Sunday, May 20, 2012

የወሮታን ዋጋ ለሚነግረኝ ወሮታውን እከፍላለው

እንደ ጀማሪ ወገኛነቴ ለሲኒየር ወገኞች ወይም ባጠቃላይ ለፀሃፊዎች አንድ ጥያቄ አለችኝ፣ የአምስት መቶ ብር አልላችሁም፣ ምክንያቱም ለአንድ ጥያቄ አምስት መቶ ብር ካወጣሁ እንደኔ ጥያቄ አወዳደድ በጥያቄ ውዝፍ ዕዳ ልጠየቅ ነዋ፡፡ ለማንኛውም እጅ ሳታወጡ የምትመልሷት አንድ ጥያቄ እነሆ፤ "ውድ ወገኞች፣ እንዲሁም ፀሃፊያን፣ ስለ አንድ ነገር ለመፃፍ ስትነሱ መጀመሪያ የሚመጣላችሁ ምንድን ነው?" ርዕሱ ወይስ የፅሁፉ ሀሳብ(idea)?"

በበኩሌ የሆነ ወሬ ስሰማ ወይም ክስተት ስመለከት ጉዳዩን በምን መልኩ አልያም ከምን ዕይታ መፃፍ እንዳለብኝ ከማሰብ ይልቅ በቀጥታ ጉዳዩን የሚገልፅ ርዕስ ከተፍ እያለብኝ ተቸግሬያለው፤ በቃ ምን አለፋችሁ ምርጥ ምርጥ ቀልብና ልብ የሚገዙ ርዕሶች ከች ይሉልኛል፤ ከዛ ፅሁፉ ይጀመራል፡፡
ኤጭ! ‘ልብ የሚገዙ ርዕሶች’ የምትለው ሀረግ ምሬቴን አስታወሰችኝ፣ የምን? አትልኙም፣ ኑሮ እንዲህ ሰማይ ሳይሆን ጠፈር በነካበት በአሁኑ ወቅት ሁሉን ነገር ገዝተን እንዴት እንደምንዘልቀው ማሰቡ እንቆቅልሽ፤ ሂሳቡ ደግሞ እንቁልልጭ ሆኖብኛል፡፡ እውነቴን እኮ ነው፤ እንጀራ ገዝተን፣ ዳቦ ገዝተን፣ ውሃ ገዝተን፣ ጋዜጣ ገዝተን፣ ልብ ገዝተን፣ ቀልብ ገዝተን፣ ፀባይ ገዝተን፣ አደብ ገዝተን… ይሄ ሁሉ ሳያንስ ደግሞ እንደገና በስንቱ ተገዝተን እንደምንዘልቀው እንጃ፡፡   
ለማንኛውም ከግዢና ገዢ ርዕሴ ልውጣና ጥያቄ እንድጠይቅ ወዳስገደደኝ ጉዳዬ ልመለስ፤ እንዳልኳችሁ ይሄ ዝምብሎ ርዕሶች ከች የሚሉብኝ ልክፍት ከጀማመረኝ ቆይቷል፤ እንደውም ስገምት የፀሃፊነት ሞራሌ ከች ካለ ጊዜ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ በሽታ ይመስለኛል፤ እናም ይሄ ልክፍት ወይም እስካሁን ስሙን በውል ያላወኩት ደዌ በጣም እያሳሰበኝ በመምጣቱ ጉዳዩ ከሥነ-ልቦና ጋር ተያያዥነት ካለው ብዬ አንድ የሥነ-ልቦና ባለሙያ የሆነ ጓደኛዬን አማከርኩት፤ ሲያቀብጠኝ፡፡ ቅብጠትን ምን አመጣው አትሉኝም? ይሄ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ጓደኛዬ ሁሉ ነገር ከሥነ-ልቦና ጋር ይያያዛል የሚል አጉል ብሂል አለው፡፡
እንደሱ አመለካከት ሳይንስ ከሥነ-ልቦና ጋር ግንኙነት አለው፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ትዳር፣ ዕድር፣ ብድር፣ ድርድር… በቃ ምን አለፋችሁ ለእርሱ ሁሉ ነገር ምንጩ ሥነ-ልቦናዊ ነው፤ ልክ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪዎች man is a political animal (ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው) እንደሚሉት አይነት፡፡
ታዲያ በዚያች በተለመደች በምሁራዊ ሙከራ -1- -2- -3- አኳኋን ጉሮሮውን ካፀዳዳ በኋላ "ባይ ዘ ዌይ, ይሄ ጉዳይ ሥነ-ልቦናዊ ሂደት ነው፤ ነገርዬው ጥልቅ ሥነ-ልቦናዊ ዕውቀት ስለሚጠይቅ ላንተ የሚገባህ አይደለም ግን እንደው ባጠቃላይ ለማስቀመጥ ያህል…" ይህቺን አረፍተነገር ተናግሮ  በአፍንጫው በኩል በፍጥነት አየር ወደ ውስጥ ከሳበ በኋላ ለአፍታ ዝም ካለ እሱ እራሱ በውል ስለማያውቀው ነገር እየፈጠረ ሊቀበጣጥር እንደሆነ ስለምረዳ ንግግሩን አላስጨርሰውም፡፡ "አይ! እንዲገባኝ አሳጥረው" እለዋለው፤ "ኦኬ! እእእ… ይህን አይነቱን አእምሯዊ የሥነ-ልቦና ሂደት ርዕሰ-ቃርሞ እንለዋለን፤ ርዕስ መቃረም፣ መፈለግ፣ መሻት እንደማለት ሲሆን፤ ይህም የሚያሳየን የአስተሳሰብ ጅማሯችንን ነው፤ ግማሹ ከቁንፅል በመጀመር ሰፋ ወዳለው ነገር የማሰብ ሂደት ሲከተል ሌላው ሰፋና ብትንትን ካለ ሃሳብ በመጀመር…" ወሬውም እንደ ሃሳቡ የተበታተነና ምሁር ለመምሰል በሚፈጣጥራቸው አዳዲስ ጥንድ ቃላቶች የተሞላ ነው፤ ልክ እንደ ርዕሰ-ቃርሞ አይነት፡፡
ብዙውን ጊዜ ወሬው እንደ ካስትሮ ለሰአታት ስለማይቋረጥ ፍሬ ሃሳቡ ሳይገባኝ በሃሳብ ሽው እላለው፤ እንደውም እሱ አማራሪ ምሁራዊ ዲስኩሩን እየደሰኮረ አንድ ሶስት ቀሽት ቀሽት ርዕሶች ሁላ ከች ይሉልኛል፤ ታዲያ በዚህ የተነሳ እኔና ሌሎች ጓደኞቼ ይሄን ጓደኛችንን የሥነ-ልቦና ባለሙያ ሳይሆን የሥነ-ልቦና ካውያ እያልን ነው በድብቅ የምንጠራው፡፡  
ለዚህም ነው፣ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ማለቴ ካውያው ጓደኛዬ ምክርና ትንተና ብዙም ስላልገባኝ፤ እንዲሁም የጓደኛ ምክር ከመስማት ከባለሙያ ጋር በዋጋ መስማማት ብዬ የሙያ አጋሮቼን በሚገባኝ ቋንቋ ለ‘ርዕሰ-ቃርሞ’ በሽታዬ ማብራሪያ እንዲሰጡኝ በሚል ዋጋው ያልተጠቀሰ ጥያቄ ለወጊያን ወይም ፀሀፊያን የሰነዘርኩት፡፡
ባይሆን የሙያ አጋሮቼ ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ በቋሚነት የምሰራበት ቢሮ ያለ አንድ የስራ ባልደረባዬ ዘውትር የሚለንን ነገር ላጫውታችሁ፣ ልጁ የሙዚቃ ተሰጥዖ የለው በመሆኑ እንደ ሙያው የሚያየው ሙዚቃን ነው ታዲያ እኛን የቢሮ ባልደረቦቹን ሲጠራን የመዋያ አጋሮቼ እያለ ነው፤ ምክንያቱም እሱ ሙያዬ ብሎ የሚያስበው ሙዚቃን በመሆኑ የሙያ አጋሮቹ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ እኔም ፀሃፊያንን የሙያ አጋሮቼ ስል ታዲያ ከላይ ባጫወትኳችሁ አይነት ትርጉዋሜ ነው፡፡
እርግጥ ነው በአሁኑ ሰዓት ሰዉ በአረንጓዴኛ ማሰብ ስለመጀመረ (በብር ማለቴ ነው፤ በመቶ) የጥያቄዬን ዋጋ ከመናገር እንዲያው በደፈናው ሁነኛ ምላሽ ለሰጠኝ ወረታውን እከፍላሁ ብል ሳይሻል አይቀርም፡፡
በነገራችን ታች (ሁሌ በነገራችን ላይ ስለሚባል ለለውጥ ብዬ ነው) የመጨረሻዋ አረፍተነገር ወደ ዛሬዋ ወግ ትወስደናለች፤ አንከባላ፡፡ መቼም አንደርድራ አልላችሁም እስከሁን በረባ ባልረባ ወሬ ስነተርካችሁ ቆይቼ፡፡
የዛሬው ወጌ በዋናነት ርዕሱን የቃረመው ከመጥፋት ጋር በተያያዘ የምንጠቀምበትን ዋጋው በውል ያልታወቀ ወዘልማዳዊ የብር ኖትን (‘ወሮታ’) በተመለከተ ነው፡፡ ስለ ወሮታ እያሰብኩ ብዙ ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ ተመላለሱብኝ፤ ግን ‘ወሮታ’ ምን ማለት ነው? ዋጋውስ ስንት ነው? (ማሳሰቢያ፡- እነዚህ ጥያቄዎች ምናባዊ በመሆናቸው ሙሉ ለሙሉ ከክፍያም ሆነ ከወሮታ ነፃ ናቸው፡፡)
አስተውላችሁ ከሆነ፣ ይህችን ቃል በተደጋጋሚ የምንጠቀምባት ወይ ሰው አልያም ዕቃ ሲጠፋን በአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ነው፤ ብዙዎቻችን በቃላችን እስክንሸመድዳቸው ድረስ በየግድግዳው ተለጥፈው ወይም በሬዲዮኖች እየተነገሩ፤ እንደዚህ፡ "አቶ/ወ/ሪት/ወ/ሮ እገሌ የተባልኩ የመንጃ ፈቃዴ፣ ፓስፖርቴና ሌሎችም በጣም አስፈላጊ ዶክመንቶች ስለጠፉብኝ ዶክመንቶቹን አግኝታችሁ ለምትደውሉልኝ ‘ወሮታ’ውን እከፍላለሁ" አልያም ደግሞ "አቶ እገሌ የሚባሉ ሰው በእንትን ቀን እንትን ለብሰው እንደወጡ ስላልተመለሱ፣ ያሉበትን የሚያውቅ ወይም የሰማ በሚከተሉት ስልክ ቁጥሮች ደውሎ ቢያሳውቀን ወሮታውን እንከፍላለን፤ ፈላጊ፡ አፋላጊ ዶት ኮም፡፡" (በነገራችን ላይ ሰሞኑን በአንዳንድ ፎቆች ላይ አፋላጊ የሚሉ የኤቲም ማሽን የሚመስሉትን የቁም ሳጥኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይ ዕቃና የጠፋ ሰው አፋላጊ በወሮታ የሚሰሩ ማሽኖች መስለውኝ ነበር፤ በዚህ አጋጣሚ አሪፍ የቢዝነስ አይዲያ ጠቆምኳቸው አይደል? መቼም ይሄ ስራ ከተጀመረ ፓተንቱን በእናንተ በአንባቢዬቼ ምስክርነት ለግሌ በማድረግ ቁጭ ብዬ እንደምጦር ነው፡፡)
ቆይ ግን ለመሆኑ ከወሮታ ላይ መንግስት ግብር ይቆርጣል እንዴ? የወሮታ-ግብር ምናምን የሚባል ነገር እስካሁን አልሰማችሁም? በሉ ከአሁን በኋላ ትሰማላችሁ፤ መንግስት ጆሮው ብዙ ነው ይባል የለ፤ አይኑም እንደ ጆሮው ብዙ ከሆነ ይህች ፅሁፍ ከተነበበች ቀን ጀምሮ ይታሰብበታል ማለት ነው፤ ከሰሞኑ አዋጅ ጠብቁ፡፡ እንደው ያድርገውና/አያድርገውና/ የወሮታ-ግብር ከተጀመረ የወሮታ-ግብር አጭበርባሪዎች ፍ/ቤቶቻችንን ሊያጨናንቁት ነው ማለት ነው፡፡ ለነገሩም ወሮታ ዋጋው ስንት እንደሆነ በውል ባለመታወቁ ለማጭበርበር ያመቻል፡፡
ቆይ ግን አቶ እገሌን (እንደውም ለምሳሌ እንዲመች አቶ ወሮታው የሚባሉ የጠፉ አዛውንት) አግኝቼ  ወሮታዬን ልቀበል ሄድኩኝ፤ መቼም ወሮታው በአርንጓዴኛ ነው የሚከፈለኝ ብዬ በማሰብ፤ ይሄኔ አፋላጊዎቹ አቶ ወሮታውን አቅፈውና ስመው ተቀብለው እኔንም ቤታቸው ወስደው በሻይና በምርቃት ቢያሰናብቱኝ ወሮታዬን አልሰጡኝም ብዬ መክሰስ እችል ይሆን? ወይስ ልክ እንደ ደሞዝ በስምምነት ወሮታም በስምምነት ነው?
የሚገርመው ነገር ይቺ ርዕስ ከተፍ እስክትልልኝ ድረስ እኔም እራሴ የወሮታ ቀንደኛ ተጠቃሚ የነበርኩ መሆኔ ነው፤ እንደውም በቅርብ የማስታውሰው አንድ አጋጣሚዬን ላጫውታችሁ፡ ለብዙ አመታት ስጠቀምበት የነበረውን የፖስታ ሳጥን ኪራዬን ለመክፈል ወደ ፖስታ ቤት አቀናሁ፤ ከረጅም ጊዜ በኋላ፤ ኮራ-ቀብረር ብዬ፣ ቱታ ለብሼ (ፈታ ብዬ ለማለት ነው እንጂ እሱስ ጅንስ ነበር የለበስኩት፤ በነገራችን ላይ ይህቺ ቃል ሰሞነኛ ናት ‘ቱታ ልበስ’ ፈታ በል እንደማለት ነው ትርጉሟ)
እናላችሁ የሳጥን ኪራይ ሰብሳቢውን ቀረብ ብዬ የመጣሁበትን ጉዳይ ስነግረው የሳጥን ቁጥሬንና መታወቂያዬን ጠየቀኝ፤ እንደተለመደው ኮራ ቀብረር ብዬ ቁጥሬንና መታወቂያዬን ሰጠሁት፡፡ ሰውዬው ፋይሌን ከብረት መሳብያው ውስጥ ፈልጎ ካወጣ በኋላ "አዝናለው የሳጥን ኪራይህን በወቅቱ ባለመክፈልህ ለሌላ ደንበኛ አከራይተነዋል፤ ሌላ ሳጥን የምትፈልግ ከሆነ ክፍት ሳጥኖች ስላሉ እዛ ጋር ያለውን ፎርም ሞልተህ አምጣ" በማለት ወደ ስራው ተመለሰ እኔም በሳጥን ደንበኝነት እድሜዬ ልክ ካጉረመረምኩና ከተነጫነጭኩ በኋላ ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ የአዲስ ሳጥን ፎርም ሞልቼ ቁልፍ ከተቀበልኩ በኋላ ለቀድሞው እኔ ለአሁኑ እገሌ/ሊት (የቀድሞው ሳጥኔ አዲሱ ባለቤት) የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፍኩ፡
፡ አዲሱ የቀድሞ ሳጥኔ ባለቤት
፡ ቀድሞው የሳጥንህ ባለቤት
ለተከበርከው አዲሱ የቀድሞ ሳጥኔ ባለቤት እኔ ከሞቀችው ከቀድሞ ሳጥኔ ሃሳብና ናፍቆት በስተቀር በጣም ደህና ነኝ፤ አንተስ የቀድሞ ሳጥኔን ካገኝህ በኋላ ጤናህ እንዴት ነው? የሞቀችው ሳጥኔ ተስማምታህ ይሆን?
ወደ ፍሬ ሃሳቤ ስገባ አሁን እየተጠቀምክበት ያለውን ሳጥን ከዚህ ቀደም እኔ በስስትና በጉጉት እየዳበስኩ ስከፍተው የደብዳቤዎች ናዳ ወደ መሬት ይጎርፍ ነበር፡፡ እናም ይህ አንዳችም ሳላጋንን ያቀረብኩት የደብዳቤ ፍሰት በቀጣይ ወደ አንተ መጉረፉ የማይቀር ነውና አዲሱ ሳጥኔ እስኪለምድና እስኪሞቅ ድረስ በቀድሞ ሳጥኔ የሚላኩ ደብዳቤዎችን በሙሉ ወደዚህኛው ሳጥኔ(አዲሱን ቁጥሬን በመግለፅ) ብትልክልኝ ወሮታውን እከፍላለሁ፤ በማለት፡፡
ከዛም ትንሽ ከረምረም ብዬ በአዲሱ ሳጥኔ ከቀድሞው ሳጥኔ መልክቶች እንደተላኩልኝ ለማዬት ወደ ፖስታ ቤት ጎራ ብልም አዲሷ ሳጥኔ ኦና ሆና አገኘኋት፡፡ ግን እንደው ያድርገውና/አያድርገውና/ አዲሱ የቀድሞ ሳጥኔ ባለቤት በቀድሞው ሳጥኔ የተላኩትን ፖስታዎች ወደ አዲሱ ቁጥሬ ልኮልኝ ቢሆን ኖሮ ምን አይነት ወሮታ ነበር የምከፍለው? የማውቀው ነገር ቢኖር እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ወሮታ ምን እንደሆነ በአግባቡ አለማውቄን ነው፡፡ እንደኔ ደብዳቤ ይዘት ከሆነ ልክ ደብዳቤ ተፅፎ ሲያልቅ ከሰላምታ ጋር ከማለት ባልተናነሰ ሁኔታ ነው ወሮታውን እከፍላለሁን የተጠቀምኩበት፡፡ ለማንኛውም፣ ትርጉሙ ሲገባኝ የምከፍለው ወሮታ ስላለበኝ ፅሁፌን በዚህ ላብቃ፤ ከሰላምታ ጋር!   
       
     

ወፍ የለም!


ቋንቋ ይፈጠራል፣ ይስፋፋል፣ ይለመዳል!

ቋንቋ ምንድን ነው? ብዬ ስጠይቅ፣ ቋንቋ መግባቢያ ነው የምትል ቅልብጭ ያለች ግና ውስጠ-ወይራ የሆነች መልስ አገኘው፤ እናም እንደገና ጠየኩ፣ አውን ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ነው? ስል፤ ምክንያቱም አሁን አሁን የምሰማቸው መጤ ቃላቶችና ሀረጎች የቋንቋን መግባቢያነት ሳይሆን ይልቁኑም ግራ-ማጋቢያነት ማሳያ በመሆናቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ትርጉሟ በደፈናው ቋንቋ ማግባቢያ ነው አለች እንጂ ግራ ይሁን ቀኝ በውል አልጠቀሰችም፤ ለዚህም ይመስላል እንደፈለግነው ግራም ቀኝም የምናንቋቋው/ቋንቋን/፡፡

ቋንቋ ሆሄያት፣ ወደ ቃል፣ ቃላት ወደ ሀረግ፣ ሀረጎች ወደ አረፍተነገር፣ አረፍተነገሮች ወደ አንቀፅ… የሚቀጣጠሉበት ተራ የድምፀት እርባታ ብቻ ሳይሆን የዚያን የተናጋሪውን ማህበረሰብ እሴቶች፣ ባህል፣ ስነምግባራት፣ ትውፊቶች፣ ወዘተ ማሳየት የሚችል እምቅ ሀይል አለው፡፡
በነገራችን ላይ ቋንቋ የስልጣኔን ደረጃም የማሳየት ብቃት አለው ብዬ በግሌ አምናለው እንዴት ማለት መልካም፣ ጉዳዩ ሰፊ ጥናትን ሊጠይቅ የሚችል፣ ምናልባትም ተጠንቶበት ሊሆን የሚችል ነው፤ ቲየሪው የመጣልኝ በስልጣኔ ዙሪያ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በስፋት አያወጋን በነበረበት ወቅት ነው እናም የሚከተለውን ዲስኩር ደሰኮርኩለት፤
"…እኛ ኢትዮጲያዊያን እኮ በብዙ ነገር ግንባር ቀደም ከሚባሉ አገራት ተርታ የምንመደብ ነን ለምሳሌ ብትወስድ የራሳችን ፊደል ያለን ነን፡፡ ዳሩ ምን ዋጋ አለው ፊደላቶቻችን እራሳቸው የአስተሳሰባችንን ሲምፕልነት ያሳያሉ፤ አብዛኞቹ ፊደሎች ቅርፃቸው ቀላል ነው፣ የሁለትና በዛ ቢባል የአራት መስመሮች ውህደት ለምሳሌ ውሰድ - ሀ፣ ተ፣ በ፣ ቸ፣ ፐ… እንደው ትንሽ ለማወሳሰብ ስንሞክር ቀለበት ይጨመርባቸዋል - ዐ፣ ወ፣ ቀ፣ ጨ… በአንፃሩ እነ ቻይና፣ ህንድ፣ እንዲሁም እስራኤልን እንደምሳሌ ውሰድ ፊደላቶቻቸው እንደመንገዶቻቸው እርስ በእርሳቸው የተጠላለፉ ስዕል የሚመስሉ ናቸው፡፡ ይህም የአእምሮ ብቃታቸውን የሚያሳይ አንዳች ነገር ነው ብዬ አስባለው፡፡ ቅም-ቅም አያቶቻችን የዋህና ቀጥተኞች ስለነበሩ ምን ነገር አወሳሰበን ብለው ነው -ሀ- እና -ፐ-ን የፈጠሩት ትለኝ ይሆናል፤ እኔ ግን የሚሰማኝ አእምሯቸው እስከዛ ድረስ ብቻ ማሰቡ ወይም ስንፍናቸው ነው፤ የዋህ እና ቀጥተኛ ቢሆኑ ኖሮማ ቅኔ የሚባል ነገር ባልፈጠሩ፡፡
እውነቴን እኮ ነው እነ ቻይና በአሁኑ ሰዓት በስልጣኔውም በኢኮኖሚውም አሉ ከሚባሉ አገራት ተርታ የሚመደቡ ናቸው፤ ታዲያ ይህ የስልጣኔ ደረጃ እነዚህ አገራት በአጋጣሚ የደረሱበት እኛ ደግሞ የክፉ ዕጣችን ሆኖ ነውን? ወይንስ የአእምሮ እድገትና የአስተሳሰብ ደረጃችን ያመጣው ልዩነት? ይህን ጅምር-ቲየሪ ኮፒ ራይቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች የዘርፉ ምሁራን ጥልቅ ምርምር /እንደ ቻይናዊያኑ ማለቴ ነው/ ቢያደርጉበት ብዬ አልፌዋለሁ፡፡
እናም ወደ ፅሁፌ መነሻ ስመለስ ቋንቋ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል! የምትል መፈክር መሰል ዑደተ-ቋንቋን የምታስረዳ ሀረግ ታወሰችኝ እርግጥ ነው ይህ ዑደት የማይታበይ እውነታን የተላበሰ ቢሆንም የኔ ወግ የሚያተኩረው በቋንቋ ውልደት ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ እናም ውልደቱን እራሱ እንዲህ በዑደት አስቀምጬዋለሁ ቋንቋ ይፈጠራል፣ ይስፋፋል፣ ይለመዳል! ስል፡፡
እንደሚታወቀው ቋንቋ የሚዳብረው ወይም የሚያድገው በውስጡ ያሉ ቃላቶች ገላጭነትና ትርጉም ሲሰፋ እንዲሁም የተመሳሳይ ቃላት አማራጮችን ተከትሎ ነው፡፡ ታዲያ አማርኛችንም እንደ አንድ ጠንካራ ቋንቋ ብርቱ ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እንደ ዘመኑ ለዘመኑ የሚገቡ ዘመን-ወለድ ቃላቶችን እየፈጠረ፣ በነባር ቃላት ጥመረታዎች አዳዲስ ቃላትን እየጨመረ፣ ከሌሎች ቋንቋዎች እንደ ወረዱ እየወረሰ እንዲሁም በሌላም በሌላም መንገዶች እየታገዘ እድገተ-ህልውናውን ማስጠበቅ አለበት፤ survival of the fittest / ሃይል ያለው ርትዕ አለው/ አይደል ጨዋታው፡፡   
የዛሬ ወጌን ለመጠረቅ ያዳዳኝ የሰሞነኛ አዳዲስ ቃላቶች መብዛት እንዲሁም የነባር ቃላት በአዲስ መልክ አዲስ ትርጓሜ ይዞ ብቅ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቃላት ወይም ሀረጎች በአብዛኛው በጥቂት ቀልድ አዋቂ ወጣቶች የሚፈጠሩ ሲሆኑ ቀስ በቀስ ግን እየተስፋፉ ይመጡና ኋላ ላይ ይለመዳሉ እንደ አንድ የቋንቋው አካል ይቆጠራሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ መስሚያዬ ድፍን ነው የሚባል አማርኛ መጥቷል፣ እረ እንደውም አንዱ ጓደኛዬ በአጭሩ MD ብሎኛል /መስሚያዬ ድፍን ነው/ መሆኑ ነው፡፡ ይህቺ ሀረግ ወይም አረፍተነገር በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው ወጣት ዘንድ ተስፋፍታ ተለምዳለች መቼም ትርጉሟ የሚገመት ነው የምትለውን አልቀበልም፣ አልሰማህም እንደማለት ነው፡፡ ሌላም ተመሳሳይ አባባል አላት መስሚያዬ ጥጥ ነው/MT/
ሌላው ነባር ቃል ነገር ግን ይዘቱን ቀይሮ በአዲስ መልክ ከተፍ ያለው "ሰምተሃል/ሰምተሻል!" ነው ይህንን ቃል አሁን አሁን የማንሰማበት ቦታ የለም ድሮ ድሮ አንድን ነገር ላለመድገም ስንፈልግ "ጨዋና ራዲዮን አንዴ ነው የሚናገረው" ነበር የሚባለው አሁን አሁን ግን "ሰምተሃል/ሰምተሻል!" ሆኗል፡፡
በነገራችን ላይ ስለዚህ ቃል አመጣጥ የሰማሁትን አፈ-ታሪክ ላውጋችሁ አንድ ሰውዬ ነበር አሉ በአመት ውስጥ መጠየቅ የሚችለው አንድ ጥያቄ  ብቻ ነው ታዲያ አንድ ቀን የረጅም ጊዜ ፍቅረኛውን "የኔ ቆንጆ ለምን አንጋባም?" ሲል ይጠይቃታል ልጅቱ ታዲያ ሰውዬውን እንብዛም አትወደውም ኖሮ "ምን አልከኝ?" ትለዋለች ያልሰማ ለመምሰል፤ ምክንያቱም አመታዊ የጥያቄ ኮታው እንድ ብቻ ነዋ፤ ታዲያ ሰውዬው ምኑ ሞኙ "ሰምተሻል!" ብሎ መለሰላት ይባላል፡፡  
ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ቃላቶች በአብዛኛው በወጣቶች ዘንድ የሚዘወተሩ ቢሆኑም ከላይ እንደጠቀስኩት ቋንቋ ይፈጠራል፣ ይስፋፋል፣ ይለመዳል! ነውና ብሂሉ አሁን አሁን እነዚህን ቃላቶች የሚጠቀሙ በእድሜ የገፉ ሰዎችንም ማስተዋሉ እየተለመደ ነው፡፡ እንደ አብነትም የቅርብ ጓደኛዬን አያት በዋቢነት መጥቀሱ በቂ ነው፤ የጓደኛዬ አያት ከሩቁ ለሚያያቸው ኮስታራና ወግ አጥባቂ ቢመስሉም ለቀረባቸው ግን ተጫዋችነታቸውን ለመገንዘብ ደቂቃ አይፈጅበትም፡፡ ጨዋታ ወዳጅነታቸው የመነጨው በወጣት ልጆቻቸው እንዲሁም የልጅ ልጆቻቸው ታጅበውና ተከበው ውለው ስለሚያመሹ ነው፡፡ ታዲያ ግማሹ ስራ ውሎ፣ ሌላው ትምህርት ውሉ ምሽት ሲገናኙ ሳሎኑ በአንድ እግሩ ነው የሚቆመው፤ ድብልቅልቅ፡፡ አያት ጋቢያቸውን ተከናንበው ሶፋቸው ላይ ተጋድመው ወሬ በያይነቱ መኮምኮም ነው፣ በወጣት ቋንቋ፣ በወጣት አንደበት የሚደሰኮሩትን ሁሉ አፋቸውን ከፍተው ሲኮመኩሙ ማምሸት የዘውትር ልማዳቸው ነው፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ይህ ጓደኛዬ ስራ ውሎ መሸትሸት ሲል ወደ ቤት ይገባል፤ እንደ ደንቡም አያቱን እጅ ነስቶ በመኪና ትሸኛለህ የተባለውን ዘመዶቹን መጥተው እንደው ይጠይቃል እንዲህ ሲል "ማማ እንግዶቹ አልመጡም እንዴ?" አያት ሲመልሱ "እረ ወፍ የለም!"
ጓደኛዬ የአያቱ ፍጥነት የተሞላበት ቅፅበታዊ አመላለስ ፈፅሞ ያልጠበቀው በመሆኑ ሶፋ ላይ እየተንከባለለ በግርምት እንደተንከተከተ አጫወተኝ፤ እኔም አያቱን በቅርበት ስለማውቃቸው "እረ ባክህ! ማማ እንዲህ አሉ?" እያልኩኝ አብሬው በሳቅ ፈረስኩ፡፡ "ለመሆኑ ከማን ሰምተው ነው ስለው?" እቺን ሀረግ በተደጋጋሚ የምትጠቀማት የልጅ ልጃቸውን ጠቀሰልኝ፤ እውነትም አልኩ ቋንቋ ይፈጠራል፣ ይስፋፋል፣ ይለመዳል!
ይህን ፅሁፌን ለማዘጋጀት ስሰናዳ እንደ "ሰምተሃል/ሰምተሻል!" ሁሉ ይህቺም ቃል /ወፍ የለም/ መነሻ አፈ-ታሪክ ካላት ብዬ ጠያየኩ አስጠያየኩ ግን አውቃለው የሚል አልተገኘም/ወፍ የለም/፤ ጎሽ! ይኸው አኔም ለመድኩላችሁ፡፡
እኔ እምለው፣ እነዚህ ቃላት የእውነት ተስፋፍተው ቢለመዱስ? መቼም መለመዳቸው አይቀርም፡፡ አንደኛ ጉጉቴ በኢቴቪ/ኢሬቴድ/ አንደበት እነዚህን ቃላቶች ለመስማት ነው፡፡ እንደው ስገምት ጋዜጠኞች ዜና ሲያነቡ እንዲህ ሊሉ ይችላሉ "በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ ያሳሰባቸው የታክሲ ባለንብረቶች ከመንግስት ጋር ባደረጉት ውይይት መንግስት በቀጣይ ጊዜያት የነዳች ዋጋውን ለማረጋጋት ድጎማ ለማድረግ አቅዶ እንደሆነ የጠየቁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ "ወፍ የለም!" በማለት በአጭሩ ምላሹን ሰጥቷል አይነት ዜናዎችን መስማታችን አይቀርም ብዬ እገምታለው፡፡                         
ሌላው ጉጉቴ እነዚህን ቃላቶች ፓርላማ ላይ ለመስማት ነው፤ እንኳን እንዲህ አይነት ቃላቶች ታክለውበት ፓርላማችን አሁን አሁን አዝናኝነቱን አልቻልነውም፤ እስኪ አስቡት "የተከበሩ እገሌ… ሰምተዋል!" ምናምን ሲባል፤ ቂቂቂቂ፡፡ እስኪ ለማንኛውም እድሜና ጤናውን ይስጠንና የምንታዘበው ነገር ይሆናል አልሰማንም እንዳትሉ ሰምታችኋል! ሰላም


Wednesday, May 9, 2012

“ስለ ፍቅር” - የቴዲ የፍቅር በረከት!

እነሆ ነገ የፍቅር ዳግማዊ ትንሳኤ የሚከበርበት ዕለት ነው፤ ቀዳሚዎቹ ቀናት ደግሞ የፍቅር ትንሳኤ የተዘከረበት ሆነው አልፈዋል፡፡ ለመሆኑ ትንሳኤ እንዴት አለፈላችሁ? ለእኔ አሸወይና ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የትንሳኤን የፍቅር መገለጫነት በጥልቅ እንዳስብ ያደረገኝን ምርጥ ሙዚቃ እያደመጥኩ፣ ትንሳኤ ዘ ዳግማዊ ፍቅርን/ዳግማዊ - ትንሳኤን/ እየጠበኩላችሁ ነው፡፡ ታዲያ ዘፈን ሁሉ  ዘፈን አይባልም፤ ዘፈን ወይም ሙዚቃ ስል፣ ቴዲ አፍሮ በአዲስ አልበሙ በቁጥር ሁለት ላይ ያስደመጠንን “ስለ ፍቅር” አይነት ምርጥ ሥራ ማለቴ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የቴዲ አፍሮን አዲስ አልበም አደመጣችሁት? እኔም እንደ አብዛኛው አድማጭ አልበሙ ይወጣል በተባለበት ቀን በብርቱ ክርክር በ25 ብር ገዝቼ የቴዲን አዲስ አልበም በጠዋቱ መኮምኮም የጀመርኩት፡፡ ረፈድፈድ ሲል ግን ጥቂት ቅጂ ብቻ ነው የተለቀቀው በሚል ሰበብ፣ ሲዲው ከ40 ብር እስከ 100 ብር ሲሸጥ እንደዋለ በመስማቴ እድሌን እና ክፉ ተከራካሪነቴን አመሰገንኩ፡፡

አልበሙ ከመለቀቁ በፊት በከተማችን አብዛኛው ክፍሎች የተለጠፉትን የቴዲን ፖስተሮች ሳልፍ ሳገድም እያየሁ፣ በጉጉት ስጠባበቅ የነበረው የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን የ“ጥቁር ሰው” ሙዚቃንና ትርጉም ለመስማት ነበር፤ ልክ የቀዳሚው አልበሙን “ያስተሰርያልን” ትርጉምና ዘፈን ለመስማት እንደቸኮልኩት ሁሉ፡፡

እናም ሲዲውን ገዝቼ በቅርብ ባገኘሁት ማጫወቻ  (ላፕቶፕ) ውስጥ ስከተው ዘፈኑን ቁጥር አንድ ላይ አገኘሁት፡፡ ሙዚቃውን በጆሮዎቼ እና በስሜቴ እየሰማሁ፣ በአይኔ ደግሞ የሲዲው ሽፋን ላይ የሰፈሩትን ጽሑፎች ማንበብ ጀመርኩ፡፡ “የአልበሙ መታሰቢያነት…” ወዲያው የ“ጥቁር ሰው” ህብረ - ቃል እና ሰም ተገለፁልኝ፡፡ ወርቁን እንደ ቅኔ ደጋግሜ ስሰማው ሊገለጽልኝ እንደሚችል በማሰብ፣ በልቤ አጨብጭቤ ወደ ሁለተኛው ዘፈን አለፍኩ፡፡

ሙዚቃ ቁጥር - 2፣ “ስለ ፍቅር”፤ የሚለው አጀማመሩ ላይ ልክ እንደ ቁጥር -1 ደቡባዊ ቃና የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ቀጠልኩ… በከፊል ጉጉታዊ፣ በከፊል ሂሳዊ አኳኋን ጆሮዬን አርዝሜ፤ እንዲያው በደፈናው የደቡብ ከመሰሉኝና ካልገቡኝ ቃላት ቀጥሎ ያሉት የመጀመሪያዎቹ የአማርኛ ሀረጐች ቀልቤን ገዙት…ሙዚቃውን በግርምት ጀምሬ በፀፀት  ጨረስኩት፡፡ ወደሚቀጥለው ሙዚቃ ለማለፍ አልፈለግሁም፤ ደገምኩት፤ እንደገና… ሶስት፣ አራት ጊዜ…የሙዚቃውን ርዕስ አንብቤ ከጠበኩት የፆታዊ ፍቅር ትርጉም በተለየ ስለ አገር የተዜመ መሆኑ የበለጠ ቀልቤን ገዛው፡፡ ለዛውም፣ አገር ስለምንላት ስለ ግዑዟ ተራራና ሸንተረር ሳይሆን ስለ ህዝቧ፣ ለህዝቧ ስለሚገባ ፍቅር መሆኑ የእርካታ ማማ ላይ አወጣኝ፡፡

የሙዚቃው ወርቅ ይገለጽልኝ አይገለጽልኝ ባላውቅም ስለ ሰሙ ግን እንዲህ ለማለት ደፈርኩ - ከሙዚቃ ስንኙ እያጣቀስኩ :-

ስለ ፍቅር ሲባል ስለፀብ ካወራን ተሳስተናል
አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል…

ሲል የህብረትና አንድነታችንን ተፃራሪነት ያሳየናል፤ አንድ ላይ ነን ብለን ብናስብም አንዳችን ፍቅር ሌላችን ጠብ እንደነገሰብን እያዜመ ይቀጥላል ዘፈኑ…

አጥተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል
የመጣነው መንገድ ያሳዝናል…እያለ፡፡

ነገር ግን በእርግጠኝነት የተለያየንበት ምክንያት ማጣታችንና መቸገራችን ብቻ ነው ብሎ ባለማሰቡ ይመስላል የቁጭት ጥያቄ ይሰነዝራል…

እግር ይዞ እንዴት አይሄድም ሰው ወደፊት አይራመድም
አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ፣ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ…

በማለት፤ ችግራችን ከተፈጥሮ እንዳልመነጨ ውብ እና አንጀት በሚበሉ ቃላት ያንጐራጉራል፤ ከእግር እግር ከአገር አገር፣ እግሩ ቀና፣ አፈሩ መና(ና ጠበቅ ብሎ ይነበብ) እያለ…
ጠይቆ ጠይቆ መልስ ያጣ ሰው ሁሌ እንደሚያደርገው፣ ወደ ኋላ መለስ በማለት የችግሩን ስር መሰረት ለመረዳት ታሪካችንን እንመርምር የሚሉት ስንኞች ደግሞ ይቀጥላሉ…

የት ጋ እንደሆነ ይታይ የኛ ጥበብ መሰረቱ
የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ…በማለት፡፡

ይቀጥልና ደግሞ መሄጃ መንገድ እንደጠፋው፣ የተስፋ ወጋገኑ እንደራቀበት በመግለጽ የእረፍት መንገድ፣ የከንቱ መዋተትና መንከራተት መቋጫን፣ የተስፋ አቅጣጫን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ እያለ…

ከአድማስ እየራቀ ምነው ይሄ መንገድ ያባክነኛል
በየት በኩል ብሄድ ወደ እረፍት ሀገሬ ቶሎ ያደርሰኛል

አገራችንን ኢትዮጵያንም ሲገልፃት በአብረቅራቂ ቀለማት፣ በተሽቆጠቆጡ ቃላት መሆኑ አገራችንን በልዩ የስሜት ከፍታ እንድናያት ያነቃናል፤ ያነሳሳናል፡፡

ቀስተ ዳመና ነው የለበስኩት ጥበብ፣ የያዝኩት አርማ
አልጠላም ወድጄ የነብሴ ላይ ፋኖስ እንዳያይ ጨለማ

ይህቺን አርማዋን በቀስተ ዳመና የመሰለች አገር፣ የነብስ ፋኖስ ብርሃኗ ጠፍቶ ለማየት እንደማይፈልግ፤ ፍቅርን እየተማፀነ ይጠይቃል፤

አንተ አብርሃም የኦሪት ስባት
የእነ እስማኤል፣ የይስሃቅ አባት
እንደ አክሱም ራስ ቀርፀሃት ራሴን
በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነብሴን

አብርሃም ከሁለት ነገዶች የተገኙ ልጆች አባት እንደሆነ፣ የፍቅርና የፅናት አባትነቱን ይጠቅስና በእሱ አምሳል እንዲቀረፅ ተማፅኖውን ያቀርባል፡፡ ነብሱ በፍቅር ጧፍ እንድትበራ፤ ልቡ ቀና እንድትሆን፤ የተስፋይቱን ምድር ከንዓን /ዳግማዊት-ኢትዮጵያን/ በአይኑ እስኪያይ ድረስ ልቡ እንዳይዝል፣ ሰውን ለመውደድ እንዳይደክመው ያዜማል፤ አገርኛ በሆነ ሆድ በሚበላ እንጉርጉሮ! …

በል አትዛል ቀና ሁን ልቤ
የህልሜን ከንዓን እንዳይ ቀርቤ
ሰው ለመውደድ ካልኩኝ ደከመኝ
ያኔ ገና ውስጤን አመመኝ …

በነገራችን ላይ አዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም መጠሪያ “ስለ ፍቅር” መሆን ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ይህን ስል ታዲያ “ጥቁር ሰው”ን ሙዚቃን እያሳነስኩ አይደለም፡፡ በግጥምም፣ በዜማም፣ በሃሳብም ጠንካራ መሆኑን መካድ ከቶም የሚቻል አይደለም፡፡ ታዲያ ይህ አልበም “ስለ ፍቅር” መሆን ነበረበት ስል ምክንያቴ የመነጨው ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ዜማዎቹ ውስጥ በተለያየ መንገድ ቢሆንም ቴዲ አፍሮ “ስለ ፍቅር” ተቀኝቷል፤ አዚሟልና ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል “ሃያል” የሚለውን ቁጥር 7  ብንመለከት…

ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ
የተራራው ጫፍ ፍቅር ናት እርስቴ
ቀላል ይሆናል ቀና አርገኝ ፅናቴ…
ቀላል ይሆናል (4X) …

በማለት ልክ እንደ ቁጥር 2  (“ስለ ፍቅር”) ዜማው የፍቅር ፅናትን ይለምናል፣ ስለ ነገ ብሩህ ተስፋ በፍቅር ሙዚቃ፣ በሬጌ ይሰብካል፡፡

ደመና ሲያይ መስሎት የጨለመ
አለ ይህ ሰው ሁሉም አከተመ
ደቂቅ ተስፋን ካየናት አርቀን
ነገ ሌላ ይሆናል ብሩህ ቀን
ቀላል ይሆናል (4X) …

በመቀጠልም የባለቅኔውን የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ግጥም በመሃል በሚጣፍጥ አኳኋን አስገብቶ በያሬዳዊ ዜማ፣ በፀናፅልና በከበሮ ታጅቦ ስለ ፍቅር ማህሌት ይቆማል፣ ስለ ፍቅር እግዚኦ ይላል …
አዬ…አዬ…ፍቅር… እያለ፡፡

በመጨረሻ የቅዱስ መፅሃፉን ቃል አስታውሻችሁ ፅሁፌን ላብቃ፡፡ “እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፡፡” ለዚህም ይመስላል ቴዲ አፍሮ የኮንሰርት ሥራዎቹን ሲያቀርብ “እንዋደዳለን? ፍቅር ያሸንፋል!” እያለ የሚናገረው፣ የሚሰብከው፡፡ የዳግማይ-ትንሳኤ በዓል የፍቅር ይሁንልን እያልኩ፣ ትንሳኤ ለዳግማዊቷ-ኢትዮጵያ እመኛለሁ፡፡ ቴዲንም ቃለ-ጥበብ ያውርስልን!! ኢትዮጵያ በፍቅር ለዘላለም ትኑር!

Saturday, 21 April 2012\ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የታተመ

http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_content&view=article&id=2136:2012-04-21-16-57-52&catid=96:3d-computer-graphics&Itemid=503 

የሁለት ሱሶች ወግ ቻትና ጫት!

የዛሬው ወጋችን (ቻታችን) በሁለተኛ ዘመነኛ ሱሶችና ፋሽኖች ላይ ያጠነጠነ ይሆናል፤ በቻትና በጫት ዙሪያ፡፡ ቻት (Chat) አሁን አሁን ቃሉ አማርኛ እስኪመስለን ድረስ እንደወረደ እየተጠቀምንበት ያለ የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ሜሪት የእንግሊዝኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ግሱን ተጫወተ፣ አወራ፣ አወጋ ሲለው፤ ሰዋሰውን ደግሞ ጭውውት ይለዋል፡፡ እኔ እምለው፣ መቼም ዘመን የማይተካው ነገር የለም፤ ስለ ዲክሽነሪ ሳስብ አይኔ ላይ ምን ድቅን እንዳለብኝ ታውቃላችሁ? የአምሳሉ አክሊሉ ያቺ ባለ ሰማያዊ ቀለም ቅልብጭ ያለች ዲክሽነሪ፡፡ ልጅ እያለሁ እሷን ዲክሽነሪ ከሽማግሌ ፈረንጅ ሁሉ አዋቂ አድርጌ ነበር የምቆጥራት፤ “አ-ቤ-ት ያ ሁሉ ቃላት!” በያኔው ጭንቅላት፡፡ ለማንኛውም “The Classic” ብያታለሁ፡፡ እንደ መረቀነ ሰው ወግ አደበላለቅሁ አይደል? በሉ ወደ ቻታችን …

ቻት (ጭውውት) ድሮ ድሮ ሰዎች በአካል በአይነ-ሥጋ ተገናኝተው ሸጋ ሸጋ ወግ የሚለዋወጡበት ማህበራዊ-ሥርዓት ነበር፤ አሁን አሁን ግን በአካል በአይነ-ሥጋነቱ ቀርቶ በድረ-ካሜራ (Web-cam) በአካል ተራርቆ በምስል እየተያዩ፣ በፈጣን የፅሁፍ መልዕክት የሚጨዋወቱበት ማህበራዊ የድረ-ገፅ ሥርዓት ሆኗል፤ በዚህ የኢንተርኔት ትውልድ፡፡

ታዲያ፣ ድሮ ድሮ ጭውውትን የናፈቁ ጓደኛማቾች “መስመር ላይ አትታይም እስኪ እንደ ድሮው እንገናኛ፤ አንጠፋፋ” ሲባባሉ፤ የዘንድሮ ጓደኛሞች ደግሞ “አትጥፊ ጀለሴ፣ ኦን ላየን (online) እንገናኝ” ሆኗል!

በአሁኑ ሰዓት አያሌ የማህበራዊ ድረ-ገፆች (Social-networks) ይህንኑ ቻት በተሳለጠ ሁኔታ ማቀላጠፍ ሆኗል ስራቸው፡፡ ከነዚህ ድረ - ገፆች መካከል እነ ፌስ ቡክ (facebook)፣ ያሁ (Yahoo)፣ ጂሜይል (gmail) እና ሆት ሜይል (hotmail) በዋነኝነት በአገራችን ውስጥ ብዙ ተጠቃሚዎችን ያፈሩ ናቸው፡፡ በተለይ ፌስቡክ የሚባለው ድረ-ገፅ በአሁኑ ሰዓት ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ አስተማሪ፣ ከሰራተኛ እስከ ቦዘኔ … ሁሉም በአንድነት ተጠምዶ የሚውልበት የወግና የስላቅ መለዋወጫ ማህበራዊ ድህረ ገፅ-ሆኗል፡፡

ይህ ድረ ገፅ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን መከወኑ፣ አዝናኝነቱና ለአጠቃቀም መቅለሉ በአለም አቀፍ ደረጃ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል፤ በአገራችንም በተለይ በአዝናኝነቱ የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት ችሏል፡፡

መቼም ማንኛውም ነገር ጥሩና መጥፎ ጎኖች እንዳለው የማይታበይ ሃቅ ነው፤ ታዲያ የእነዚህ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ዋነኛ አሉታዊ ጎን ጊዜ ተሸሚነታቸው ነው፤ በዚህም አሉታዊ ጎናቸው ተማሪዎችን ከጥናታቸው፤ ሰራተኞችን ከስራቸው እያስተጓጎሉ ይገኛሉ፡፡ ለልማትና ለበጎ ስራ ሊውሉ የሚገባቸው ውድ ጊዜያት በቧልትና በቀልድ እንደዋዛ ይባክናሉ፤ በነዚህ ማህበራዊ ድረ-ገፆች፡
በአሁኑ ሰዓት የፌስቡክ (አካውንት) የለኝም ማለት ወይም ፌስቡክ ተጠቃሚ አይደለሁም ማለት እንደ ትልቅ ነውርና ውርደት እስከ መቆጠር ደርሷል፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከወጣት እስከ አዋቂ የፌስ ቡክ አካውንት ባለቤት ነው፡፡ እንደውም አንድ በዚሁ ድረ-ገፅ ያነበብኳት ቀልድ መሰል ተግሳፅ /ሲሪየስ-ኮሜዲ ልንለው እንችላለን/ ትዝ አለችኝ፡፡ እንዲህ ትላለች፤ “ሰው የባንክ አካውንት ይከፍታል አንተ የፌስ ቡክ አካውንት ክፈት!” ትላለች፡፡ እቺው ፅሁፍ ከታክሲ ላይ ፅሁፎች የተወሰደ በሚል እንዲህ ተቀይራ ቀርባለች “ሰው አካውንት ይከፍታል አንተ አፍህን ክፈት! (lol) በነገራችን ላይ ይህች ቃል በእነዚህ ድረ-ገፆች በብዛት የምንጠቀማት የእንግሊዘኛ ምህፃረ - ቃል ናት፤ ሙሉ ቃሉም “Laugh out loud” (በሳቅ ፈረስኩ እንደ ማለት) ሲሆን ለአማርኛችን እንዲስማማም Sbs ተብላለች፤ ሳቅ - በ-ሳቅ እንደማለት፡፡

መቼም በአግባቡና በስርዓቱ ለተጠቀመባቸው እንደዚህና የመሳሰሉትን አይነት ቀልዶችና ቁምነገሮችን በትርፍ ሰዓት እያነበቡ መዝናናትና መማር ስለሚቻልባቸው እነዚህ ማህበራዊ ድረ-ገፆች በጎ ማህበራዊ ፋይዳ አላቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ማህበራዊ ፋይዳቸው ሳይሆን ዕዳቸው እየጎላ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም  ከአዝናኝነትና መረጃ ሰጪነታቸው ባሻገር ሱስ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በየትምህርት ቤቱ በትምህርት ሰዓት ሳይቀር እነዚህን ድህረ-ገፆች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ሲጠቀሙ የተያዙ ተማሪዎች፣ ወላጅ እንዲያመጡ እየተደረጉ መሆኑ አንዱ ማሳያ ሲሆን ሌላው ደግሞ በየቢሮው “በስራ ሰዓት ፌስቡክ መጠቀም ክልክል ነው” የሚሉ ማስታወቂያዎች በየግድግዳው ተለጣጥፎ መታየቱ ነው፡፡ ኧረ እንደውም አንዳንድ ቢሮዎች ባስ ሲልባቸው እነዚህን ድህረ-ገፆች ብቻ ለይተው ያዘጋሉ (block) ያስደርጋሉ፡፡

እንደው በአጋጣሚ ጥሏችሁ (ማለቴ ሱስ ጥሏችሁ) ወይም እንደኔ ለሪሰርች (lol) ወደ ጫት ቤት ጎራ ያላችሁ ከሰኞ እስከ ሰኞ፣ ከጠዋት እስከ ማታ ጫት ቤቶች በጫትና በቻት ተጠምደው ውለው ማምሸታቸውን ሳትታዘቡ አልቀራችሁም፡፡ ከተማሪ እስከ ቢሮ ሰራተኛው ሁሉም በየፊናው፣ ከየፊናው የፎረፈባትን ሰዓት በጫቱና በቻቱ ተጠምዶባት ታያላችሁ፡፡ ይህን ጉዳይ ካስተዋልኩ በኋላ የድሮ ወጣቶች ትዝ አሉኝ፣ በጣም ድሮም አይደለም፤ ያኔ በ70ዎቹ ምናምን ያሉ ወጣቶች፤ “በምን ይሆን ያኔ ቢዚ የሚሆኑት ብዬ ጠየቅሁ?” እእእ…አዎ ትዝ አለኝ፤ የያኔው ሱስ ፖለቲካ ነበር፤ በየካፌው፤ በየጥጋ ጥጉ በየዩኒቨርስቲው የጦፈ ፑትለካ ይካሄድ ነበር፤ በተለያዩ ጽንፎች ጐራ በመያዝ ወጣቶች በፖለቲካዊ ሱስ የተጠመዱበት ዘመን፡፡

የዘንድሮ ወጣትም ታዲያ እንዲሁ በሁለት ጐራ ሀይለኛ ሱሳዊ ጦርነት ይዟል፤ በቻትና በጫት፤ ጫቱን እየቃመ ቻቱን ያደራዋል፤ የረባውን ያልረባውን፣ የባጡን የቆጡን፣ ከአገር ውስጥ እስከ አለምአቀፍ፤ ከፈጠራ ወሬዎች እስከ ፈጠራ ቀልዶች…ወዘተ የማይደሰኮር ነገር የለም፤ በቻትና በጫት ቤት፡፡

ወደ ርዕሰ ወጌ ስመለስ ቻትና ጫት ከቃሎቹ ዜማዊ ምት መመሳሰል ባሻገር እንደ ሱስ ምን ይሆን የሚያመሳስላቸው ስል አወጣሁና አወረድኩ፤ እናም አንዳንድ የተገለፁልኝን ነጥቦች እነሆ፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት ቻት በአሁኑ ሰዓት ወጣት፣ አዋቂ ሳይል በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደ ሱስ የተዛመደ የማህበረሰብ ነቀርሳ መሆኑ ከጫት ጋር የሚያመሳስለው ሲሆን፡፡ በሌላ አነጋገር ቻትም ጫትም ሁለቱም ጊዜን በከንቱ የምንገድልባቸው ከንቱ ሱሶች ናቸው፡፡

ሌላው መመሳሰላቸው የሚመነጨው ሁለቱም በአብዛኛው የቧልትና የፌዝ መድረኮች መሆናቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ማህበራዊ ድረ ገፆች ከጽሑፍ ልውውጥ (ቻት) በዘለለ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችና ትምህርቶች የሚተላለፉባቸው መድረኮች ቢሆኑም በአብዛኛው የሚውሉት ለቀልድና ለስላቅ መሆኑ ከጫት ማስቃሚያ ቤቶች ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡
ሶስተኛው ነጥቤ፣ ቻትም ጫትም የሁለትና ከዛ በላይ ግለሰቦችን ከንቱ ጊዜያት የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ መቼም ጫትን ለብቻም መቃም ይቻላል ትሉኝ ይሆናል፤ ለዚህ ደግሞ ሁነኛ መልሴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፤ አንድ ሰው ብቻውን እንኳን ጫት ቢቅም ብቻውን ነው አይባልም፤ ምክንያቱም የጫቱ (የምርቃናው) ባህሪ ብዙ ማንነቶችን በቃሚው ላይ ስለሚፈጥር እንዲሁም በሃሳብ አነውልሎ በውስጡ ካሉት ገፀባህሪያት ጋር መነጋገር ስለሚጀምር በእርግጥ ብቻውን ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ታዲያ ቻትም በተመሳሳይ መልኩ የሁለትና ከዛ በላይ ግለሰቦችን ከንቱ፣ ባካኝ ጊዜ የሚጠይቅ ነው (ቁምነገራዊ ቻቶችን አያካትትም) በነገራችን ላይ፣ ጫት ቤት አካባቢ በቡድን/በግሩፕ የመቃምን ሂደት ጀመአ በማለት ሲጠሩት፤ በቻት ቤት ደግሞ የቡድን ጭውውት (group chat) ይሉታል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ቻትም ጫትም የሚፈጥሩት የማህበራዊ ህይወት ክፍተት ነው፡፡ ጫት በባህሪው ቁጭ ማለትን የሚጠይቅ ሲሆን አንዴ ቁጭ ከተባለ ደግሞ ስለሚያደነዝዝ የመነሳት ስሜትን ያጠፋል፡፡ ታዲያ ይህ ባህሪው ከቻት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ አንድ ሰው ቻት ላይ ከተጣደ ተነስ ተነስ አይለውም፡፡ ረዥም ሰዓታትን ቁጭ ብሎ ያሳልፋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከሰዎች ጋር ያለን ማህበራዊ ግንኙነት እንዲቀንስ ብሎም እንዲጠፋ ያደርገዋል፡፡

እንደውም ትንሽ የቆየን እንደሆን ለቅሶን፣ ሀዘንን፣ እንዲሁም የታመመ ሰው ጥየቃን ሁሉ በነዚሁ ድረ - ገፆች እስከ መጠቀም ሳንደርስ አንቀርም፤ አሁንስ አልተጀመረም ብላችሁ ነው? በዚህ አኳኋናችን እርግጠኛ ነኝ ወደፊት የሙዝና የብርቱካን ስዕል ፌስ ቡክ ላይ Tag በማድረግ (በመለጠፍ) የታመመን ሰው መጠየቅ እንደምንጀምር፤ አልያም RIP እገሌ (እገሌን ነብሱን ይማር) የሚል ግሩፕ በፌስ ቡክ ፈጥረን ቻት በማድረግ ለቅሶን መድረስ ባንጀምር…

ሌላኛው ተመሳሳይነታቸው በተጠቃሚው ላይ የሚያደርሱት አካላዊ ጉዳት ነው፡፡ መቼም ስለ ጫት የጤና ጠንቅነት መዘርዘር አይጠበቅብኝም፤ ምክንያቱም አብዛኞቻችን በቂ መረጃ አለን ብዬ ስለምገምት፡፡ ጫት የሚያደርሰው አካላዊ ጉዳት እንዳለ ሆኖ፣ ቻትን አዘውትሮ መጠቀም ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ቻትን በኮምፒውተር ስለምንጠቀም ለረጅም ሰዓት ኮምፒውተር ላይ በማፍጠጥ ለሚከሰት የአይን ብርሃን ጉዳቶች እንዳረጋለን…ወዘተ…ወዘተ፡፡

እርግጥ ነው በአሁኑ ሰዓት የነዚህን ሁለት አደገኛና አደንዛዥ ሱሶች ስርጭት ለመግታት የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው፡፡ በጫት በኩል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመሆን ጫት ማስቃሚያ ቤቶች እንዲታሸጉ እያደረገ ሲሆን በቻት በኩል ደግሞ በየትምህርት ቤቱና በየቢሮው ያሉ ኮምፒውተሮች ላይ እነዚህ ድረ ገፆች ቢያንስ በስራ እና በትምህርት ሰዓት እንዲዘጉ (block እንዲደረጉ) እየተደረጉ ነው፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱንም ሱሶች በዚህም መልክ ከነአካቴው ልናስቀራቸው አንችልም፡፡ ምክንያቱም ጫት ቤቶችም ቢታሸጉ በየግል ቤታቸው እና የስራ ቦታቸው ጫትን የሚቅሙ ወጣቶች አይጠፉም፡፡ በቻት በኩል ደግሞ የቢሮና የት/ቤት ኮምፒውተሮች እንኳን ብሎክ ቢደረጉ በግል ሞባይሎቻቸው መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ የወጣቱ ልብ እስካልተለወጠ ድረስ ብናሽገው፣ ብንዘጋው፣ ብናስረው፣ ብንገስፀው በዚህም ሆነ በዚያ ብሎ ሱሱን ከማስታገስ ወደ ኋላ አይልም፡፡ እዚህ ላይ አንድ የእንግሊዝኛ አባባል ትዝ አለችኝ “ሱስን ጨርሶ ማጥፋት አይቻልም ባይሆን በሌላ ሱስ መቀየር ይቻላል እንጂ” የምትል፤ አባባሏ እውነትነት ካላት እነዚህን ደባል ሱሶች(ቻትና ጫት) የምናስተውበት ቀጣዮቹ የወጣቶቻችን ሱሶች ምን ይሆኑ? ሰላም!


የታፈኑ የቢሮ ድምፆች

እንዴት ናችሁ? ኑሮስ? ስራ ምናምን? እንደ ጐበዝ ተማሪ ጥያቄ አበዛው አይደል! አበው መጠየቅ የማወቅ በር ነው ሲሉ ሰምቼ ጉድ ሆኜላችኋለሁ፡፡ “እንዴት?” አትሉኝም፤ በቃ ከድሮ ጀምሮ ተማሪ እያለሁ መጠየቅ እወዳለሁ፤ የማልጠይቀው ነገር የለም፣ አደግ ስል እንደውም መጠየቅን ሁላ መጠየቅ ጀመርኩ (ፍልስፍና ጀመርኩ ማለቴ ነው፡፡)በተለምዶ “መጠየቅ ሀጢያት አይደለም” ሲባልም ስለሰማሁ ይሆናል አንዳንዴ ከልክ ያለፉ ጥያቄዎችን ሁላ እጠይቃለሁ፤ መልስ ባገኝም ባላገኝም፤ በቃ…መጠየቅ በራሱ ለኔ አንዳንዴ መልስ ነው፤ /እንዴት ብላችሁ ደግሞ እንዳትጠይቁኝ/ ባይሆን የሆነች ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡

ልጁ የኔ ቢጤ ነው፣ ማለቴ…መጠየቅ ይወዳል፤ እንጂ ተመጽዋች ነው ለማለት ፈልጌ አይደለም፤ ለነገሩ የኔ ቢጤ/ተመጽዋች/ እራሱ መጠየቅ አይደለም ስራው፡፡ አይ ጭንቅላት! ከየት ከየት አገናኘኋት ባካችሁ? አሁን ይሄ ጭንቅላት ፓርላማ አያስገባም? ለማንኛውም ወደ ቀልዱ ልመለስ፡፡ እናላችሁ ይሄ መጠየቅ የሚወድ ልጅ ከት/ቤት ሲመለስ ሁልጊዜ አባቱን ቤት ውስጥ በጥያቄ ያጣድፈዋል፡፡ አባትም ለአብዛኛው ጥያቄ መልሳቸው “ልጄ ይሄን አላውቀውም” የሚል ነው፡፡ ታዲያ ልጁ መች መጠየቅ ያቆማል፡፡ አሁንም ሌላ ጥያቄ…ይሄን ጊዜ የልጁ እናት “ኧረ ተው አንተ ልጅ! አባትህን ዝም ብለህ በጥያቄ አታድርቀው” ይሉታል፣ አባትም መልሰው “ተይው እንጂ ይጠይቅ፤ ካልጠየቀ እንዴት ያውቃል!” በማለት መለሱ እላችኋለሁ፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ መጠየቅ እራሱ ለመልስ እሩብ ጉዳይ ነው፤ ወይንም በራሱ መለስ ነው፡፡ “መጠየቅ መጠየቅ አሁንም መጠየቅ” አይደለም ያለው ሌኒን/መቼም ሌኒን ያላለው ነገር የለም ብዬ ነው/

እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ራሴ ጨዋታ ልመልሳችሁና አንድ የተማሪነት ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ የኤለመንተሪ ተማሪ እያለሁ ጓደኞቼ ሲያሾፉብኝ፣ እገሌ እኮ ለሊቱን በሙሉ ሲያጠና ስለሚያድር ጠዋት ክፍል ውስጥ ገብተን ስንማር እንቅልፍ ሲያሸልበው በእንቅልፍ ልቡ ሁሉ እጁን ወጣል ይሉኝ ነበር - መጠየቅ መውደዴን ሲያጋንኑት፡፡ እርግጥ ስሆን አልጋ ላይ እንደተኛ ሰው ሙሉ ለሙሉ በእንቅልፍ - ልብ ውስጥ ስለማልሆንና ይልቁንም በክፍል - ልብ ውስጥ ሆኜ ስለምተኛ ነው፡፡ በሌላ አማርኛ ነቃ ብዬ ስለምተኛ ነው፡፡ ታላቅ ወንድሜ ደግሞ ሁልጊዜ ለጥናት ብዬ ቡና ስጠጣ “ነቃ ብለህ ለመኛት ነው አይደል?” እያለ ያሾፍብኝ ነበር፤ ምክንያቱም ለጥናት ብዬ ቡና ጠጥቼ ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንቅልፍ ስለሚያዳፋኝ ነው፡፡ ታዲያ ልክ እንቅልፍ ሲያዳፋኝ እናቴ ታየኝና “አንተ ፈንዳሳ ቡናዬን በከንቱ ታከስራለህ አይደል!” ብላ በተራዋ በጥፊ ስለምታዳፋኝ ከቡናው ከቡናው ይልቅ ጥፊውን እያሰብኩ ነቃ ብዬ እተኛ ነበር፡፡ አይ ጥፊ! እንቅልፍን እስከነመፈጠሩ የሚያስጠላ ጥፊ! ደግሞ ሰዓቱ ነው የሚያናድደው፡፡ ልክ እንቅልፍ ሊወስድ ሲል ያለችው ጊዜ እኮ ናት!  ያቺ በመብረርና በመንሳፈፍ፣ በመዋኘትና በመቅዘፍ መካከል ያለችው ልዩ ውብ ሰዓት…እዛች ሰዓት ላይ አይደለም በጥፊ ጆሮ ግንድህ እስኪጮህ ተወልውለህ… በስርዓት እንኳን ሰው ሲቀሰቅስህ እንዴት እንደምትናደድ ስለኸዋል?/ስዕል አልችልም እንዳትለኝ/

አይ የኔ ነገር፡ ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ ትቼ ሌላ ሌላ ነገር እቀባጥራለሁ አይደል? አሁን ታዲያ ለኔ ጥፊ ያንሰኛል? ለማንኛውም ወደ ጉዳዬ…ነገሩ የተፈጠረው በቅርቡ ነው፤ “የት?” አትሉኝም፤ ጠይቁ እንጂ፤ ጉዳዩ እኔው የምሰራበት ቢሮ ነው የተከሰተው፤ የመጠየቅ መዘዙ የተመዘዘው፡፡

ቢሯችን እየከሰረ ነው፣ ኧረ እንደውም ሊዘጋ ነው የሚል ሩም ሩምታና ጉም ጉምታ በሰፊው እየተናፈሰ ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ሀሜታ የሰማነው ደሞዝ ከተሰጠን ወር ከአስራ አምስት ቀን በሆነን ጊዜ በመሆኑ “ምንድነው ነገሩ” ብለን ግራ ቀኙን ስንጠያይቅ ነበር፡፡ እናም ምክክር ያዝን፡፡ እንደ መፍትሔ ሃሳብ ምን መደረግ አለበት ስንል የቢሮ ባልደረቦች በምሳ እረፍታችን መከርን፤ ዘከርን፤ ፎከርን፤ አሴርን፡፡ የምሳ እረፍታችንን ለምክክር የተጠቀምንበት ሌላ የመመካከሪያ ጊዜ አጥተን አይደለም፤ ይልቁኑም ምሳን በምሳሌ፣ እራትን በተረት የሚያስብል ደሞዝ ተከፋዮች በመሆናችን ነው፡፡ ደሞዙስ ቁጥሩ ሲጠራ ሞገስ ነበረው፡፡ የዛሬን አያድርገውና! ግን፤ ያው ዘንድሮ ብሩ በረሮ ሆነ እንጂ፡፡

እናም ምክክራችን ጦፎ አንኳር ጉዳዮችን በጥልቅ የርሃብ ስሜት ውስጥ ሆነን ከተወያየን በኋላ የመፍትሔ ሃሳብ ጥቆማ ተጀመረ፡፡ አንዱ ባልደረባችን “ለምን ሰላማዊ ሰልፍ አንወጣም?” አለ፤ ሌላኛው አከለ “ሰላማዊ ሰልፉ እንዳለ ሆኖ እንደሚታወቀው የምሳ መብያም ስለሌለን በዛውም ለምን የረሃብ አድማ አንመታም?” ሲል በረሃብ ስሜት ብቻውን መቆም ባለመቻሉ የባልደረባው ሃሳብ ላይ ተደገፈ፤ እኔ ግን ምንም ነገር ባልዋጠው አንጀቴ ያቀረቡት ሃሳብ ያልተዋጠልኝ በመሆኑና በባዶ ሆድ ከመሰለፍ ወደሚቀጥለው ሃሳብ ማለፍ ያዋጣል ብዬ በማሰብ፣ የሌላኛውን ባልደረባችንን ሃሳብ እና የሆዳችንን ጩኸት መስማት ጀመርን፡፡ “እኔ የምለው ግን አለቆቻችንን በማያስቆጣ መልኩ ለየት ያለ የአጠያየቅ መንገድ ብናስብስ?” በማለት ወዲያው ንግግሩን ባጭሩ አቋርጦ እራቱን ማሰብ ጀመረ፤ /መሰለኝ/፡፡ በዚሁ ውይይታችን ለሻይ ቡና እረፍት ክፍት ሆነ፤ ወጉ አይቅር ተብሎ፡፡

ቢሮ ገብቼ በባዶ ሆዴ ለፈጠራ ብንጠራራም እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ አልሆነም፤ ወዲያውም አንድ ሀሳብ ብልጭ ብሎ ድርግም አለብኝ፤ እንደገና ብልጭ አለልኝ…አገራችን ውስጥ ብዙ የፈጠራ ሰዎች የሌሉት ለካ ስለሚራቡ ነው ብዬ “ሃንገር ቲዮሪ” አፈለቅሁ፡፡ አንድም የቲዮሪ ፈጣሪነት ችግራችንን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ሌላም ትሪ የናፈቀውን ወገኔን በቲዮሪ ለመካስ በማሰብ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ አንዲት ስርጉት የምትባል የቢሮ ባልደረባችን ብስኩት ገዝታ እየበላች ነበርና አንድ ብስኩት ፀደቀችብኝ፡፡

ብስኩቴን ከሽ እንዳደረኩ “ጨጉዌክስ” ለአእምሮዬ ሜሴጅ ላከለት መሰለኝ ደረጃ -3 ውስጥ ሊካተት የሚችል ምን የመሰለ ሃሳብ መጣልኝ፡፡ ሃሳብን በስዕል የመግለጽ ሃሳብ/መብት ልል ነበር ቸኩዬ፤ ሃሳብ ሁሉ መብት ቢሆን የት በደረሰን/፡፡ ለማንኛውም፣ ሃሳቡ የመጣልኝ በፌስ ቡክ ድረ-ገጽ በተደጋጋሚ ካየኋት ስዕል ነው፤ ስዕሏ “Salary, why do you take so long!” የምትል መግለጫ (caption)  አላት፡፡ እንግሊዝኛና ህልም እንደ ፈቺው ነው ይላል የለ! (ደሞዝ ሆይ ወዴት አለሽ?) እንደ ማለት ነው ትርጉሟ እናም ይችን ስዕል የኮምፒውተሬ ስክሪን ሴቨር ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ምክንያቱም አለቆቼ ከፊት ለፊቴ ስለሚቀመጡ ስዕሏ አንድም ሃሳቤን ትገልጥላቸዋለች፣ ሌላም ታዝናናቸዋለች፡፡ በዋናነነትም ጥያቄዬን ትጠይቅልኛለች በማለት - በየዋህነት፡፡ ታዲያ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነውና ይህንን ያየችው አለቃዬ እንኳን የስዕሌን ሃሳብ ተረድታ ልትዝናና እና ጥያቄዬን ልትመልስ ቀርቶ፣ “አገኘኋት እንደተመኘኋት” በሚል  “በስራ ኮምፒውተር ላይ ኢ-ስነምግባራዊ መልዕክት በመለጠፍ” የሚል የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አሻረችኝ፡፡

አሁን እውነት እንነጋገር ከተባለ ደሞዝ በጊዜውና በአግባቡ አለመስጠት ነው ወይስ “ደሞዝ ሆይ ወዴት አለሽ?” ብሎ ሃሳብን በስዕል መግለጽ ኢ-ሥነምግባራዊ ተግባር? ለማንኛውም ይህንን ጉዳይ በቀላሉ የማየው አይሆንም፡፡ እስከ አለም አቀፉ የኢ-ሥነምግባር አጣሪ ኮሚሽን ድረስ ቢቻለኝ በጽሑፍ አልያም በስዕል ሃሳቤን አስረዳለሁ፡፡ ማን ይሙት ዲሞክራሲ በጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በስዕል በሚገኝባት አገር ይህን አይነቱን ኢ…ተግባር ምን ይሉታል? ምናልባት የመጠየቅ ጠንቅ? እኔ እንጃ!
በሌላ የቢሮ ወሬ እንገናኝ፡፡ ሰላም!

Monday, 05 March 2012/ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የታተመ

http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_content&view=article&id=1873:2012-03-05-14-39-21&catid=96:3d-computer-graphics&Itemid=503