Thursday, June 13, 2013

ይድረስ ለውዷ እናቴ፣ ሉሲይድረስ ለውዷ እናቴ፣ ሉሲ


መቼም ለዘንድሮ የትንሳኤ በዓል  ወደ አገሩ ያልተከተተ ኢትዮጲያዊ የለም፡፡ ያው ከአገሩ የወጣ ሰው ወደ ትውልድ ቀዬው ለመመለስ ምክንያት መደርደሩ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ታዲያ ለእንዲህ አይነቱ ሰው በተለይ ለክርስቲያኑ ማህበረሰብ ወደ አገሩ ለመመለስ እንደ ፋሲካ ያለ ድንቅ በዓል አይገኝም፡፡ ይሄ በውጪ ያሉ ሰዎች ይናፍቀናል የሚሉት የዓውድ-ዓመት ሽታና ግርግር ከሌሎች በዓላት በተሻለ ሁኔታ በትንሳኤ በዓል ስለሚደምቅ ነዋ፡፡ 

ታዲያ በዚህ የትንሳኤ በዓል በህይወት ያለ ኢትዮጲያዊ ቀርቶ አንቺ ውዷ እናታችን-ሉሲ እንኳን ከአምስት አመታት የአሜሪካ ቆይታ በኃላ ወደ አገሽ ከተፍ ማለትሽን ሰማን፡፡ ፋሲካን ከዘመድ አዝማዶቼ፣ እትብቴ ከተቀበረባት፣ አፅሜ ተቆፍሮ ከወጣበት የትውልድ አገሬ ልከተት ብለሽ፡፡ ለማንኛውም እንኳን በሰላም ወደ አገርሽ ተመለሽ ብለናል፡፡ እንኳን በሰላምና በጤና ላገርሽ፣ ለአፈርሽ፣ ለቀዬሽ አበቃሽ ብለናል፡፡ ድንቅ ነሽና ድንቅ የሆነ የዳግማ-ትንሳኤ በዓልንም ተመኝተናል፡፡

ከሁሉ ከሁሉ የደነቀኝ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ስለ አንቺ የሚወራው አሉባልታ መብዛቱ ነው፤ እንደውም ምን ሲሉ ሰማሁ መሰለሽ፣ ሉሲ አሜሪካን አገር በነበራት ቆይታ በቁሙ ያለ ኢትዮጲያዊ ያልሸቀለውን ዶላር ሸቃቅላ ነው የመጣችው እያሉ ሲያወሩ፡፡ እሰይ! እንኳን! ደግ አደረግሽ! እንደ አንዳንድ ዓላማ ቢስ፣ ቡኩን፣ ስደተኛ በብልጭልጭ ነገር ሳትታለይ፣ በዘመነው የውጭ አገር አኗኗር ሳትደለይ፣ የተሰደደሽበትን አላማ ሳትረሺ፣ አልበላም አልጠጣም ብለሽ፣ የሰራሻትን እያንዳንዷን ሽርፍራፊ ሳንቲም ሳትቀር በመሃረብሽ ቋጥረሽ ወደ አገርሽ መመለስሽ ብልጥነት እንጂ ፋራነት አይደለም፡፡ 

ሌላ ደግሞ ምን እያሉ ሲያወሩ ሰማሁ መሰለሽ፣ ሉሲ አሜሪካን አገር በሸቀለችው ዶላር ለእናቷ ሲኤምሲ አካባቢ ምን የመሰለ ቤት ገዝታላቸዋለች፣ ለአባቷ ደግሞ ሲኖ ትራክ፣ ለወንድሞቿ ለአንዱ ላዳ፣ ለአንዱ ሚኒ ባስ… ምናምን እያለ ሰዉ ያወራል፡፡ እውነት ይሆን ሉሲ?
የሚወራው ነገር እውነት ቢሆንም እንኳን ምንም አይደለም ሉሲዬ፡፡ በሰው አገር ላብሽን አንጠፍጥፈሽ፣ የስንቱን አይንና ግልምጫ ችላ ብለሽ፣ በስንቱ ታይተሸ፣ ያገኘሽውን ገንዘብ ለራስሽ አንድም ነገር ሳታደርጊበት፣ መዘነጥ፣ መሽቀርቀር፣ ዳንኪራ መርገጥ አማረኝ ሳትይ ወደ አገርሽ ይዘሽ መመለስሽ የሚያስመሰግንሽ እንጂ የሚያሳማሽ አይደለም፡፡ ይልቁንም የጀግና፣ የኩሩ ኢትዮጲያዊ ተግባር ነው፡፡ ኩሩ የናቷ ልጅ! ልጅ ማለት እንዲህ ነው! የሚያስብልሽ ነው፡፡ አንዳንዱ በቁሙ ቤተሰብ ያሳዝናል፣ አገር ያሰድባል፤ እንደ አንቺ አይነቱ ግን 'አይ ልጅ!' እየተባለ ይሞካሻል፡፡ ይኸው በሙትሽ እንኳን እኛ ጋር ነይ፣ እኛ እንይሽ እየተባለሽ በየቦታው፣ በየአገሩ ጥሪ ይቀርብልሻል፤ ለእይታ ብቻ በርካታ ዶላር ይዘንብልሻል፡፡

በኔ በኩል ወደ አገርሽ መመለስሽን ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? በቃ ይሄ በየቦታው ቁጭ ብሎ ወሬውንና ሃሜቱን ከመሰለቅ ውጪ ቁም ነገር የማያውቀውን፣ የኩታራ አሉባልታና እነቶ ፈንቶ ወሬ ኩሽ አደርገሽዋ፡፡ 

አንድ ሰሞን የእናትነት መንፈስሽ ካለሽበት ጠርቶኝ ነው መሰል በናፍቆት ተቃጥዬ "አረ የሉሲ ነገር እንዴት ነው፣ ጠፋችብን እኮ ቤቷ ስንሄድ የምናገኘው ምስለ-አካሏ የሷነቷን ያህል መንፈስ የለውም፣ የእናትነት ጠረን የለውም፣ የእምዬን ናፍቆትና ርሃብ አያስታግስም" ብዬ ብጠይቅ  "አልሰሜን ግባ በለው! ሉሲ እኮ አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቃለች፤ ላትመለስ ነው የሄደችው አሉኝ" ጠላትሽ ክው ይበል፤ ው ብዬ ቀረሁ፤ በድንጋጤ እንዳንቺው አፅም ሆንኩልሽ፡፡ ጠላትሽ አመዱ ቡን ይበልና አመዴ ቡን አለ፡፡ አሁን ግን በቃ መምጣትሽን ስሰማ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ፣ የደስታና የናፍቆት ሲቃ ተናነቀኝ፤ ለነገሩ ያው የልጅ ነገር ሆኖብኝ ደነገጥኩ እንጂ ጨቅነሽ እንደማትጨክኚ፣ ቀርተሸ እንደማትቀሪ ልቤ ያውቀው ነበር፤ ለማንኛውም በድጋሚ እንኳን በሰላም መጣሽልኝ እናቴ፡፡

ያው የዚህ አገር ኑሮ እንደምታውቂው ነው፤ መቼም ትረሺዋለሽ ብዬ አላስብም፤ ምንም እዛ ብትሆኚም ልብሽ እዚህ ነውና፡፡ ኸረ ለመሆኑ! ረስቼው ሳልጠይቅሽ፣ የዛሬ አምስት አመት ጥለሻት የሄድሻት አገርሽን እንዴት አገኘሻት? ፐ! ጉድ ሆናለች አይደል! አዲስ አበባንማ ተያት በቃ ቀውጢ እኮ ነው የሆነችው፤ የሆነ የልማት አርበኛ ገበሬ የቆፈራት ትልቅ ማሳ እኮ ነው የምትመስለው፡፡ ብቻ የሁን መቼም የአስፋልቶቻችን ማማርና መስፋት እራሱ ቀላል ነገር አይደለም ቢያንስ ቢርበን እንኳን ጥሩ አስፋልት ላይ ተሰጥተን ጥርሳችንን እንፍቃለን፣ ሆዳችንን ረሃብ እየፋቀውም ቢሆን፡፡ በዛ ላይ ደግሞ እንደ 77ቱ ምናምና ይሄ ለፎቶ የሚደብር ባግራውንድ አይኖረንም፤ በቃ… አለ አይደል… ቀብረር ያለ አስፋልት ላይ ባንቺ መሪነት ምርጥ የአፅም ሾው እናሳያለን፤ ልክ እንደ ማይክል ጃክሰን ክሊፕ፡፡  

ኪ.ኪ.ኪ.ኪ.ኪ.… አልሽ? አይይይ…እ… አንቺ ምን አለብሽ እናቴ፣ ሳቂ በድድሽ፣ ሆድ የለሽ፣ ጥርስ የለሽ እኛው እንደፈረደብን እናማር እንጂ፤ የፈለገስ ቢሆን ደግሞ እድሜ ለአሜሪካን ዶላር፣ መመንዘር ነው፡፡ አይ የኔ ነገር፣ ይቅርታ የኔ እናት፣ ይሄ የኑሮ ነገር ሲነሳ ፀባዬ ሁሉ ቅይርይር ይላል ታውቂው የለ ክፋት እንደሌለብኝ፤ መቼም አትቀየሚኝም፤ ደግሞ መቀየም እኮ የኢትዮጲያዊ ብቸኛ ባህሪ ነው፤ አንቺ ደግሞ አምስት አመት አሜሪካ ተቀምጠሸ መቀየም የሚባለውን ቃል ከነመፈጠሩም የረሳሽው ይመስለኛል፡፡

እ…ሺ...! ታዲያ አሜሪካንን እንዴት አገኝሻት? መቼም እንደነ እገሌ ምነው አሜሪካዊ በሆንኩ ብለሽ አልተመኘሽም፤ እንደውም እንኳንም ኢትዮጲያዊ ሆንኩ ነው ያልሽው አሉ፡፡ ምክንያቱም አሜሪካዊ ብትሆኝ ኖሮ ማን ቆፍሮ ያወጣሽ ነበር፤ አሜሪካ ውስጥ አርኪዮሎጂስቶች ቆፍረው ሊያወጡት የሚችሉት እድሜ ጠገብ ታሪካዊ ቅርስ ቢኖር የክርስቶፎር ኮሎምበስ የውሃ መያዣ ኮዳ ነዋ፤ በቃ ከዛ የዘለለ ታሪክ የላትማ፡፡ ታዲያ ኢትዮጲያዊ በመሆነሽ ከነድህነታችንም ቢሆን አልኮራሽም? እንደውም ስሰማ፣ ፕራውድ ቱ ቢ ኢትዮጲያን የሚል ቲ-ሸርት አድርገሽ ሁላ ነው ወደ ኢትዮጲያ የገባሽው ይባላል፤ እውነት ነው?

በነገራችን ላይ፣ ያው የደሃ ነገር ታውቂዋለሽ፣ አይሞላለትም፤ ላይ ታች ስል፣ ከዛሬ ነገ እህዳለሁ ስል፣ መጥቼ ሳላይሽ ይኸው ዳግማ-ትንሳኤ መጣ፡፡ ቢሆንም ግን ይህቺ ደብዳቤ ከእኔ ቀድማ እንደምትደርስሽ አስባለሁ፡፡ በአካል ተገናኝተን የልብ የልባችንን እስክናወጋ፣ የፈረንጅ አገር ትዝብትሽንና ቆይታሽን እስክታጫውቺኝ፣ የናፍቆቴን ያህል ይህችን እጥር ምጥን ያለች ደብዳቤ አሰናድቻለሁ፡፡

እስቲ አሁን ደግሞ፣ ልጅ ነኝና እንደ ልጅ የልጅ ጥያቄ ልጠይቅሽ፣ ከውጪ አገር ምን አምጥተሸልኝ ይሆን? ላፕ ቶፕ፣ አይ ፎን፣ ስኒከር ወይስ ቲሸርት? መቼም ቲ-ሸርትም እንኳን ቢሆን እንደ እነ እገሌ አይ ላቭ ኒው ዮርክ የሚል ቲሸርት አታመጪልኝም፤ ምክንያቱም አይ ላቭ ኢትዮጲያ ብለሽ ነዋ የመጣሽው፡፡ ለማንኛውም ቸኮሌትም ቢሆን ይቀመጥልኝ ከሰሞኑ መጥቼ ሳላይሽ አልቀርም፡፡
"አይት በይ ነብሴ!" (ይቺ ከፊል እንግሊዘኛ፣ ከፊል አማርኛ፣ ከፊል አማርዝኝ የሆነች ሀረግ፣ በእንግሊዘኛ Alright then፣ እንደማለት፤ አሜሪካ ደርሰው የተመለሱ ጀለሶቻችን የሚያዘወትሯት ናት) አንቺም ሳትለምጂያት አትቀሪም ብዬ ነው፡፡ በይ እናቴ በአገርኛው ደግሞ፣ በአካል በአይነ ስጋ እስክንገናኝ ድረስ ቸር ሰንብቺ፡፡ እስከዛው ግን ሰላምታዬ በአይር ይድረስሽ ብያለሁ ውድ እናቴ-ሉሲ፤ ሎንግ ሊቪ ሉሲ! ሎንግ ሊቭ ኢትዮጲያ!

No comments:

Post a Comment