱ ስለሚወጣ ከጋቢ ጋር የሚገናኙት በ‘ሜሞ' (አጭር የፅሁፍ ማስታወሻ) ነው፡፡ 



የናሆምና የጋቢ ሜሞዎች ትዕዛዝና መረጃ ከመለዋወጫነት በዘለለ ስለ ብዙ ጉዳዮች በስፋት የሚያወጉበት፣ የሚቀላለዱበት፣ የሚበሻሸቁበት፣ የሚደናነቁበት… ወዘተ ነው፡፡ እነዚህ ብጫቂ ወረቀቶች በሁለቱ መካከል ያለውን ንፁህ እህታዊና ወንድማዊ ግንኙነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ሲሆኑ፤ ስነፅሁፍዊ ይዘታቸውም የሚናቅ አይደለም፡፡ ሜሞዎቹን ሲያሻቸው በእንግሊዘኛ፣ አልያም በአራዳ ቋንቋ ስለሚፅፏቸው አንዳንድ ጊዜ ከፅሁፍ ይልቅ ወሬ ቢመስሉም ስርዓተ-ነጥብን ሳይቀር በአግባቡ ያካተቱና አንዱ ከሌላው በቀርፅም በይዘትም የማይገናኙ ናቸው፡፡ አስቂኝ ወሬ ወይም ተረባ በመሃከል ካለ የሳቅ ድምፃቸውን ሁሉ ሳያስቀሩ ያስገባሉ፤ ናሆም- ካካካካ… ጋቢ- ቂቂቂቂ… እያለች፡፡ 



ደስ ብሏቸው ይፃፃፋሉ… አንዱ የሌላውን ለማንበብ ይቸኩላል… እንኳን እነሱ እኛም ሳንቀር የቢሮ ስራችንን የምንጀምረው በእኒህ አዝናኝ ፅሁፎች ነበር፡፡ እንደውም፣ እነዚህን ፅሁፎች ማሳተም አለብህ እያልኩ እወተውተው ነበር፡፡ ወደፊት ‘የወንደ-ላጤውና የሰራተኛዋ ‘ሜሞ'' በሚል ርዕስ እንደሚያሳትማቸው ከልብ እየተመኘሁ ከሜሞዎቹ በጥቂቱ እነሆ… ኤን ቢ፡ ፅሁፎቹ እንደወረዱ የቀረቡ ናቸው… 




ቀን፡ 10/4/2001ዓ.ም
ይድረስ፡ ለገበያነሽ (Arrive: for Marketing) ካካካካ…

ጋቢዬ፣ ዛሬ ጓደኛዬን እቤት ምሳ ስለጋበዝኩት ቤቷን ሰንደል ጨስ ጨስ አድርጊባትና አሪፍ ምሳ አዘጋጂልን፤ አራት ድንችና ሶስት ራስ ሽንኩርት አለ በሱ አሪፍ፣ ጣት የሚያስቆረጥም ጥብስ ፍርፍር ስሪልን… ካካካካ… ለማንኛውም ለእንጀራና ሌላ መግዛት የምትፈልጊው ነገር ካለ ብዬ ኮመዲኖው ላይ ሃያ አምስት ብር አስቀምጬልሻለሁ፡፡ መልስ ካለ እዛው አስቀምጪልኝ፤ በተረፈ መልካም ፈተና፡፡
ናሆም፣ ከማይነበብ ፊርማ ጋር


ቀን 10/4/2001ዓ.ም
ይድረስ፡ ለናሆም…
ኡኡቴ! አንተን ብሎ ምሳ ጋባዥ…ቂቂቂቂ… ለማንኛውም አራቱ ድንቾች ትንንሽ ስለሆኑ ግማሽ ኪሎ ድንች ገዝቻለው ከዛ ውጪ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና እንጀራ ገዝቼ የተረፈውን 1ብር ከ50 ኮመዲኖው ላይ ላስቀምጠው ብዬ እናቴ ለታላቅ አይመለስም ትል የነበረው ትዝ ሲለኝ ይዤው ሄጃለሁ… ቂቂቂቂ… በተረፈ በአራት ድንችና በሶስት ሽንኩርት የሚሰራ ጥብስ ፍርፍር ስለማልችልበት አልጫ ድንች ወጥና… ጥብስ… አምሮህ እንዳይቀር ብዬ… ጥብስ ቅጠል ያለው ፍርፍር ሰርቼልሃለው... ቂቂቂቂ… ያው ወጡ ከቀዘቀዘባችሁ አሙቃችሁ ብሉ… ዘይት ስለጨረስኩ ለነገ ብር አስቀምጥልኝ፡፡
ቻው፣ ገበያነሽ

ቀን 11/4/2001ዓ.ም
ይድረስ ለጋቢያንስ

ኸረ ጋቢያችን! ጨዋታ ጨምረሽ የለ እንዴ! የትላንቱ ተረብሽን አልቻልኩትም፤ ልቤ እስኪፈርስ ነው ያሳቅሽኝ… ወጡም በጣም አሪፍ ነበር፤ እኔ እምልሽ፣ ቅቤ ደግሞ ከየት አምጥተሸ ነው? ከሼባው ወንደላጤ ቤት ቋ አድርገሽ እንዳይሆን? ቤተሰብ አደረግሽን እኮ…ካካካካ… በነገራችን ላይ፣ ቤት ውስጥ ምንም አስቤዛ በሌለበት ምግብ የምትፈጥሪው ነገር ብዙም አይገባኝም፤ ለነገሩ እንዲገባኝም አልፈልግም፣ በአስማትም ይሁን በፀሎት ዋናው ቁም ነገር የሚበላ ነገር መኖሩ ነው፡፡ የትም ፍጪው… (Where crash bring my ash) አይደል የሚባለው…ካካካካ… መቼም ባንቺ መላ ባይሆን ኖሮ ይቺ ደሞዜ ሁለት ሳምንት እንኳን በቅጡ እንደማታዘልቀኝ ታውቂዋለሽ፡፡ ለማንኛውም በድጋሚ አመሰግናለሁ፣ የኔ አስማተኛ… ካካካካ… የዘይት ብር ኮመዲኖው ላይ አስቀምጬልሻለሁ፡፡
ፒስ በይ- ናሆም

ቀን 11/4/2001ዓ.ም
ለ፡ እርሶ

አንተ ነገረኛ! እንደው ምን ይሻልሃል… ለማንኛውም ወጡ ቅቤ አለው ምናምን ያልከውን ወሬ ቅቤ ያለው እስኪመስል ይጣፍጣል ለማለት ከሆነ ከአንገቴ ሰበር፣ ከወገቤ ጎንበስ ብዬ ተቀብዬዋለሁ …ይህቺ የፈጠርካት ታሪክ ግን ብዙም አልተመቸችኝም፤ እኔኮ ፕሮፌሽናል ነኝ! እንዴት ከአንዱ ቤት ወስጄ ለሌላው እሰራለሁ፣ ከአስራ ሁለቱ የስነምግባር መርሆች መካከል አንዱ ታማኝነት እንደሆነ ረሳኸው? ቂቂቂቂ… ለማንኛውም ሀሳብህን በመርህ ደረጃ ተቀብዬዋለው ባይሆን ሚስጥሩን ልንገርህ፣ አንዳንድ ጊዜ ምንም አስቤዛ ሳይኖር ምግብ የምሰራልህ ከራሴ ቤት እያመጣሁ ነው፤ ምክንያቱም ስለምታሳዝነኝና ስለምታዝናናኝ… በዛ ላይ ልክ እንደ ወንድሜ ስለማይህ ነው፡፡ በል አሪፍ ምስር ወጥ ሰርቼልሃለው አሙቀህ ብላ… ያጠብኳቸውን ልብሶች አልጋው ላይ አጣጥፌ አስቀምጬልሃለው… ብር ስላልነበረኝ እንጀራ አልገዛውልህም፡፡
እደር፣ ጋቢ

ይህች ቀጣይዋን ሜሞ ናሆም በጋቢ የምግብ ዘይት አጠቃቀም በጣም ቅር በመሰኘቱ የፃፋት ናት፡፡ ለአንድ ወር የሚገዛትን አንድ ሊትር ከግማሽ ዘይት እሷ በሁለት ሳምንት ጭጭ ስለምታደርጋት እንዲህ ሲል ፅፎላታል…
ጋቢ ከተጫዋችነቷና ከምስኪንነቷ ባሻገር የዋህ ቢጢ ናት፤ የነገሯትን ሁሉ አምና የምትቀበል… ከቅርበታቸው የተነሳ ስለ ዘይቱ የፃፈውን ሜሞ አንብባ ‘በግልፅ ዘይቴን አትጨርሺ አትልም…' ብላ ኩም የምታደርገው መስሎት ነበር፤ ነገር ግን ልጅቷ ጋቢ ናት… አምና ተቀብላዋለች፡፡

ለተከበሩ…
ጋቢሽካ፣ የትላንቱ ምስር ወጥ በጣም አሪፍ ነበር፤ ነገር ግን ቅባት በጣም ስለበዛበት ነው መሰለኝ ጨጋራዬ ሲነድ ነው የዋለው፡፡ ሌላ ነገር ይሆናል እንዳልል ውጪ አልመገብም፤ ባለፈው ሳምንትም የሰራሽልኝን ድንች ወጥ ቅባቱን እየፈራሁ በልቼው በቃ ምን አለፋሽ፣ አንቆራጠጠኝ… ስቃጠል ነው የዋልኩት… ለማንኛውም ካሁን በኋላ የምትሰሪልኝ ወጦች ላይ ዘይት በጣም አትጠቀሚ፡፡ በዛ ላይ ደግሞ የልብ በሽታ እንዳለብኝ ነገሬሻለሁ አይደል? በዘር ነው መሰለኝ እኛ ቤት ሁሉም የልብ በሽታ ታማሚ ስለሆነ ለዘይት የሚደረገው ጥንቃቄ ለየት ያለ ነው፡፡ ሰሞኑን ደረጃ ስወጣ ሁሉ ልቤ ድው ድው እያለች ነው፡፡ እናም… ባጭሩ… እንዳልጭርብሽ ለማለት ያህል ነው! ካካካካ… በነገራችን ላይ ሶስቱንም የፊዚክስ ጥያቄዎች በትክክል ሰርተሻቸዋል፤ የሆነ የተሳሳትሽው ስቴፕ ነበረ እሱን ምልክት አድርጌበታለሁ በደንብ እይው፡፡
ቻው! ናሆም

ለ፡እርሶነቶ…
ናሆሜ ለምንድን ነው እስከ ዛሬ ድረስ ያልነገርከኝ! እኔ እኮ ላንተ ማሰቤ ነበር፤ ጣፍጦህ እንድትበላ ብዬ ነው ቅባት የማበዛው፡፡ ለማንኛውም ከአሁን በኋላ አስተካክላለሁ፡፡ አይዞህ! አትጭርም… ቂቂቂቂ.. ለልብ በሽታህ ደግሞ ጠዋት ጠዋት ትንሽ ዱብ ዱብ በልባት… ሰሞኑን ብር ሳታስቀምጥልኝ እየወጣህ ስለሆነ ምንም ነገር አልገዛሁልህም፤ ሽሮም የመጨረሻዋን ዱቄት አራግፌ ነው የሰራሁልህ… ለነገ ምን እንደምሰራልህ አሳውቀኝ…
ደህና እደር፣ ጋቢ

በነገራችን ላይ ምንም እንኳን በመሃከላቸው ጥሩ ቅርርብና ግልፅነት ቢኖርም የዘይት ቅነሳውን እውነተኛ ምክንያት ለምን እንዳልነገራት ናሆምን ስጠይቀው እንዲህ ነበር ያለኝ... ‘ባክህ! እሷ ምስኪን ስለሆነች እንደዛ ካልኳት ዘይት ከራሷ ቤት እያመጣች ልትሰራልኝ ትችላለች፤ ያን ደግሞ እኔ አልፈልኩም…’ የናሆምና የጋቢ መተሳሰብና መዋደድ በጣም የሚያስቀና፣ የሚያዝናና… ብዙ ብዙ የሚባልለት ነው…
እስኪ በመጨረሻ ጋቢ ከላይ ለፃፈችው ሜሞ ናሆም የፃፈላትን መልስ አስነብቤያችሁ ወጌን ላብቃ…

ለ፡ ጋቢሻ...
ጋቢቾ! ፒስ ነው አይደል? ጠፋህ ነው ያልሽው? አንቺ ምን አለብሽ… አምስት ደሞዝ እየበላሽ… ካካካካ… ለማንኛውም የጠፋሁት… ያው እንደምታውቂው አራተኛው ሳምንት አይደል፤ እናም ብር ኔፕ ሆኜ ነው… ለአስቤዛ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስሌለኝ ለእራት የሆነች ነገር ይዤ እገባለሁ፡፡ ባይሆን ‘ምን ሰርቼ ልሂድ?' ላልሽው፣ ምንም ሳትሰሪ ከምትመለሺ ፑሻፕ ሰርተሽ ሂጂ… የቻልሽውን ያህል… ካካካካ… ሰራሁልሽ… ካካካካ...
ናሆም፣ ቻው!
 

የድብርታሙ ሰው ዲያሪ


ቀን፡ ግንቦት 12 13 12… ኤጭ! 


ዛሬ ቀን ስንት ነው? እኔ እንጃ! ለነገሩ ስንትስ ቢሆን ምን አገባኝ፣ ምን ልዩነት ያመጣል… የቀን ማስታወስ ችግሬ እንዳለ ሆኖ ሃያ ምናምን አመት የኖርኩ ይመስለኛል፡፡ እድሜዬን በሙሉ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሐምሌ… እያልኩ ስቆጥር፤ ህይወቴን በሙሉ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ እሮብን… ስደጋግም ኖሬያለሁ ግን ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ቢያንስ የቀናቱ ስም እንኳን አልተቀየረም፣ የወራቱ ስም እንኳን አልተቀየረም፤ ሲደብር! ለነገሩ ህይወት ማለት አሰልቺ የሰባት ቀናት ሳምንት እንዲሁም ተደጋጋሚ የአስራ ሁለት ወራት አመት ነች (ኦ! ለካስ አስራ ሶስት ወራት ናቸው ያሉን፣ ድንቄም!)


…ጠዋት፣ ከሰዓት፣ ማታ፣ ቀን፣ ሌሊት… እስቲ አሁን የህይወት አጓጊነትዋና ጣዕሟ የቱ ጋር ነው? ኑሯችን በነዚህ ደባሪና አሰልቺ አዙሪት ውስጥ የተዘፈቀች አይደለችምን? ለምድን ነው አራሳችንን የምናታልለው፣ ለምንድን ነው "እያንዳንዷ ቀን አዲስ ናት" እያለን የምንፎጋገረው? እውን እያንዳንዱ ቀን አዲስ ነው? ነው!? ከሆነስ ምኑ ጋር ነው አዲስነቱ? በቀን ሁለትና ሶስት ጊዜ መብላት፣ መውጣት፣ መግባት፣ መተኛት፣ መነሳት፣ እንደገና መተኛት፣ እንደገና መነሳት… ኡፍፍፍ.. ደባሪ!


ቀን፡ ግንቦት 13 14… አጭ! በቃ በንጋታው
ቅዳሜ/የእረፍት ቀን… ቀኑ እንደተለመደው ነው… ደባሪ! አልጋዬ ውስጥ ስንከባለል ቆይቼ ረፋድ ላይ በግድ ተነሳሁ፤ የምግብ ፍላጎቴ ጠፍቷል ነገር ግን እንደምንም ብዬ ቤት ውስጥ የነበረ ምግብ በግድ ቀማመስኩ፡፡ ቀጥሎም ምን ማድረግ እንዳለብኝ  ወይም የት መሄድ እንዳለብኝ ማሰላሰል፣ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡ 


ጓደኞቼ ጋር ልሂድ፣ ፊልም ልይ፣ ወይስ እዚው ቁጭ ብዬ አዲስ የገዛኋትን መፅሃፍ ላንብብ… አስራ ሁለት ልብ ሆንኩ፤ በመጨረሻም ረጅም ደቂቃዎችን ከፈጀ ውስጣዊ-ግለ-ጭውውት (Internal Monologue) በኋላ፣ አውጥቼ አውርጄ ማለቴ ነው ቤቴ ቁጭ ብዬ መፅሃፌን ለማንበብ ወሰንኩ፡፡ በነገራችን ላይ ሰው ማግኘት ሲደብረኝ ወይም ወደ ውጪ መውጣት ሲያስጠላኝ ሁሌም የማደርገው ይህንን ነው፤ ማንበብ፡፡ መፅሃፍትን የማነበው ህይወቴን ለመርሳት ነው፤ እራሴን ለመርሳት፤ ‘ስለ እውነተኛው’ አለም (ስለ ‘ገሃዱ አለም’) ላለማሰብ፡፡


የፍልስፍና መፅሃፍቶችን ማንበብ የምመርጠውም ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ መፅሃፍት በአብዛኛው የ‘ገሃዱ አለም’ ቀጥተኛ ነፀብራቆች አይደሉምና፡፡ እኔ ለምኖረው አይነት ህይወትና ለጥያቄዎቼ መልስ የሚሰጡኝ እንዲህ ያሉ መፃህፍት ብቻ ናቸው፡፡ ብዙ የPhilosophical Skepticism (ነቀፌታዊ ወይም ጥርጣሬያዊ ፍልስፍና) መፃህፍትን አንብብዬለው፡፡


በውሳኔዬ መሰረት መፅሃፌን ካስቀመጥኩበት መደርደሪያ ውስጥ አውጥቼ ለማንበብ በመስኮቴ ፊት ለፊት በተቀመጠው ፎቴ ላይ ተመቻችቼ ተቀመጥኩ(ዘፍ አልኩ)፡፡ ወዲያውም አንዴ ከተቀመጥኩ መነሳት ያለመውደድ ስንፍናዬ ትዝ አለኝና በቅርብ የሚያስፈልጉኝን እቃዎች በእጄ እርቀት እንዲሆኑ አድርጌ አቀራረብኩ፤ ሲጋራ፣ የሲጋራ መለኮሻ፣ መተርኮሻ፣ አንድ ሁለት ቢራዎች፣ የሲዲ ማጫወቻ የርቀት መቆጣጠሪያ፣ ‘ቢራ መክፈቻ’ (ለስላሳ ስለማልወድ እናንተ ‘ለስላሳ መክፈቻ’ የምትሉትን እኔ ቢራ መክፈቻ ነው የምለው)


ሶፋዬ ላይ ጀርባዬን አደላድዬ ቢራዬን ከፍቼ ጎርጎጭ ካደረኩ በኋላ ሲጋራዬን ለኮስኩ፣ ጭሱን ወደ ውስጥ በስስት ምጥጥ አድርጌ በአፍንጫዬ በኩል ወደ ውጭ በማስወጣት ጠባቧን ክፍሌን በጭስ ሞላኋት፡፡ አሁን ለማንበብ ዝግጁ ነበርኩ፤ ‘ያልተሄደበት መንገድ’ ትላለች የመፅሃፏ ርዕስ፤ የመፅሃፉ የውጭ ሽፋን ላይ ለአፍታ አፈጠጥኩ ሁለት ቅያሶች ያሉት መንገድ ይታያል፣ በዙ ሰዎች በአንደኛው መንገድ ላይ ተሰልፈው ይታያሉ፤ በሌላኛው መንገድ መጀመሪያ ላይ ደግሞ እነዚያን የተሰለፉትን ሰዎች ቆሞ የሚያይ ሰው ይታያል፡፡


ወደ ውስጥ ገፅ ዘለቅኩ፣ ገፅ-3፣ መታሰቢያ፣ “ይህ መፅሃፍ ላንተ ነው!” “ለኔ!?” አልኩ ሳላስበው፤ ፅሁፉን እኔው እራሴው ያነበብኩት አልመሰለኝም ይልቁንም ጎርነን ያለ ድምፅ ያለው ሰው ያነበበልኝ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ …የመፅሃፉን የመጀመሪያ ምዕራፍ ማንበብ ጀመርኩ፤ የቃላቶቹ ጥፍጠትና ጥንካሬ ደስ ይላል፤ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመግባቴ በፊት ቢራዬን ጎንጨት አልኩኝ፤ ንባቤ ቀጥሏል፣ አንድ አንቀፅ ላይ ግን ቀልቤ አርፏል ደጋግሜ አነበብኩት ወደ ቀጣዩ አንቀፅ ማለፍ አልቻልኩም፡፡
“… ህይወት ሙከራ ናት፤ አዎ! የሙከራ ፈተና! ህይወት የእውነት ብትሆን ኖሮ የት መሄድ፣ መቼ፣ ምን፣ ለምን፣ ማድረግ እንዳለብህ ይነገርህ ነበር…” እውነትም! አልኩ ውስጤ ላለው የ‘ገሃዱ አለም’ አውነተኝነት ጥርጣሬና ነቀፌታ ምላሽ ያገኘው መሰለኝ፤ ደስ አለኝ! ለሰው ልጅ ያሰበው ወይም የተናገረው ነገር ልክ ሆኖ እንደማየት የሚያስደስተው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ አላልኩህም/ሽም! ለማለት፡፡ በተመሳሳይ ስሜት እኔንም በጣም ደስ አለኝ፡፡


ንባቤን ቀጠልኩ “…ህይወት በተከታታይ ፈተናዎች የተሞላች ናት፣ ተፈትነህ ትወድቃለህ፣ እንደገና ታጠናና ታልፋለህ፣ ከውድቀትህ ትነሳለህ፣ ደረጃህ ከፍ እያለ በመጣ ቁጥር በሌላ ፈተና ትወድቃለህ፣ አሁንም ከውድቀትህ ትማርና አሻሽለህ ታልፋለህ… ይህ የማይቀር መንገድ ነው፤ የማይቀር የህይወት ጉዞ፡፡ ታዲያ የዚህ ጉዞ አጓጊነትና ጣፋጭነት የሚወሰነው በምትመርጠው መንገድ ነው፤ የትኛውን መንገድ ነው የመረጥከው? ብዙሃኑ የሄደበትና የተሰለፈበትን ወይስ ሌላው ልብ ያላለውን፣ ያልተሄደበትን መንገድ? የህይወት ጣዕሟና አጓጊነቷ እዚህ ላይ ነው እያንዳንዱ መንገድ የራሱ የሆነ መልስና ውጤት አለው፡፡ ተነሳ! ውጣ! ሂድ! ህይወትህን ሞክራት! ፈተናውን ስትሞክር ለመሳትፍ ሳይሆን ለማለፍ፣ ለመብለጥ ሳይሆን፣ ለመላቅ ይሁን፤ ያልተሄደበትን መንገድ ሞክር! ምናልባትም ታዕምር ታገኝ ይሆናል፣ ማን ያውቃል ታሪክ ትሰራ ይሆናል… ማን ያውቃል! ለነገሩስ ህይወት ሙከራ አይደለችምን?


ጀምበር እያዘቀዘቀች ነው፤ አይኖቼን ከመፅሃፉ ላይ መንቀል አቃተኝ፤ ለአፍታ እንኳን፤ ቀልቤን ገዝቶታል፣ ውስጤ ገብቷል፣ ፊደል በፊደል፣ ቃል በቃል እየለቀምኩ ነው የማነበው፤ በሚገባኝ ቃላት፣ በምረዳው አገላለፅ ለእኔ የተፃፈልኝ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ በቃላት ጠግባችሁ ታውቃላችሁ? አንድ ነገር ከመጠን ሲያልፍ እንደሚያቅለሸልሸው ነው የሆነብኝ፣ የሆነ የማስታወክ ስሜት ተሰማኝ፣ በቃላት ቁንጣን ተወጠርኩ፣ የፊደላት ህቅታ፣ ወደ ላይ ሊለኝ ሆነ… እንደ ምንም ብዬ መፅሃፉን ከአይኔ ላይ መነጨኩት፡፡


ሲጋራዬን ለኩሼ በረጅሙ ወደ ውስጥ ከመጠመጥኩት በኃላ ኡፍፍፍፍፍ! ብዬ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡ ከዛም የመፃፍቱን ቃላቶች በተመስጦ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡ በቃላቶቹ ያ ጎርናና ድምፅ ያለው ሰውዬ እየደጋገመ የሚገስፀኝ መሰለኝ፣ በሚቆጣ ትዕዛዛዊ ድምፅ፡፡ ማንነቴን ወደ ኋላ ዞር ብዬ መገርመም ጀመርኩ፣ በሂሳዊ አይን፡፡ “ህይወቴን በጥርጣሬና በነቀፌታ ሞልቻት ኖሬያለሁ፤ በዚህም ምክንያት ችሎታዬንና አውቀቴን አውጥቼ እንዳልጠቀም ሆኛለው፣ እውቀቴ የመመፃደቅና የትችት ነበር፤ በራሴ ድብርታም አለም ውስጥ ስሽከረከር ጊዜዬን ፈጅቼዋለሁ…  እራሴን ጠዘጠዝኩት፤ አቤት ግለ-ሂስ!” 


ውስጤ ሲታደስ ተሰማኝ፤ በሀሴት ተሞላሁ፡፡ “…ምናልባትም ህይወት እኔ እንደማስባት ጨለማ ላትሆን ትችላለች፣ ምናልባትም ብሩህ መንገድ ይኖራታል፤ እይታዬን የማስተካከያ ጊዜዬ አሁን ነው…” አልኩኝ፣ ለራሴ ይሁን ለባለ ጎርናናው ድምፅ ሰውዬ ሳላውቀው፡፡
ወደ ውጪ መውጣት ፈለ’ኩ፣ የህይወትን ሌላ ጎን ለማየት ጓጓሁ፣ ባልተሄደበት መንገድ ለመሄድ ፈለኩ፤ ዳሩ ምን ዋጋ አለው ቀኑ አርጅቶ ነበር፤ ምሽት፡፡


ግንቦት 14 (ለመጀመሪያ ጊዜ ሳልሰርዝ ሳልደልዝ ቀን የፃፍኩበት ቀን)
አይናችሁን መጀመሪያ ገልፃችሁ ነው ከዛ የምትነቁት ወይስ ነቅታችሁ ነው አይናችሁን የምትገልፁት? እኔ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቴ በፈገግታ በርቶ ከእንቅልፌ ተነሳሁ፤ አይኔን ገለፅኩ፤ ነቃሁ! በሬን ከፍቼ እስክወጣ አላስችል አለኝ፣ ባልተሄደበት መንገድ ጉዞዬን ለመጀመር አሀዱ አልኩ፤ ደስ ሲል!  


ይድረስ ለውዷ እናቴ፣ ሉሲይድረስ ለውዷ እናቴ፣ ሉሲ


መቼም ለዘንድሮ የትንሳኤ በዓል  ወደ አገሩ ያልተከተተ ኢትዮጲያዊ የለም፡፡ ያው ከአገሩ የወጣ ሰው ወደ ትውልድ ቀዬው ለመመለስ ምክንያት መደርደሩ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ታዲያ ለእንዲህ አይነቱ ሰው በተለይ ለክርስቲያኑ ማህበረሰብ ወደ አገሩ ለመመለስ እንደ ፋሲካ ያለ ድንቅ በዓል አይገኝም፡፡ ይሄ በውጪ ያሉ ሰዎች ይናፍቀናል የሚሉት የዓውድ-ዓመት ሽታና ግርግር ከሌሎች በዓላት በተሻለ ሁኔታ በትንሳኤ በዓል ስለሚደምቅ ነዋ፡፡ 

ታዲያ በዚህ የትንሳኤ በዓል በህይወት ያለ ኢትዮጲያዊ ቀርቶ አንቺ ውዷ እናታችን-ሉሲ እንኳን ከአምስት አመታት የአሜሪካ ቆይታ በኃላ ወደ አገሽ ከተፍ ማለትሽን ሰማን፡፡ ፋሲካን ከዘመድ አዝማዶቼ፣ እትብቴ ከተቀበረባት፣ አፅሜ ተቆፍሮ ከወጣበት የትውልድ አገሬ ልከተት ብለሽ፡፡ ለማንኛውም እንኳን በሰላም ወደ አገርሽ ተመለሽ ብለናል፡፡ እንኳን በሰላምና በጤና ላገርሽ፣ ለአፈርሽ፣ ለቀዬሽ አበቃሽ ብለናል፡፡ ድንቅ ነሽና ድንቅ የሆነ የዳግማ-ትንሳኤ በዓልንም ተመኝተናል፡፡

ከሁሉ ከሁሉ የደነቀኝ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ስለ አንቺ የሚወራው አሉባልታ መብዛቱ ነው፤ እንደውም ምን ሲሉ ሰማሁ መሰለሽ፣ ሉሲ አሜሪካን አገር በነበራት ቆይታ በቁሙ ያለ ኢትዮጲያዊ ያልሸቀለውን ዶላር ሸቃቅላ ነው የመጣችው እያሉ ሲያወሩ፡፡ እሰይ! እንኳን! ደግ አደረግሽ! እንደ አንዳንድ ዓላማ ቢስ፣ ቡኩን፣ ስደተኛ በብልጭልጭ ነገር ሳትታለይ፣ በዘመነው የውጭ አገር አኗኗር ሳትደለይ፣ የተሰደደሽበትን አላማ ሳትረሺ፣ አልበላም አልጠጣም ብለሽ፣ የሰራሻትን እያንዳንዷን ሽርፍራፊ ሳንቲም ሳትቀር በመሃረብሽ ቋጥረሽ ወደ አገርሽ መመለስሽ ብልጥነት እንጂ ፋራነት አይደለም፡፡ 

ሌላ ደግሞ ምን እያሉ ሲያወሩ ሰማሁ መሰለሽ፣ ሉሲ አሜሪካን አገር በሸቀለችው ዶላር ለእናቷ ሲኤምሲ አካባቢ ምን የመሰለ ቤት ገዝታላቸዋለች፣ ለአባቷ ደግሞ ሲኖ ትራክ፣ ለወንድሞቿ ለአንዱ ላዳ፣ ለአንዱ ሚኒ ባስ… ምናምን እያለ ሰዉ ያወራል፡፡ እውነት ይሆን ሉሲ?
የሚወራው ነገር እውነት ቢሆንም እንኳን ምንም አይደለም ሉሲዬ፡፡ በሰው አገር ላብሽን አንጠፍጥፈሽ፣ የስንቱን አይንና ግልምጫ ችላ ብለሽ፣ በስንቱ ታይተሸ፣ ያገኘሽውን ገንዘብ ለራስሽ አንድም ነገር ሳታደርጊበት፣ መዘነጥ፣ መሽቀርቀር፣ ዳንኪራ መርገጥ አማረኝ ሳትይ ወደ አገርሽ ይዘሽ መመለስሽ የሚያስመሰግንሽ እንጂ የሚያሳማሽ አይደለም፡፡ ይልቁንም የጀግና፣ የኩሩ ኢትዮጲያዊ ተግባር ነው፡፡ ኩሩ የናቷ ልጅ! ልጅ ማለት እንዲህ ነው! የሚያስብልሽ ነው፡፡ አንዳንዱ በቁሙ ቤተሰብ ያሳዝናል፣ አገር ያሰድባል፤ እንደ አንቺ አይነቱ ግን 'አይ ልጅ!' እየተባለ ይሞካሻል፡፡ ይኸው በሙትሽ እንኳን እኛ ጋር ነይ፣ እኛ እንይሽ እየተባለሽ በየቦታው፣ በየአገሩ ጥሪ ይቀርብልሻል፤ ለእይታ ብቻ በርካታ ዶላር ይዘንብልሻል፡፡

በኔ በኩል ወደ አገርሽ መመለስሽን ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? በቃ ይሄ በየቦታው ቁጭ ብሎ ወሬውንና ሃሜቱን ከመሰለቅ ውጪ ቁም ነገር የማያውቀውን፣ የኩታራ አሉባልታና እነቶ ፈንቶ ወሬ ኩሽ አደርገሽዋ፡፡ 

አንድ ሰሞን የእናትነት መንፈስሽ ካለሽበት ጠርቶኝ ነው መሰል በናፍቆት ተቃጥዬ "አረ የሉሲ ነገር እንዴት ነው፣ ጠፋችብን እኮ ቤቷ ስንሄድ የምናገኘው ምስለ-አካሏ የሷነቷን ያህል መንፈስ የለውም፣ የእናትነት ጠረን የለውም፣ የእምዬን ናፍቆትና ርሃብ አያስታግስም" ብዬ ብጠይቅ  "አልሰሜን ግባ በለው! ሉሲ እኮ አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቃለች፤ ላትመለስ ነው የሄደችው አሉኝ" ጠላትሽ ክው ይበል፤ ው ብዬ ቀረሁ፤ በድንጋጤ እንዳንቺው አፅም ሆንኩልሽ፡፡ ጠላትሽ አመዱ ቡን ይበልና አመዴ ቡን አለ፡፡ አሁን ግን በቃ መምጣትሽን ስሰማ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ፣ የደስታና የናፍቆት ሲቃ ተናነቀኝ፤ ለነገሩ ያው የልጅ ነገር ሆኖብኝ ደነገጥኩ እንጂ ጨቅነሽ እንደማትጨክኚ፣ ቀርተሸ እንደማትቀሪ ልቤ ያውቀው ነበር፤ ለማንኛውም በድጋሚ እንኳን በሰላም መጣሽልኝ እናቴ፡፡

ያው የዚህ አገር ኑሮ እንደምታውቂው ነው፤ መቼም ትረሺዋለሽ ብዬ አላስብም፤ ምንም እዛ ብትሆኚም ልብሽ እዚህ ነውና፡፡ ኸረ ለመሆኑ! ረስቼው ሳልጠይቅሽ፣ የዛሬ አምስት አመት ጥለሻት የሄድሻት አገርሽን እንዴት አገኘሻት? ፐ! ጉድ ሆናለች አይደል! አዲስ አበባንማ ተያት በቃ ቀውጢ እኮ ነው የሆነችው፤ የሆነ የልማት አርበኛ ገበሬ የቆፈራት ትልቅ ማሳ እኮ ነው የምትመስለው፡፡ ብቻ የሁን መቼም የአስፋልቶቻችን ማማርና መስፋት እራሱ ቀላል ነገር አይደለም ቢያንስ ቢርበን እንኳን ጥሩ አስፋልት ላይ ተሰጥተን ጥርሳችንን እንፍቃለን፣ ሆዳችንን ረሃብ እየፋቀውም ቢሆን፡፡ በዛ ላይ ደግሞ እንደ 77ቱ ምናምና ይሄ ለፎቶ የሚደብር ባግራውንድ አይኖረንም፤ በቃ… አለ አይደል… ቀብረር ያለ አስፋልት ላይ ባንቺ መሪነት ምርጥ የአፅም ሾው እናሳያለን፤ ልክ እንደ ማይክል ጃክሰን ክሊፕ፡፡  

ኪ.ኪ.ኪ.ኪ.ኪ.… አልሽ? አይይይ…እ… አንቺ ምን አለብሽ እናቴ፣ ሳቂ በድድሽ፣ ሆድ የለሽ፣ ጥርስ የለሽ እኛው እንደፈረደብን እናማር እንጂ፤ የፈለገስ ቢሆን ደግሞ እድሜ ለአሜሪካን ዶላር፣ መመንዘር ነው፡፡ አይ የኔ ነገር፣ ይቅርታ የኔ እናት፣ ይሄ የኑሮ ነገር ሲነሳ ፀባዬ ሁሉ ቅይርይር ይላል ታውቂው የለ ክፋት እንደሌለብኝ፤ መቼም አትቀየሚኝም፤ ደግሞ መቀየም እኮ የኢትዮጲያዊ ብቸኛ ባህሪ ነው፤ አንቺ ደግሞ አምስት አመት አሜሪካ ተቀምጠሸ መቀየም የሚባለውን ቃል ከነመፈጠሩም የረሳሽው ይመስለኛል፡፡

እ…ሺ...! ታዲያ አሜሪካንን እንዴት አገኝሻት? መቼም እንደነ እገሌ ምነው አሜሪካዊ በሆንኩ ብለሽ አልተመኘሽም፤ እንደውም እንኳንም ኢትዮጲያዊ ሆንኩ ነው ያልሽው አሉ፡፡ ምክንያቱም አሜሪካዊ ብትሆኝ ኖሮ ማን ቆፍሮ ያወጣሽ ነበር፤ አሜሪካ ውስጥ አርኪዮሎጂስቶች ቆፍረው ሊያወጡት የሚችሉት እድሜ ጠገብ ታሪካዊ ቅርስ ቢኖር የክርስቶፎር ኮሎምበስ የውሃ መያዣ ኮዳ ነዋ፤ በቃ ከዛ የዘለለ ታሪክ የላትማ፡፡ ታዲያ ኢትዮጲያዊ በመሆነሽ ከነድህነታችንም ቢሆን አልኮራሽም? እንደውም ስሰማ፣ ፕራውድ ቱ ቢ ኢትዮጲያን የሚል ቲ-ሸርት አድርገሽ ሁላ ነው ወደ ኢትዮጲያ የገባሽው ይባላል፤ እውነት ነው?

በነገራችን ላይ፣ ያው የደሃ ነገር ታውቂዋለሽ፣ አይሞላለትም፤ ላይ ታች ስል፣ ከዛሬ ነገ እህዳለሁ ስል፣ መጥቼ ሳላይሽ ይኸው ዳግማ-ትንሳኤ መጣ፡፡ ቢሆንም ግን ይህቺ ደብዳቤ ከእኔ ቀድማ እንደምትደርስሽ አስባለሁ፡፡ በአካል ተገናኝተን የልብ የልባችንን እስክናወጋ፣ የፈረንጅ አገር ትዝብትሽንና ቆይታሽን እስክታጫውቺኝ፣ የናፍቆቴን ያህል ይህችን እጥር ምጥን ያለች ደብዳቤ አሰናድቻለሁ፡፡

እስቲ አሁን ደግሞ፣ ልጅ ነኝና እንደ ልጅ የልጅ ጥያቄ ልጠይቅሽ፣ ከውጪ አገር ምን አምጥተሸልኝ ይሆን? ላፕ ቶፕ፣ አይ ፎን፣ ስኒከር ወይስ ቲሸርት? መቼም ቲ-ሸርትም እንኳን ቢሆን እንደ እነ እገሌ አይ ላቭ ኒው ዮርክ የሚል ቲሸርት አታመጪልኝም፤ ምክንያቱም አይ ላቭ ኢትዮጲያ ብለሽ ነዋ የመጣሽው፡፡ ለማንኛውም ቸኮሌትም ቢሆን ይቀመጥልኝ ከሰሞኑ መጥቼ ሳላይሽ አልቀርም፡፡
"አይት በይ ነብሴ!" (ይቺ ከፊል እንግሊዘኛ፣ ከፊል አማርኛ፣ ከፊል አማርዝኝ የሆነች ሀረግ፣ በእንግሊዘኛ Alright then፣ እንደማለት፤ አሜሪካ ደርሰው የተመለሱ ጀለሶቻችን የሚያዘወትሯት ናት) አንቺም ሳትለምጂያት አትቀሪም ብዬ ነው፡፡ በይ እናቴ በአገርኛው ደግሞ፣ በአካል በአይነ ስጋ እስክንገናኝ ድረስ ቸር ሰንብቺ፡፡ እስከዛው ግን ሰላምታዬ በአይር ይድረስሽ ብያለሁ ውድ እናቴ-ሉሲ፤ ሎንግ ሊቪ ሉሲ! ሎንግ ሊቭ ኢትዮጲያ!

መፈክር አልባ ሰልፈኛ!

በቃ ጦቢያ እንዲህ ሰልፍ አፍቃሪ ሆና ትቅር? እውነቴን እኮ ነው፣ ለትንሽ ትልቁ መሰለፍ የዕለት ተዕለት ተግባራችን እየሆነ መጥቷል፡፡ ነጋዴዎች ገዢ ሲሰለፍላቸው፣ የመንግስት ሰራተኞችም ባለጉዳይ ሲደረደርላቸው ደስታቸው ነው፡፡ ይብዛም ይነስም ሁላችንም ባለችን አቅም ማሰለፍ እንወዳለን፡፡ መንግስትም ግለሰብም፤ ዕድርም ጠበልም … ያሰልፉናል፡፡ እግረኛም ሁኑ ባለ መኪና በቀን ውስጥ ትንሽም ብትሆን ሳትሰለፉ የምትውሉባት አጋጣሚ አትጠፋም፡፡ የትምህርት ቤት፣ የዳቦ ቤት፣ የማደያ፣ የቀበሌ አልያም ክ/ከተማ፣ የኢሚግሬሽን፣ የአውቶቢስ፣ የሲኒማና የቲያትር ቤት ሰልፍ፣ የታክሲ ሰልፍ…ብቻ ምን አለፋችሁ ሰልፍ በያይነቱና በየቦታው ሞልቶላችኋል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው መንግስትም ሰልፉን እያየ መፍትሄ የማይፈልገው … ይሄ ህዝብ የ “ሰላማዊ ሰልፍ” ረሃቡን ይወጣ” እያለ ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ግን መፈክር አልባ ሰልፍ መሆኑ ነው፡፡ መፈክር የሌለው ሰልፈኛ! የጦቢያ ሰው መቼም ስም አወጣጡ የሚገርም እኮ ነው፡፡ የሀበሻ ወላጅ ለልጁ ሰልፉ፣ ሰልፍነሽ፣ ሰልፏ እያለ ሁሉ ስም ያወጣል፡፡ ውሸት እንዳይመስላችሁ፡፡

የድሮ ሰራተኛችን ስሟ ሰልፏ ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ Line ወይም Queue ብሎ ለልጁ ስም የሚያወጣ ፈረንጅ አይኖርም፤ ካለም ወይ ኢትዮጵያዊ ያገባ አልያም ኢትዮጵያ የገባ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ወግ ትዝ አለኝ፡፡ ሴትየዋ ከሰፈር ሰው አይስማሙም አሉ፤ በቃ በትንሽ ትልቁ ከሰው የሚናቆሩ፣ ከጐረቤት የሚሰዳደቡ ቢጤ ስለሆኑ የአካባቢው ሰው ሁሉ አግልሏቸዋል፡፡ ታዲያ የውሻቸውን ስም ምን ብለው እንዳወጡለት ታውቃላችሁ? “ምን ሊጐዱህ” እናም ግቢያቸው ውስጥ ሆነው ጐርደድ ጐርደድ እያሉ ለጐረቤት በሚሰማ ድምጽ ጮክ ብለው “ምን ሊጐዱህ … ምን ሊጐዱህ” እያሉ ይጠሩታል፤ “ናስቲ ምን ሊጐዱህ…ምን አባታቸውንስና ነው! ማነው የመታህ? ደግሞ አይዞህ!” እያሉ ያባብሉታል፣ ያሻሹታል -የራሳቸውን ስሜት በውሻቸው አስመስለው… በነገራችን ላይ ይሄን ሁሉ ወግ የት ሆኜ እንዳውጠነጠንኩት ታውቃላችሁ? (አታውቁም! እዚሁ ገርጂ የቦሌ ድልድይ ጋ የታክሲ ወረፋ ቆሜ እየጠበቅሁ ነው፡፡ ሰልፉ ረጅም ስለሆነ ረጅም ሃሳብ አሳስቦኛል፡፡

ለዚያውም በጠዋት ተነስቼ፣ ከፊል “ደመናማ” ሆኜ … ማለትም ከፊል እንቅልፋማ ሆኜ ነው፡፡ ይሄ የታክሲ ሰልፍ የሚባል ነገር ከመጣ በኋላ እንቅልፌን በአግባቡ ሳልጠግብ እየተነሳሁ ተቸግሬያለሁ፡፡ እርግጥ ነው ሰልፉ ለሴቶች፣ ለህፃናትና ለአቅመ ደካሞች ፍትሃዊ አሰራር የፈጠረ ቢሆንም ለእንደኔ አይነቱ ጐረምሳ ግን ጠዋት ጠዋት የምሰራትን ፑሻፕ ከንቱ አድርጎብኛል፤ ምክንያቱም ሰልፍ ላይ ግፊያ የለማ! ግፊያ ከሌለ ደግሞ አቅሜን አላሳይም፡፡ በአንድ በኩል ይህ ሰልፍ በመጀመሩ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ እንዴት? አትሉም፣ በቃ ታክሲ ለመያዝ ስትጋፉ ስልኮቻችሁንና ዋሌቶቻችሁን ላጥ የሚያደርጉ ሌቦች አፈር በላቸዋ! ግርግር ለሌባ ይመቻል አይደል የሚባለው፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ‘የታክሲ ግፊያ ሌቦች’ በአሁኑ ሰዓት አጭር ስልጠና እየወሰዱ ነው፤ ስልጠናው ‘የሰልፍ ላይ መንጩ’ የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን የስልጠናውም ዋና አላማ ስነ-ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንዴት ወደ ኪስ ተገብቶ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን መስረቅ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ተግባራዊ ስልጠና መሆኑን ያልታመኑ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ካሁን በኋላ በግርግር አትሰረቁም ማለት ነው፤ ይልቁንም በእርጋታና በስነ-ሥርዓት እንጂ፡፡ የታክሲ ሰልፍ በእኔ አተያይ እንደሌሎች ተራ ሰልፎች አይደለም፡፡ እንደውም ከተራ ሰልፍነት በዘለለ አያሌ ጥቅሞችን ሊያስገኝ የሚችል ነው ባይ ነኝ፡፡
ከአያሌ ጥቅሞቹም መካከል አንዱ የስራ ዕድል ፈጣሪነቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ግንባር ቀደም ወጣቶች በቀድሞ አጠራራቸው የመንደር ቦዘኔዎች በቅርቡ ‘ህዳሴ የታክሲ ላይ ወረፋ ያዦች የህብረት ስራ ማህበር’ በሚል ተደራጅተው ወረፋ በመያዝ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያከራዩ … (አሃ! ይሄ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ ያስብላቸው ይሆን እንዴ?) እንደሚሸጡ ይጠበቃል፡፡ ታዲያ ወረፋውን ከፍሎ ያስይዘ የኔ አይነቱ እንቅልፋም ሀሳቡን ጥሎ ለጥ ብሎ፣ ስልክ ሲደወልለት ብቻ ጎርደድ ጎርደድ እያለ መጥቶ ታክሲው ውስጥ መግባት ነው፡፡ ያው የቀረው ተሰላፊ ደግሞ እንደተለመደው “እንዴ! ምንድነው እኛ ተሰልፍን የለ እንዴ?!” ምና ምን … ምና ምን … ጉሩምሩምታ ሲያሰማ ቀብራራው እኔ “ዝም በል ባክህ! ከፍዬ እኮ ነው ሰልፍ ያስያዝኩት… እንዳንተ በነፃ የተሰለፍኩ መሰለህ እንዴ” ብዬ ይህንን ግሳፄና ክፍያ የሚፈራውን የሃበሻ ልጅ ውሃ አደርገዋለሁ፡፡

ቁጥር ሁለት የስራ ዕድል ደግሞ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ጥቃቅንና አነስተኛ ካፌዎች ሊፈጠሩ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩ ነው፡፡ ‘ይቻላል ቁርስ ቤት’ አይነት ሱቅ በደረቴ ቁርስ ቤቶችን ጠብቁ፡፡ ይሄ መንገድ ላይ መፀዳዳት እንጂ መመገብ አይሆንለትም እየተባለ የሚሞካሸው ማህበረሰባችንን ቀለል ያሉ ቁርሶችን … እንደ ሻይ በዳቦ አጫጭር ሰልፎች ላይ፤ እንዲሁም ከፉል እስከ ፍርፍርን ደግሞ ረጃጅም ሰልፎች ላይ በመሸጥ በጊዜ እጥረት ሳይሆን በእንቅልፍ እጦት የተነሳ የአመጋገብ ባህሉን እንዲያዘምን ማድረግ … በዚያውም የትላንት “የሰፈር ቦዘኔዎች”ን የዛሬ ግንባር ቀደም ነጋዴ ወጣቶች እንዲሆኑ ማገዝ … በነገራችን ላይ የታክሲው ጉዞ ከሚፈጀው ጊዜ ይልቅ የሰልፉ ርዝመት ስለሚበልጥ ድርጅቶች፤ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን በሬዲዮ ከሚያስተዋውቁ ይልቅ እነዚህ ሰልፎች አካባቢ ተንቀሳቃሽ ቢልቦርድ በማቆም ወይም ፍቃደኛ ተሰላፊዎችን ማስታወቂያ በማስያዝ ቢያስተዋውቁ፣ ይበልጡኑ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሰልፎቹ ሊያስገኙ የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በጥቂቱ ከላይ ለመግለፅ ሞክሬአለሁ፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ልለፍ፡፡ እነዚህ ሰልፎች ህዝቡ ስለ ኑሮ ውድነቱ፣ ስለ ፖለቲካው፣ ስለ አገር ልማቱ፣ ስለ ገቢ መቀነስ ስለ ሆድና መንገዶቻችን መስፋት ወዘተ የሚማከርባቸውና የሚያማርርባቸው መድረኮች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች ቀልዶችን የሚሰነዛዘሩባቸውና የሚዝናኑባቸው፣ ባስ ሲልም የሚጠባበሱባቸው ቦታዎች ሆነዋል፡፡ ወደፊት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የታክሲ ወረፋ ወደያዙ ሰልፈኞች መጥተው ቢቀሰቅሱ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች በመኪና እየዞሩ ቤንዚንና ጎማቸውን ከሚጨርሱ እነዚህ ሰልፎች ጋ ቆመው ቢቻል ኩኪስና ሃይላንድ እያደሉ፣ ካልሆነም ደግሞ አበል እየሰጡ መፈክር ቢያሲዙንና የምረጡኝ ሲንግላቸውን ቢለቁብን ሰልፋችን አንድም አሰልቺ፣ አሊያም መፈክር አልባ አይሆንም እላለሁ፡፡ በሉ ሰልፌ ደርሶ ታክሲ ውስጥ ገብቻለሁ፤ ቸር ሰንብቱ፡፡ ሰልፍ ለዘላለም ትኑር!

Saturday, 20 April 2013 Saturday, 20 April 2013
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የታተመ