Sunday, August 25, 2013

ህፃንኛ-2


ሁለት በ ሁለት ፍቅር

ተወልጄ ያደኩት ከእናቴ ጋር ነው… እናቴም የምትኖረው ከኔና ከእናትና-ልጅ(አረቄ) ጋር ነው… በ ሁለት በ ሁለት ቤታችን ውስጥ…

ታዲያ… ፍቅር የሚገለፀው ሁሌም በሁለትዮሽ ብቻ ይመስለኛል… ለምሳሌ እኔና እናቴ… ሁለት ብቻ ነን… የአረቄ ጠርሙሱ ላይ ያሉት እንስሶች… አጋዘን መሰሉኝ… እናትና ልጅ ይሏቸዋል… እነሱም ሁለት ናቸው… እኛ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው የእመቤታችንና የልጇ ምስል… እነሱም ሁለት ናቸው… ከሩቅ ደግሞ… የነዚህን ሁለት ነገሮች ፍቅር ከላይ ሆነው የሚጠብቁ... ሁለት መልዓክት አሉ… ልክ የእመቤቴና የልጇ ምስል ላይ እንዳሉት…  

የሰፈር ልጆች… "አባትህ የት ነው? አባት የለህም እንዴ?" እያሉ ይጠይቁኝና ሊያበሽቁኝ ይሞክራሉ… እኔ ግን አልበሽቅላቸውም… እንደውም እንደኔና እማዬ ሁለት ባለመሆናቸው አዝን ነበር… ምክንያቱም ሁሉም ጎረቤቶቻችን ሲጨቃጨቁ… ሲጣሉ… ሲደባደቡ አያለው… እናም እንደኔና እማዬ ሁለት ባለመሆናቸው ነው ብዬ አስባለው… እኔና እማዬ አንድም ቀን ተጣልተን አናውቅም… ሁለት በ ሁለት ቤታችን ውስጥ ሁልጊዜም ደስ የሚል ፍቅር አለ… ጥልና ፀብ እራሱ ምን እንደሆነ ያወኩት በጎረቤቶቻችን ምክንያት ነው…

አንዳንድ ጊዜ ቤታችን ከሁለት በ ሁለት ትንሽ ብትሰፋ እኔና እማዬ እራሱ ዝም ብለን የምንጣላ ይመስለኛል… ምንም እንኳን ሁለት ሰው ባይጣላም…

አባት ግን ምን ይሰራል? አባት ኖሮኝ ባያውቅም… የሌሎች ልጆች አባቶች ሁሌም ሲቆጧቸውና ሲገርፏቸው… ልጆቹም አባቶቻቸውን ሲፈሩ ነው የማውቀው… አባቶች ልጆችን ብቻ አይደለም የሚቆጡትና የሚገርፉት እናቶችንም ጭምር ነው… አንዳንድ ጊዜ ሳስበው… ግድ ሆኖባቸው እንጂ… እንደኔና እማዬ እደለኛ ሳይሆኑ ቀርተው እንጂ… የጎረቤት ልጆችና እናቶች እራሱ አባት ባይኖራቸው የሚመርጡ ይመሰልኛል…

አባቶችም ለክፋትና ለፀብ ብቻ የተፈጠሩ ይመሰልኛል… ለዛም ነው… ጦር ሜዳ የሚልኳቸው… ለምሳሌ እኛ አረቄ ቤት የሚመጡት ሁሉም አባቶች ናቸው… ታዲያ… ሰክረው ጮክ ብለው ከማውራትና ከመሰዳደብ ውጪ ሌላ ስራ የላቸውም… ታዲያ አባት ምን ይሰራል? የእመቤቴ ማሪያምና የልጇ ምስል ላይ እራሱ አባት የለም… ስለዚህ ፍቅር የሚገለፀው በሁለት ነው ብዬ አስባለው…

ሰው ከሁለት በላይ ከሆነ ሁሌም የሚጨቃጨቅ ይመስለኛል... ለምሳሌ የኛ ቤት… ሁለት በ ሁለቷ… አረቄ ጠጪዎች ሲመጡባት… ወዲያው ቀውጢ ትሆናለች… እኔና እማዬ ለሁለት የዘራንባት ፍቅር ወዲያው በጭቅጭቅና በፀብ ይደፈርሳል…

እናም… በቃ… ሰው ከሁለት በላይ ሆኖ መኖር የለበትም ብዬ አስባለው… ለዚህም ይመስለኛል የሰውነት ክፍሎቻችን እራሳቸው በአብዛኛው ሁለት ሁለት ሆነው የተፈጠሩት… ሁለት እጅ… ሁለት እግር… ሁለት ጆሮ… ሁለት አይን… እንዲሁም… እንደ ነገረኛ ጎረቤታችን… ሁለት ምላስ…



10/90… 20/80… 40/60 እና 50


`ህዝቡ መንግስት ከንግድ ባንክ ጋር በመሆን አጭበርብሮኛል ሲል አስታወቀ… ለዝርዝሩ… ገንዘቤ ሽብሩ…

አመሰግናለው ባልደረባዬ… እንደሚታወቀው… መንግስት ባሁኑ ሰዓት… በነዋሪው ቅድመ-ቁጠባ የሚገነቡ የኮንኮሚኒየም ቤቶችን ለመዝራት ማቀዱንና የአፈር ምርመራ… የአረሳ… የጉልጎላና (ነዋሪውን ከየቤቱ)… የምርጥ ሳይት መረጣ ቅድመ ሥራው ከወዲሁ በሚገባ መጠናቀቁን አስታውቋል…

መንግስትን… "ይህን ፕሮግራም እንዴት አሰብከው ጃል?" ብዬ ላቀረብኩለት ጥያቄ እንዲህ ሲል ምላሹን ሰጥቶኛል…

"እንደምታውቁት የመንግስት ዋነኛ አላማ ህብረተሰቡን ማስከፋት ነው… ህብረተሰቡ ሲከፋ ደግሞ ችግሩን ይገልጣል… ችግሩን ሲገልጥ ደግሞ እኛ መፍትሄ ይዘን ብቅ እንላለን ማለት ነው…"
እንዴ?! መንግስት የህዝቡን ጥያቄ የሚረዳው ህዝቡን በማስከፋት ነው ወይስ በሰለጠኑ ባለሙያዎቹ የህዝቡ ፍላጎት ምን እንደሆነ አስጠንቶ ነው?

"ምን አይነት ጥያቄ ነው? እናንተ ጋዜጠኞች ስትባሉ ደግሞ ጥያቄ አመራረጥ አትችሉበትም… ቆይ የህዝቡን በሽታና መከፋት ካላወቅን… አመመኝ… ደከመኝ… እንዲህ ሆንኩ… እንዲያ ሆንኩ… እዚህ ጋር ቆረጠኝ… እዛጋ ፈለጠኝ ካላለን… መንግስት ጠንቋይ ነው እንዴ በግምት አስጠንቶ የሚደርስበት? ለጥናትና ለምርምር ብለንስ ምን ትርፍ ወጪ አስወጣን… ህዝቡ… እራሱ… ሲበላው ይናገር የለም እንዴ… እኛ ማን ነንና ነው ህዝቡ ሳይበላው የምናክለት…"

ታዲያ… እንደዛ ከሆነ… በቤት ጉዳይ… የህዝቡን መከፋት እንዴት ደረሳችሁበት…

"ያው እሱማ… መንግስት አይኑም ጆሮውም ሰፊ ነው… ብዙ ነው… ሲባል ሰምተህ የለ… ታዲያ ይሄ ጆሯችን ምን ሰማ መሰለህ… ህዝቡ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር የሚያቀነቅናትን የአዲስ አመት ግጥም…"

ምን የሚለውን?

"‘እንኳን ቤትና የለኝም አጥር እደጅ አድራለው ኮከብ ስቆጥር' የሚለውን ነዋ… በየአመቱ የቤት ባለቤት ብናረገውም… ይቺ ግጥሙ ይኸው እስከዛሬ ድረስ አልተለወጠችም… ታዲያ ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው… ለህዝቡ በሰፊው… ፕሮጀክት ቀርፆ… ቤት መዝራት እንደሆነ ደረስንበትና ከንግድ ባንክ ጋር ሆነን አረሳችንን ጀመርን…"

ይህ በእንዲህ እንዳለ… በተመሳሳይ ዜና… መንግስት ይህን የቤት ልማት ፕሮጀክት አብረን በደቦ እንዝራ ብሎ ንግድ ባንክን ሽማግሌ የላከበት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን… ንግድ ባንክም በበኩሉ… ለጋራ ጥቅማችን እስከሆነ ድረስ ምን ገዶኝ በማለት አጉራአጠናኛ ማለቱን ሰምተናል…

በመሆኑም… ንግድ ባንክ በወራት ከፋፍሎ… የብር ለቀማ ስራውን ካከናወነ በኋላ… 10/90… 20/80… እንዲሁም 40/60 ቤቶችን ከመንግስት ጋር ሆነን አብረን እንዘራላችኋለን ካለ በኋላ… ብዙም ሳይቆይ… የህዝቡን ዘፈን መልሶ ለራሱ እንዲሉ… ንግድ ባንክም እንዲህ ሲል ተደምጧል…

እኔም እኮ… ለወጉ እንጂ… ነፍስ ያለው ቤት የለኝም… ይኸው ከተመሰረትኩ ጀምሮ ዝንት አመት ሙሉ የማስበው… የማሰላስለው ይሄንኑ ነበር… እኔም እንደ ህዝቡ ስለ ቤት ስዘፍን ከርሜያለው… በመሆኑም… እድሜ ለዚህ ምስኪን ህዝብ (ብር አምጣ ሲሉት እሺ ነው… በዚህ ውጣ ሲሉት እሺ ነው… በዛ ተነቀል ሲሉት እሺ ነው…) እንዲሁም እድሜ ለቤቶች ልማት ፕሮጀክት… አሁንማ ካዝናዬ ሞልቶ ብዬ… በአገር ውስጥና በውጭ አገር ተቋራጭ ድርጅቶች አስጠንቼ… የቅርንጫፎቼ ሁሉ ዋና የሆነውን አውራ ብር መሰብሰቢያ ቤቴን… ባለ ሃምሳ ፎቅ ልሰራ ነው… እ-ን-ቁ-ጣ-ጣ-ሽ ማለት እንዲህ ነው… እልል በሉልኝ… ሲል በአፉ ሙሉ ተናግሯል… በካዝናው ሙሉም ብር ይዟል…

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ ማለት ይሄኔ ነው… ከኋላ የመጣ አሉ… መንግስት እንኳን ይሄን ሁሉ አመት በአንድ ቤት እየኖረ… ለራሴ ቤት አማረኝ ሳይል… ለህዝቡ ምሬት በአንድ ቤት እንደቆመ… ይኸው አጅሬ ንግድ ባንክ ከኋላ መጥቶ… ለምን ህዝቡ ብቻ ኮከብ ይቆጥራል… እኔስ ለምን ለኮከብ አልቀርብም ብሎ ባለ 50 ፎቅ ቤት ሊያሰራላችሁ ነው…

ለነገሩ ንግድ ባንክ እውነቱን ነው… ብር ካገኙ አይቀር እንዲህ ነው… መቼም ማናችንም ጥሩ ፈራንካ ብትኖረን መሬት ላይ አንድበሰበስም… ባለ አንድም ትሁን፣ ባለሁለት… እንጣዋን ሰርቶ… ከሰው በላይ ከፍ ማለት ነው እንጂ… የምን ከጭቃና ከደሃ መጋፋት ነው… ፈረንጆቹ ብር ስላላቸውም አይደል መሬት ደበረችን ብለው ወደ ጠፈር ከፍ እንበል ያሉት…

ለማንኛውም… ንግድ ባንክን… እሰየው… ጎሽ… ደግ አደረክ… አንተም ባለ 50 ፎቅህን ስራና እኛም ባለ አስራ ሁለቷ ላይ ሆነን ጭቃንና ድህነትን አብረን እንጠየፋለን በሉልኝ፤ ከዛም… ከመሬቷ ከፍ ብለን… ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር! እንንላለና…
  



Saturday, August 24, 2013

ህፃንኛ-1

ዝናብ

ከጓደኛዬ ከፓፒ ጋር ኳስ እየተጫወትኩ ነበር… እኔና ፓፒ ጎረቤታሞች ነን… ቤታችን ፊት ለፊት ለፊት ለፊት ነው…

አሁን ዝናብ እየዘነበ ነው… ዝናብ ሲዘንብ የኔና የፓፒ እናት ወደ ቤት እንድንገባ ስለሚጠሩን እኔና ፓፒ መጋረጃውን ከፍተን በሳሎን መስታወት ፊት ለፊት እየተያየን በምልክት ብቻ እናወራለን… እንሳሳቃለን… እንደንሳለን… እንበሻሸቃለን…

ዝናቡ በጣም እየጣለ ነው… ዝናብ… ዝ-ና-ብ… ስሙ ራሱ ሲያስቅ…

ዝናብ ግን ከየት ነው የሚጀምረው?

እማዬን… "ዝናብ ከየት ነው የሚጀምረው?" ስላት…
"ከደመና አለኝ"

ደመናስ ከየት ነው የሚጀምረው? እንዴትስ ዝናብ ደመና ላይ ሊጠራቀም ይችላል?

ደመና እንደ ስፖንጅ ያለ ነገር አለው? ዝናብን መጦ አየር ላይ የሚይዝበት?

ዝናብ ከሚጀምርበት(ከደመና)- እማዬ እንዳለችኝ… እስከ መሬት እንዴት ብሎ ነው የሚደርሰው?

ዝናብ ከደመና እስከ መሬት እስኪደርስ በዛችው ፓስታ በምታካክል ቅጥነቱ ነው ወይስ ከላይ ሲጀምር ልክ በባልዲ እንደሚደፋ ውሃ ነው?

ከመሬት እስከ ሰማይ ያለው ርቀት አካባቢ ሳይንስ ቲቸር እንደሚሉት በጣም እሩቅ ከሆነ እንዴት ዝናቡን መሃል ላይ ንፋስ አይበታትነውምና አይወስደውም? እንዴትስ መሬት ሳይደርስ አያልቅም?

እኔ ግን የሚመስለኝ… ዝናብ ማለት… ልክ የኛ ዘበኛ ጋሼ ይበቃል… አትክልቶቼን ፀሃይ ቀጠቀጠብኝ… አቃጠለብኝ… ምና ምን… እያሉ ማታ ማታ በውሃ ጎማ እንደሚያጠጧቸው ሁሉ… መልዓክት ደግሞ እኛ ልጆቻቸውንና ምድርን 10ወር ሙሉ ፀሃይ ስታቃጥለን በማዘናቸው ለሶስት ወር ያህል በርሜል በሚያክል የውሃ ጎማ ከላይ ሆነው ምድርን የሚያቀዘቅዟትና የሚያርሷት ነው የሚመስለኝ…








Wednesday, August 14, 2013

እከክና አካኪ


ልጅ እያለው… ገላዬን የምታጥበኝ እናቴ ነበረች… በሳምንት ቁጥሩን በውል የማላውቀው ጊዜ ታጥበኛለች… ኋላ ግን ጉርምስናው ሲመጣ- ማባበጥና ማበቃቀል ስጀምር… እፍረትም አብሮ መጣና እራሴ እታጠባለው ማለት ጀመርኩ…

እናም… ልክ እንደ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ገላዬን በሳምንት አንዴ መታጠብ ጀመርኩ… ሰንበትን ጠብቄ፡፡ ያኔ ተማሪ እያለን እሁድ ብዙ ነገር ናት፡-
-    ገላችንን እንታጠባለን…
-    ካልሲዎቻችንን እናጥባን…

-    ጫማችን ሸራ ወይንም ስኒከር ከሆነ በቆሮቆንዳ ፈትግን እናጥባለን…
-    ቆዳ ከሆነ ደግሞ በስፖንጅ ወልውለን፣ በቁራጭ ጨርቅ አድርቀን፣ በባለ እንጨቱ ቡርሽ ኪዊ ቀለም እስኪያብረቀርቅ ቀብተን አልጋ ስር እናስቀምጣለን…
-    ዩኒፎርማችንን አጣጥፈን ወንበር ላይ እናስቀምጣለን…

ይሄን ሁሉ ነገር ከስምንት ሰዓት በፊት እንጨርስና ስምንት ሰዓት ላይ 120 ለማየት እንደረደራለን… 120 ብዙ ደስ ደስ የሚሉ ነገሮች ነበሩት… ከአድማስ ባሻገር፣ አጀብነው… ሌላም፣ ሌላም… ዜናው ሁላ ደስ ይል ነበር…
-   
120 ሲያልቅ ደግሞ ጂሌት ወርልድ ስፖርት ስፔሻል እናያለን…በቃ… የድሮዋ እሁድ ብዙ ነገር ነበረች… እናም እወዳት ነበር… ልክ አሁን አሁን ቅዳሜን እንደምወዳት፡፡ አይገርምም? እድሜ ሲጨምር የሳምንቱ ምርጥ ቀናችን ይቀንሳል ማለት ነው?

እሁድን ሙሉ ለሙሉ አልወዳትም ነበር… እሁድ ማታ ትደብር ነበር… አባቴ ከያለንበት ያስጠራንና… "የቤት ስራ ሰርታችኋል? እርሳስ፣ እስኪሪብቶ… አሳዩ" እንባላለን… ብዙ ጊዜ እስኪሪፕቶ ስለሚጠፋብኝ ወይ ከጎረቤት ልጆች ተቀብዬ አሳያለው አልያም… ሁሌም የማሳያትን ያለቀች ቢክ እስኪሪፕቶ ከደበኩባት አውጥቼ አሳይና አዲስ እቀበላለው፡፡

ከዛ ያ ቀፋፊ ሰኞ ይመጣል… ከሰኞ እስከ አርብ ያለው ቀን አንድ አይነት ነው… ጠዋት ተነስቶ ሻይ በዳቦ በልቶ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ… ከትምህርት ቤት ተመልሶ እግርን በማስታጠቢያ ውስጥ ዘፍዝፎ መታጠብ… መክሰስ በልቶ የቤት ስራ መስራት… ከዛ ማጥናት… ከዛ ፔትሮላተም ቅባት ተቀብቶ መተኛት….

ያኔ… ተማሪ እያለን… ቀኑን ሙሉ ስንራገጥ ስለምንውል… ላብ በላብ ሆነን አቧራችንን ጠጥተን ወደ ቤት እንገባለን… አንድ አይነት ልብስ-ዩኒፎረም ሳምንቱን ሙሉ ስለምንለብስ እከኩ መከራ ነው፡፡

ደግሞ ምን እንደሚያናድ ታውቃላችሁ? እከክ የሚይዘኝ አልባሌ ቦታ ላይ መሆኑ… መሃል ጀርባዬ ላይ… የማልደርስበት ቦታ…

መጀመሪያ የቀኝ እጄን በማጅራቴ በኩል ወደ ኋላዬ እልክና ለማከክ እሞክራለው… እፍፍፍ… እንዴት አባቱ እንደሚበላ… ዝለል ዝለል ይለኛል… አልደርስበትም… እንደገና የግራ እጄን እልክና ወደ ኋላዬ በእጄ እሳባለው… ጀርባዬ ላይ… እከኳ ላይ ለመድረስ… አአአአአ… አሁንም አልደርስበትም… ከዛ ደግሞ በወገቤ በኩል አድርጌ እጄን ወደ ላይ አንፈራጥጥና እሞክራለው… ጀርባዬን በጥፍሬ እቧጭራለው… ኡኡኡኡ… አሁንም አልደርስበትም… በቃ ያቁነጠንጠኛል… ያዘልለኛል… እንደ በግ ግድግዳ ላይ እታከካለው…
ግድግዳ መታከክ በራስ እጅ እንደ ማከክ አያስደስትም… እንደገና እጄን እያፈራረቅኩ እሞክራለው… የእከኬን አስኳላን… አፏን ለማግኘት… ይሄን ጊዜ አንዱ ጓደኛዬን አይና… "ኡሁሁሁ… በናትህ ጀርባየን እከክልኝ… እዚህ ጋ…" ብዬ የማልደርስበትን ቦታ በእጄ እጠቁማለው…

ከፍ… ትንሽ ከፍ… በቃ… ትንሽ ወደ ግራ… ኖ… ትንሽ… ትንሽ ወደ ቀኝ… ወደ ታች… በቃ… በቃ! እሱ ጋ… ኡሁሁሁ… በደንብ… በደንብ… እ-ሰ-ይ! ሳላቀው ጣፍጭ ምራቄ አገጬ ላይ ይዝረበረባል… አይኔ ይስለመለማል… እፍፍፍ… የሆነ በቃላት የማይገለፅ ደስታ ይሰማኛል… እንደሱ አይነት እርካታ የምረካው አንድም ሽንቴን ወጥሮኝ ስሸና… አሁን አሁን ደግሞ እንትን ሳደርግ ነው፡፡

አንድ ጓደኛዬ ይሄን ፅሁፍ ስፅፍ አጠገቤ ነበር… ስለ እከክ አንድ ቀልድ ነገረኝ… እነሆ፡

አንዱ እንደኔው ያሳክከውና ጓደኛውን ጠርቶ "…ጀርባዬን እከክልኝ?" ይለዋል… አካኪው ታዲያ ከፍ፣ ዝቅ፣ ወደ ግራ… ሳያስብል የበላው ቦታ ላይ- የእከኩን አፍ በአንዴ አግኝቶ ያክለታል…

ታዲያ… ልጁ የበላው ቦታ ላይ በአንዴ ሲያክለት በጣም ተገርሞ… ምን እንዳለው ታውቃለህ?
.
.
.

"እንዴ! አተንተ ነህ እንዴ የበላኸኝ?"




ጉራ ችርቸራ ትሪዲንግ


እኔ እምልሽ… ባለፈው ወክ እያደረግን… የሆነ ጎረምሳ አይተሸ… "ወይኔ ዳኒዬ! አየኸው ያን ልጅ? ዳኒ ይባላል… አብረን ነው የተማርነው… ፐ! አለባበሱ… አረማመዱ… አወራሩ… በቃ ሁሉ ነገር የሚያምርበት ልጅ… በዛ ላይ ኩራቱ… ጉራውስ ብትል… በነገራችን ላይ፣ ጉረኛ ሰው በጣም ነው የምወደው…" ብለሽ የጎረርሽው… ጉራ የማልችል መስሎሽ እዳይሆንና እዳልጎርር…

ጉራ አሪፍነት መስሎሽ ከሆነ ተሸውደሻል… ጉረኛ ሰው የለየለት ቀጣፊ መሆኑን… ያልተፈጠረን የሚፈጥር፣ ያልሆነውን የሚሆን መሆኑን ካላወቀሽ… በቃ... ተሸውደሻል…

አንድ ነገር ልንገርሽ? አላዋጣ ብሎኝ ትቼው ነው እንጂ… በዚ ምድር ላይ… እንዲሁም በዛኛው… እንደኔ አይነት ቀጣፊና ጉረኛ ሰው አልነበረም… ደግሞ ይሄን ንግግር ጉራ እንዳታደርጊው…

"የተውኩትን ነገር ተመክሬ፣ ተነግሬ፣ ባገር…" አለች ዘፋኟ… በነገራችን ላይ ጨዋታን ጨዋታ ያመጣዋል የለ… ይሄን ግጥም ለጂጂ የሰጠኋት እኔ ነኝ? "እንዴት?" አትይም… ቀኑን በውል አላስታውሰውም… ያኔ ጉራ ስቸረችር ነው… ከተወሰኑ አርቲስቶች ጋር ሰብሰብ ብዬ (ይቅርታ ከበውኝ) እየተጨዋወትኩ… አንዱ አርቲስት… "አንተ በቃ ያለሹፌር አትንቀሳቀስም ማለት ነው? መኪና መንዳት እንዲህ ያስጠላህ?" ብሎ ሲጠይቀኝ "የተውኩትን ነገር…" ብዬ በዜማ ከመመለሴ… ጂጂ ቀለብ አድርጋ… "በናትህ ያሁኑን አባባል ከነዜማው ልዝፈነው ብላ እግሬ ላይ አትወድቅ መሰለሽ…" በቃ… ምና ላርግ… እንደዛ እግሬ ላይ ወድቃ ስትለምነኝ አሳዘነችኝ… በቃ ዝፈኚው አልኳት… ይኸው ታወቀችበት…

እናም… ወደ ጨዋታዬ ልመለስና… በቃ… ላንቺ ስል ጉረኛ ልሆን ነው… ለዛውም አንቱ የተባለ… እንደውም ድርጅት ከፍቼ… ጉራ ችርቸራ ትሪዲንግ የሚባል… በቃ… ከኔ አልፎ እንዳንቺ ጉራን ለሚፈልጉ እንስቶች… በብዛትና በጥራት፣ በጅምላና በችርቻሮ… በተመጣጣኝ ዋጋ አከፋፍላለው… በቃ… የጉራን ዋጋ ሰብሬ ገብቼ ቻይናን ሁላ ጉድ እሰራታለው… አገሩን በሙሉ ጉራ በጉራ አደርገዋለው… አጥለቀልቀዋለው… ከተማው ሁላ የኔን ጉራ ለብሶና ታጥቆ ሲዞር ታይዋለሽ… "ጉረኛ!" ነው ያልሽው? ጉራ አይደለም… አደርገዋለው!

በይ ወደ ገራዬ… ጊዜ የለኝም… የስድስቱ ፋብሪካዎቼን አጠቃላይ ሪፖርት ልሰማ ልሄድ ነው…

ስብሰባዬ ቃሊቲ ስለሆነ በፎር ዊል ድራይቬ ነው የምሄደው… "ኤጭ… ምን አይነት መንገድ ነው… ገና ከመስቀል ፍላወር መንገድ ሳልወጣ ሰዓቱ ሄደብኝ… ምን እንደሚያናድደኝ ታውቂያለሽ? 1ብር ለመልቀም ምድረ ታክሲ የኛን ሰዓት የሚሻማው ነገር… ደሞ በኛ አስፓልት… ነግሬሻለው? የመስቀል ፍላወር መንገድ የፋዘር እንደነበር? ምን ዋጋ አለው… መንግስት ወረሰብን… ልጅ እያለሁ ሳይክል የለመድኩት ሁላ እዚሁ መስመር ላይ ነው… ፋዘር መስመሩን ያዘጋውና ቀኑን ሙሉ ስነዳ እውላለው…"

ለነገሩ አሁንም ቢሆን መስመሩን ለማስመለስ በግሌ ፍርድ ቤት እየተከራከርኩ ነው… ያው እንደምታውቂው የዛሬ ዳኛ በትንሽ ሺ ብሮች ተደላይ ነው… ስለዚህ... የተወሰነች ብር በA3 ካኪ ፖስታ አሽጌ እሸጉጥላቸውና የቤተሰቦቼን ንብረት አስመልሳለው… ካልሆነም ከቤቴ እስከ ቃሊቲ የራሴን መንገድ አሰራና ታክሲ ዘጋብኝ አልዘጋብኝ ሳልል ቀብረር ብዬ እጓዛለው… የማሰራው መንገድ እራሱ ቀለበት መንገድ ነው… ይሄን ምድረ ታክሲና ቪትዝ ከላይ ሆኜ እንደ ቁጫጭ እያየሁ ለመሄድ… ቢበዛ መንግስት በአመት አንዴ የአፍሪካ ህብረት ተሰብሳቢዎችን እናጓጉዝበት ቢለኝ ነው… ያው በአመት አንዴ ብቸገር ነው…

በነገራችን ላይ… ከፈለግሽ… ከናንተ ቤት እስከ ዩኒቨርስቲው ያለውን መንገድም በግሌ አሰራልሻለው… ለዛውም በባለደረጃ አንዱ ተቋራጭ ድርጅቴ… ከታክሲ ጋር ምን አጋፋሽ… እነዛ ምስኪን ቤተሰቦችሽስ በስተርጅና ምን አጎሳቆላቸው… እነዛ አቃጣሪ ጓደኞሽም ቢሆን ማንነቴን ይወቀቱ… መቼም ይህን ለማድረግ በማሰቤ "ጉረኛ!" እንደማትይኝ ነው?

አንድ… እንድታውቂልኝ የምፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ይሄን ሁሉ ነገር የማደርገው ገንዘብ ተርፎኝ አይደለም… ለጉራም አይደለም… ስልጣኔን ለማሳየትም አይደለም… ጓደኞችሽ እንዲወዱኝ ብዬም አይደለም… ቤተሰቦችሽ እንዲያከብሩኝም አይደለም… አንቺ እንድትወጂኝም አይደለም… ለሌላ ለምንም አይደለም… ያው… ስለምወድሽ ነው፡፡






ፍቅርኛ


ፍቅር… ፍንቅር ቅር… ምንቅር ቅር… ፍር ፍር ፍር… ፍርቅቅቅ… ፍቅቅቅ…  ፍ-ቅ-ር-ዬ… የኔ ቆንጆ… (ፍቅርን የኔ ቆንጆ ያለ ብቸኛ ተብሎ ይያዝልኝ)… አቦ እንዴት አባቱ ደስ የሚል ነገር ነው-ፍቅር…

ኡፍፍፍ… በተለይ የኔና የሷ ፍቅር… የኔና የሷ ፍቅር እስከዛሬ ከተፃፈውም፣ ከተዘፈነውም፣ ከተተወነውም፣ ከተገጠመውም፣ ከተተረከውም በላይ ነው፡፡ ጉረኛ እንዳትሉኝ… እንዳትታበዩም… በቃ… ዝም ብላችሁ አንብቡ…

የኔና እሷ ፍቅር ከላይ እንዳልኳችሁም… እንዳላልኳችሁም ነው… ለዛም ነው… ስለኔና እሷ ፍቅር የማልፅፈው… ለዛም ነው ስለኔና እሷ ፍቅር የማልገጥመው… ሼክስፒር እንኳን በኛ ጊዜ ቢኖር የኔና እሷን ፍቅር እንዲፅፈው አልፈቅድለትም፡፡ ምክንያቱም የኔና እሷ ፍቅር ከቃላት በላይ ነው… የኔና እሷን ፍቅር ቃላቶች ያሳንሱታል እንጂ አይገልፁትም… እስኪ አሁን… ውብ… ገዳይ… ፈንዲሻ... አፍዝ… እንኮይ… ጥዝዝ… ጭርር… ብዝዝ… ምና ምን… ምና ምን… እያልኩ በየቀኑ አዳዲስ ስም የማወጣለትን ፈገግታዋን ሼክስፒር ምን ብሎ ይፅፈዋል?

ዛሬ የምታሳየኝ የፈገግታዋ ውበት ከትላንቱ የተለየ ነው… የጠዋቱ ከማታው… የማታው ከከሰዓቱ… ሁሉም የየራሱ ውበትና ትርጉም አለው… ታዲያ ሼክስፒር ይህን ፈገግታዋን ብቻ በአንድ መፅሀፍ ፅፎ ይጨርሰዋል? አይመስለኝም፡፡

በቃ… የኔና እሷ ፍቅር… ውይይይይ… ምን ልበላችሁ? ምንም ብላችሁ አልገልፀውም… ብገልፀውም አይገባችሁም… የኔና እሷን ፍቅር ሊገልፁት የሚችሉ ቢኖሩ እኔና እሷ ብቻ ነን፡፡ እኔና እሷም በፅሁፍና በወሬ ሳይሆን በመፋቀር ብቻ ነው የምንገልፀው… ፍቅርቅርቅር… እየተደራረግን… ውድድድድ… እየተደራረግን…  

የኔና እሷን ፍቅር ተቀርፆ ብታዩት እንኳን… ቋንቋው አይገባችሁም፡፡ ምክንያቱም… አንደኛ- ከምስልም ከድምፅም በላይ የሆኑ በአቅመ-ካሜራ የማይቀረፁ ነገሮች ስላሉት… ሁለተኛ- ቋንቋው እራሱ ፍቅርኛ ስለሆነ…

ፍቅርኛ ልዩ ቋንቋ ነው… በፍቅር ውስጥ ያሉ ጥንዶች ብቻ የሚፈጥሩት…  በፍቅር ውስጥ ያሉ ጥንዶች ብቻ የሚያወሩት… በፍቅር ውስጥ ያሉ ጥንዶች ብቻ የሚግባቡት ቋንቋ… ፍቅርኛ ጥንዶችን ብቻ የሚያግባባ ቋንቋ ነው ከሁለቱ ተፋቃሪዎች ውጪ ለሌላ ለማንም አይገባም… የአንዱ ጥንድ የፍቅር ቋንቋ ከሌላው የተለየ ነው… የኔና የእሷ ግን ከጥንዶች ሁሉ በፍፁም የተለየ ነው… እኔና እሷ በፍቅር ቋንቋ የረቀቅን ነን… ፍቅርኛን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደረግን… ለዚህም ነው የኔና እሷን ፍቅር ላወራውም፣ ልፅፈውም የማልችለው… ምክንያቱም… አይገባችሁም!  

"ግድየለህም!" ካላችሁኝ ግን ፅፌ ላሳያችሁ… ለምሳሌ ቀጣዩ ፅሁፍ እሷ እኔን "እወድሃለው" ስትለኝ ነው… "¤¥±ÐኊªፘÏዄ፨ጜ¤ፚፙዿ"    

እህስ?

አላልኳችሁም?

ዝም ብላችሁ ነው…


አይገባችሁም! 

ኑሮን ያስወደድከው አንተ ነህ!


ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው… ከኦሎምፒያ ወደ አጎና ሲናማ ለመሄድ በመከራ የተገኘች ሚኒ ባስ ውስጥ ለመግባት ሰዉ ይጋፋል… ምንም እንኳን ታሪፉ 1ብር ከ35 ቢሆንም ረዳቱ "ሁለት፣ ሁለት ብር ነው… ሰምታችኋል!" እያለ እያስጠነቀቀ በተገኘው ክፍት ቦታ ተሳፋሪውን ይጠቀጥቃል… እንደምንም ብዬ ታክሲው ውስጥ ከገባሁ በኋላ… የረዳቱን ማስጠንቀቂያ ማንም ቁም ነገሬ አለማለቱ በጣም አስገርሞኝ ለረዳቱና አብሮኝ ለነበረ ጓደኛዬ በሚሰማ ድምፅ… "ለምን ሲባል!" ብዬ አጉረመረምኩ… ተሟግቼም… "አንተ ከማን ትበልጣለህ…" ተብዬም ለኔና ለጓደኛዬ 2ብር ከ70 ከፈልኩ…

እዛው ታክሲ ውስጥ ሳለን… ጓደኛዬን እንዲህ አልኩት… "ኑሮን ግን ማን እንዳስወደደብን ታውቃለህ?" መልስ እስኪሰጠኝ አልጠበኩም… ንግግሬን ቀጠልኩ…

"ኑሮን ያስወደድነው እኛው እራሳችን ነን… አንተና እኔ!" ጓደኛዬ ጆሮውን ሰጠኝ… ቀጠልኩ…
"እዚህ ታክሲው ውስጥ ስንት አይነት ሰው ሊሳፈር እንደሚችል አስበኸዋል?"

"ለምሳሌ… ታክሲ ውስጥ ከተሳፈሩት አንዱ ዶክተር ነው እንበል… ይሄ ዶክተር ክሊኒክ አለውም ብለን እናስብ… ታዲያ… ባለ ታክሲውና ረዳቱ ስለመሸ ብለው 65ሳንቲም እዚህ ዶክተር ላይ ሲጨምሩበት… ዶክተሩ በተራው ወደ ክሊኒኩ ይገባና 50ብር የነበረውን የካርድ ማውጫ ዋጋ ከሁለት ሰዓት በኋላ 60ብር ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታላ!
ሌላም… የዳቦ ቤት ባለ ቤት የሆነ ግለሰብ እዚህ ታክሲ ውስጥ አለ እንበል… እሱም… ምናልባትም… ከሶስትና አራት ዳቦ የሚያተርፋትን 65ሳንቲም በትራንስፖርት ላይ ስለተጨመረበት እሷን ለማካካስ ሲል 1ብር የነበረውን ዳቦ 1ብር ከ10ሳንቲም ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታላ!

አንዷ ደግሞ እንጀራ ሻጭ ናት እንበል… 2ብር ከ50 ትሸጥ የነበረውን እንጀራ 2ብር ከ75 ታደርገዋለች… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮባታላ!

ሌላው ደግሞ ባለ ሱቅ ነው እንበል… 25ብር የነበረውን የስኳር ዋጋ 26 ብር ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታል!

እንዲሁም… ሌላኛው ተሳፋሪ ትምህርት ቤት አለው እንበል… ታዲያ ይሄ ግለሰብ… 150ብር የነበረውን ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያ 160ብር ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታል!
ሌላኛው… ባለ ስጋ ቤት ነው፣ ሌላው… ባለ ወፍጮ ቤት… ሌላው… እህል ነጋዴ… ሌላው…  አትክልት ነጋዴ… ሌላው… ባለ ምግብ ቤት… ሌላው… ጠበቃ… ሌላው… ጥበቃ… ሌላዋ የቤት ሰራተኛ… ሌላም… ሌላም…

ታዲያ ባለታክሲውና ረዳቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሆነው ሳሉ እነሱ በጨመሯት 65 ሳንቲም ምክንያት ህክምና ይጨምርባቸዋል፣ ዳቦ ይጨምርባቸዋል፣ እንጀራ ይጨምርባቸዋል፣ ስኳር ይጨምርባቸዋል… ሌላም… ሌላም…

ሾፌሩና ረዳቱ ዛሬ ማታ የለኮሷት ትንሽ ክብሪት ሌሊቱን ሙሉ ስትቀጣጠል አምሽታ… አንዱ፣ ለሌላው እያቀበላትና እየተቀባበላት አድራ በነጋታው ሰደድ እሳት ሆና እነሱኑ ትፈጃቸዋለች፡፡
የሚገርመው ነገር… ባለታክሲው ትርፍ የጫናቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 ሰዎችን ጭኗል እንበል… ታዲያ በ65ሳንቲሟ ተሰልቶ ዛሬ ማታ 13ብር አትረፎ ሊሆን ይችላል… ነገር ግን… በንጋታው… ከላይ ከጠቅስኳቸው፣ እሱ እራሱ ከሚጠቀማቸው አምስት አገልግሎቶች ብቻ 21ብር ከ35ሳንቲም ተጨማሪ ሊከፍል ግድ ይሆንበታል ማለት ነው፡፡

ወንድሜ ሆይ! ኑሮ ተወደደ እያልክ እያማረርክ ነው? እኔ ግን አንድ ነገር ልንገርህ… ኑሮን ያስወደደው ማንም ሳይሆን… አንተው እራስህ ነህ!

አንቺ እህቴስ! ኑሮ ንሮብሻል? እንግዲያውስ አንድ ነገር ልምከርሽ… ኑሮሽ የተወደደው አንቺ በወደድሽው ልክ ነው… አንቺ በመረጥሽውና በፈቀድሽው ልክ… ኑሮሽ የተወደደው ያለ በቂ ምክንያት 70ሳንቲም ሳታንገራግሪ የጨመርሽ ጊዜ ነው… ኑሮሽ የተወደደው የጋገርሽው እንጀራ ላይ ያለ አግባብ ዋጋ የጨመርሽ ጊዜ ነው… ኑሮሽ የተወደደው የጋገርሽው አምባሻ ላይ የተጋነነ ዋጋ የጨመርሽ ጊዜ ነው… ኑሮሽ የተወደደው ከጓሮሽ ያበቀልሽው ጎመን ላይ የማይገባ ዋጋ የጫንሽ ጊዜ ነው…

አንተ ኑሮ የተወደደብህ፣ አንቺ ኑሮ የተወደደብሽ… ያልተረዳኸው፣ ያልተረዳሽው ነገር ቢኖር ህይወት የቅብብሎሽ ሰንሰለት መሆኗን ነው… ኑሮ የገዢና የሻጭ፣ የአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ ቀለበት መሆኗን ነው… ታዲያ! ዛሬ በሌላው ላይ የወረወረከው ጠጠር ነገ ከሌሎች ጠጠሮች ጋር ተደማምሮ አንተ ላይ ከባድ አለት ሆኖ ይመጣብሃል… የማትሸከመው ቀንበር ይሆንብሃል… አንገትህን ያስደፋሃል… አንተ ዛሬ የከፈትካት ቀዳዳ ነገ በሌሎች ሰፍታ የአውሬዎች ሲሳይ ታደርግሃለች… አንተ ዛሬ የፈጠርካት ጠብታ ነገ ጎርፍ ሆና ይዛህ ትሄዳለች…

ታዲያ ያኔ ማን ላይ ልታላክክ ነው? መንግስት ላይ? ባለ ሃብት ላይ? ነጋዴ ላይ? ገበሬ ላይ? እኔ ግን ልምከረህ… የመንግስትም፣ የነጋዴም፣ የገበሬም፣ የመምህርም፣ የአስተማሪም፣ ስልጣን ሰጪና ነፋጊ አንተ ነህ! ማንም የሚገዛህም ሆነ የሚሸጥልህ አንተ በሰጠኸው ዋጋና ተመን ልክ ነው፡፡ እሱ ያወጣው ዋጋ ካልተስማማህ እያጉረመረምክ አትግዛ! ይልቁንም በኢትዮጲያዊ ቆራጥነት ቆፍጠን ብለህ… "አልገዛህም!" በለው ያኔ እሱም የሚገዛው ነገር አለና ብር ስለሚያስፈልገው አንተ በተመንክለት ዋጋ ይሸጥልሃል…

ምናልባት… ዛሬ የተጣለችብህን ጭማሬ የመግዛት አቅሙ ስላለህ ከመጨቃጨቅ ብለህ ጭማሬዋን ከፍለህ ልትሄድ ትችላለህ… ነገር ግን ካንተ በታች ያለውን ወንድምህን ደግሞ አስብ!

አንተ ዛሬ ለደካማው ወንድምህ ዘብ ካልቆምክለት፣ ነገ… ትላንት የናቅካት ጭማሪ አንተው ላይ እጥፍ ሆና ስትመጣብህ ማን ከጎንህ ሊቆም ነው? ስለዚህ… አንድ ነገር ተረዳ… የማንኛውም ነገር አስጨማሪም ጨማሪም አንተ ነህ! ኑሮህን ያስወደድከው አንተው እራስህ ነህ!