Wednesday, August 14, 2013

ኑሮን ያስወደድከው አንተ ነህ!


ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው… ከኦሎምፒያ ወደ አጎና ሲናማ ለመሄድ በመከራ የተገኘች ሚኒ ባስ ውስጥ ለመግባት ሰዉ ይጋፋል… ምንም እንኳን ታሪፉ 1ብር ከ35 ቢሆንም ረዳቱ "ሁለት፣ ሁለት ብር ነው… ሰምታችኋል!" እያለ እያስጠነቀቀ በተገኘው ክፍት ቦታ ተሳፋሪውን ይጠቀጥቃል… እንደምንም ብዬ ታክሲው ውስጥ ከገባሁ በኋላ… የረዳቱን ማስጠንቀቂያ ማንም ቁም ነገሬ አለማለቱ በጣም አስገርሞኝ ለረዳቱና አብሮኝ ለነበረ ጓደኛዬ በሚሰማ ድምፅ… "ለምን ሲባል!" ብዬ አጉረመረምኩ… ተሟግቼም… "አንተ ከማን ትበልጣለህ…" ተብዬም ለኔና ለጓደኛዬ 2ብር ከ70 ከፈልኩ…

እዛው ታክሲ ውስጥ ሳለን… ጓደኛዬን እንዲህ አልኩት… "ኑሮን ግን ማን እንዳስወደደብን ታውቃለህ?" መልስ እስኪሰጠኝ አልጠበኩም… ንግግሬን ቀጠልኩ…

"ኑሮን ያስወደድነው እኛው እራሳችን ነን… አንተና እኔ!" ጓደኛዬ ጆሮውን ሰጠኝ… ቀጠልኩ…
"እዚህ ታክሲው ውስጥ ስንት አይነት ሰው ሊሳፈር እንደሚችል አስበኸዋል?"

"ለምሳሌ… ታክሲ ውስጥ ከተሳፈሩት አንዱ ዶክተር ነው እንበል… ይሄ ዶክተር ክሊኒክ አለውም ብለን እናስብ… ታዲያ… ባለ ታክሲውና ረዳቱ ስለመሸ ብለው 65ሳንቲም እዚህ ዶክተር ላይ ሲጨምሩበት… ዶክተሩ በተራው ወደ ክሊኒኩ ይገባና 50ብር የነበረውን የካርድ ማውጫ ዋጋ ከሁለት ሰዓት በኋላ 60ብር ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታላ!
ሌላም… የዳቦ ቤት ባለ ቤት የሆነ ግለሰብ እዚህ ታክሲ ውስጥ አለ እንበል… እሱም… ምናልባትም… ከሶስትና አራት ዳቦ የሚያተርፋትን 65ሳንቲም በትራንስፖርት ላይ ስለተጨመረበት እሷን ለማካካስ ሲል 1ብር የነበረውን ዳቦ 1ብር ከ10ሳንቲም ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታላ!

አንዷ ደግሞ እንጀራ ሻጭ ናት እንበል… 2ብር ከ50 ትሸጥ የነበረውን እንጀራ 2ብር ከ75 ታደርገዋለች… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮባታላ!

ሌላው ደግሞ ባለ ሱቅ ነው እንበል… 25ብር የነበረውን የስኳር ዋጋ 26 ብር ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታል!

እንዲሁም… ሌላኛው ተሳፋሪ ትምህርት ቤት አለው እንበል… ታዲያ ይሄ ግለሰብ… 150ብር የነበረውን ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያ 160ብር ያደርገዋል… ምክንያቱም የታክሲ ዋጋ ጨምሮበታል!
ሌላኛው… ባለ ስጋ ቤት ነው፣ ሌላው… ባለ ወፍጮ ቤት… ሌላው… እህል ነጋዴ… ሌላው…  አትክልት ነጋዴ… ሌላው… ባለ ምግብ ቤት… ሌላው… ጠበቃ… ሌላው… ጥበቃ… ሌላዋ የቤት ሰራተኛ… ሌላም… ሌላም…

ታዲያ ባለታክሲውና ረዳቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሆነው ሳሉ እነሱ በጨመሯት 65 ሳንቲም ምክንያት ህክምና ይጨምርባቸዋል፣ ዳቦ ይጨምርባቸዋል፣ እንጀራ ይጨምርባቸዋል፣ ስኳር ይጨምርባቸዋል… ሌላም… ሌላም…

ሾፌሩና ረዳቱ ዛሬ ማታ የለኮሷት ትንሽ ክብሪት ሌሊቱን ሙሉ ስትቀጣጠል አምሽታ… አንዱ፣ ለሌላው እያቀበላትና እየተቀባበላት አድራ በነጋታው ሰደድ እሳት ሆና እነሱኑ ትፈጃቸዋለች፡፡
የሚገርመው ነገር… ባለታክሲው ትርፍ የጫናቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 ሰዎችን ጭኗል እንበል… ታዲያ በ65ሳንቲሟ ተሰልቶ ዛሬ ማታ 13ብር አትረፎ ሊሆን ይችላል… ነገር ግን… በንጋታው… ከላይ ከጠቅስኳቸው፣ እሱ እራሱ ከሚጠቀማቸው አምስት አገልግሎቶች ብቻ 21ብር ከ35ሳንቲም ተጨማሪ ሊከፍል ግድ ይሆንበታል ማለት ነው፡፡

ወንድሜ ሆይ! ኑሮ ተወደደ እያልክ እያማረርክ ነው? እኔ ግን አንድ ነገር ልንገርህ… ኑሮን ያስወደደው ማንም ሳይሆን… አንተው እራስህ ነህ!

አንቺ እህቴስ! ኑሮ ንሮብሻል? እንግዲያውስ አንድ ነገር ልምከርሽ… ኑሮሽ የተወደደው አንቺ በወደድሽው ልክ ነው… አንቺ በመረጥሽውና በፈቀድሽው ልክ… ኑሮሽ የተወደደው ያለ በቂ ምክንያት 70ሳንቲም ሳታንገራግሪ የጨመርሽ ጊዜ ነው… ኑሮሽ የተወደደው የጋገርሽው እንጀራ ላይ ያለ አግባብ ዋጋ የጨመርሽ ጊዜ ነው… ኑሮሽ የተወደደው የጋገርሽው አምባሻ ላይ የተጋነነ ዋጋ የጨመርሽ ጊዜ ነው… ኑሮሽ የተወደደው ከጓሮሽ ያበቀልሽው ጎመን ላይ የማይገባ ዋጋ የጫንሽ ጊዜ ነው…

አንተ ኑሮ የተወደደብህ፣ አንቺ ኑሮ የተወደደብሽ… ያልተረዳኸው፣ ያልተረዳሽው ነገር ቢኖር ህይወት የቅብብሎሽ ሰንሰለት መሆኗን ነው… ኑሮ የገዢና የሻጭ፣ የአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ ቀለበት መሆኗን ነው… ታዲያ! ዛሬ በሌላው ላይ የወረወረከው ጠጠር ነገ ከሌሎች ጠጠሮች ጋር ተደማምሮ አንተ ላይ ከባድ አለት ሆኖ ይመጣብሃል… የማትሸከመው ቀንበር ይሆንብሃል… አንገትህን ያስደፋሃል… አንተ ዛሬ የከፈትካት ቀዳዳ ነገ በሌሎች ሰፍታ የአውሬዎች ሲሳይ ታደርግሃለች… አንተ ዛሬ የፈጠርካት ጠብታ ነገ ጎርፍ ሆና ይዛህ ትሄዳለች…

ታዲያ ያኔ ማን ላይ ልታላክክ ነው? መንግስት ላይ? ባለ ሃብት ላይ? ነጋዴ ላይ? ገበሬ ላይ? እኔ ግን ልምከረህ… የመንግስትም፣ የነጋዴም፣ የገበሬም፣ የመምህርም፣ የአስተማሪም፣ ስልጣን ሰጪና ነፋጊ አንተ ነህ! ማንም የሚገዛህም ሆነ የሚሸጥልህ አንተ በሰጠኸው ዋጋና ተመን ልክ ነው፡፡ እሱ ያወጣው ዋጋ ካልተስማማህ እያጉረመረምክ አትግዛ! ይልቁንም በኢትዮጲያዊ ቆራጥነት ቆፍጠን ብለህ… "አልገዛህም!" በለው ያኔ እሱም የሚገዛው ነገር አለና ብር ስለሚያስፈልገው አንተ በተመንክለት ዋጋ ይሸጥልሃል…

ምናልባት… ዛሬ የተጣለችብህን ጭማሬ የመግዛት አቅሙ ስላለህ ከመጨቃጨቅ ብለህ ጭማሬዋን ከፍለህ ልትሄድ ትችላለህ… ነገር ግን ካንተ በታች ያለውን ወንድምህን ደግሞ አስብ!

አንተ ዛሬ ለደካማው ወንድምህ ዘብ ካልቆምክለት፣ ነገ… ትላንት የናቅካት ጭማሪ አንተው ላይ እጥፍ ሆና ስትመጣብህ ማን ከጎንህ ሊቆም ነው? ስለዚህ… አንድ ነገር ተረዳ… የማንኛውም ነገር አስጨማሪም ጨማሪም አንተ ነህ! ኑሮህን ያስወደድከው አንተው እራስህ ነህ!                          

No comments:

Post a Comment