Thursday, June 13, 2013

የድብርታሙ ሰው ዲያሪ


ቀን፡ ግንቦት 12 13 12… ኤጭ! 


ዛሬ ቀን ስንት ነው? እኔ እንጃ! ለነገሩ ስንትስ ቢሆን ምን አገባኝ፣ ምን ልዩነት ያመጣል… የቀን ማስታወስ ችግሬ እንዳለ ሆኖ ሃያ ምናምን አመት የኖርኩ ይመስለኛል፡፡ እድሜዬን በሙሉ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሐምሌ… እያልኩ ስቆጥር፤ ህይወቴን በሙሉ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ እሮብን… ስደጋግም ኖሬያለሁ ግን ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ቢያንስ የቀናቱ ስም እንኳን አልተቀየረም፣ የወራቱ ስም እንኳን አልተቀየረም፤ ሲደብር! ለነገሩ ህይወት ማለት አሰልቺ የሰባት ቀናት ሳምንት እንዲሁም ተደጋጋሚ የአስራ ሁለት ወራት አመት ነች (ኦ! ለካስ አስራ ሶስት ወራት ናቸው ያሉን፣ ድንቄም!)


…ጠዋት፣ ከሰዓት፣ ማታ፣ ቀን፣ ሌሊት… እስቲ አሁን የህይወት አጓጊነትዋና ጣዕሟ የቱ ጋር ነው? ኑሯችን በነዚህ ደባሪና አሰልቺ አዙሪት ውስጥ የተዘፈቀች አይደለችምን? ለምድን ነው አራሳችንን የምናታልለው፣ ለምንድን ነው "እያንዳንዷ ቀን አዲስ ናት" እያለን የምንፎጋገረው? እውን እያንዳንዱ ቀን አዲስ ነው? ነው!? ከሆነስ ምኑ ጋር ነው አዲስነቱ? በቀን ሁለትና ሶስት ጊዜ መብላት፣ መውጣት፣ መግባት፣ መተኛት፣ መነሳት፣ እንደገና መተኛት፣ እንደገና መነሳት… ኡፍፍፍ.. ደባሪ!


ቀን፡ ግንቦት 13 14… አጭ! በቃ በንጋታው
ቅዳሜ/የእረፍት ቀን… ቀኑ እንደተለመደው ነው… ደባሪ! አልጋዬ ውስጥ ስንከባለል ቆይቼ ረፋድ ላይ በግድ ተነሳሁ፤ የምግብ ፍላጎቴ ጠፍቷል ነገር ግን እንደምንም ብዬ ቤት ውስጥ የነበረ ምግብ በግድ ቀማመስኩ፡፡ ቀጥሎም ምን ማድረግ እንዳለብኝ  ወይም የት መሄድ እንዳለብኝ ማሰላሰል፣ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡ 


ጓደኞቼ ጋር ልሂድ፣ ፊልም ልይ፣ ወይስ እዚው ቁጭ ብዬ አዲስ የገዛኋትን መፅሃፍ ላንብብ… አስራ ሁለት ልብ ሆንኩ፤ በመጨረሻም ረጅም ደቂቃዎችን ከፈጀ ውስጣዊ-ግለ-ጭውውት (Internal Monologue) በኋላ፣ አውጥቼ አውርጄ ማለቴ ነው ቤቴ ቁጭ ብዬ መፅሃፌን ለማንበብ ወሰንኩ፡፡ በነገራችን ላይ ሰው ማግኘት ሲደብረኝ ወይም ወደ ውጪ መውጣት ሲያስጠላኝ ሁሌም የማደርገው ይህንን ነው፤ ማንበብ፡፡ መፅሃፍትን የማነበው ህይወቴን ለመርሳት ነው፤ እራሴን ለመርሳት፤ ‘ስለ እውነተኛው’ አለም (ስለ ‘ገሃዱ አለም’) ላለማሰብ፡፡


የፍልስፍና መፅሃፍቶችን ማንበብ የምመርጠውም ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ መፅሃፍት በአብዛኛው የ‘ገሃዱ አለም’ ቀጥተኛ ነፀብራቆች አይደሉምና፡፡ እኔ ለምኖረው አይነት ህይወትና ለጥያቄዎቼ መልስ የሚሰጡኝ እንዲህ ያሉ መፃህፍት ብቻ ናቸው፡፡ ብዙ የPhilosophical Skepticism (ነቀፌታዊ ወይም ጥርጣሬያዊ ፍልስፍና) መፃህፍትን አንብብዬለው፡፡


በውሳኔዬ መሰረት መፅሃፌን ካስቀመጥኩበት መደርደሪያ ውስጥ አውጥቼ ለማንበብ በመስኮቴ ፊት ለፊት በተቀመጠው ፎቴ ላይ ተመቻችቼ ተቀመጥኩ(ዘፍ አልኩ)፡፡ ወዲያውም አንዴ ከተቀመጥኩ መነሳት ያለመውደድ ስንፍናዬ ትዝ አለኝና በቅርብ የሚያስፈልጉኝን እቃዎች በእጄ እርቀት እንዲሆኑ አድርጌ አቀራረብኩ፤ ሲጋራ፣ የሲጋራ መለኮሻ፣ መተርኮሻ፣ አንድ ሁለት ቢራዎች፣ የሲዲ ማጫወቻ የርቀት መቆጣጠሪያ፣ ‘ቢራ መክፈቻ’ (ለስላሳ ስለማልወድ እናንተ ‘ለስላሳ መክፈቻ’ የምትሉትን እኔ ቢራ መክፈቻ ነው የምለው)


ሶፋዬ ላይ ጀርባዬን አደላድዬ ቢራዬን ከፍቼ ጎርጎጭ ካደረኩ በኋላ ሲጋራዬን ለኮስኩ፣ ጭሱን ወደ ውስጥ በስስት ምጥጥ አድርጌ በአፍንጫዬ በኩል ወደ ውጭ በማስወጣት ጠባቧን ክፍሌን በጭስ ሞላኋት፡፡ አሁን ለማንበብ ዝግጁ ነበርኩ፤ ‘ያልተሄደበት መንገድ’ ትላለች የመፅሃፏ ርዕስ፤ የመፅሃፉ የውጭ ሽፋን ላይ ለአፍታ አፈጠጥኩ ሁለት ቅያሶች ያሉት መንገድ ይታያል፣ በዙ ሰዎች በአንደኛው መንገድ ላይ ተሰልፈው ይታያሉ፤ በሌላኛው መንገድ መጀመሪያ ላይ ደግሞ እነዚያን የተሰለፉትን ሰዎች ቆሞ የሚያይ ሰው ይታያል፡፡


ወደ ውስጥ ገፅ ዘለቅኩ፣ ገፅ-3፣ መታሰቢያ፣ “ይህ መፅሃፍ ላንተ ነው!” “ለኔ!?” አልኩ ሳላስበው፤ ፅሁፉን እኔው እራሴው ያነበብኩት አልመሰለኝም ይልቁንም ጎርነን ያለ ድምፅ ያለው ሰው ያነበበልኝ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ …የመፅሃፉን የመጀመሪያ ምዕራፍ ማንበብ ጀመርኩ፤ የቃላቶቹ ጥፍጠትና ጥንካሬ ደስ ይላል፤ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመግባቴ በፊት ቢራዬን ጎንጨት አልኩኝ፤ ንባቤ ቀጥሏል፣ አንድ አንቀፅ ላይ ግን ቀልቤ አርፏል ደጋግሜ አነበብኩት ወደ ቀጣዩ አንቀፅ ማለፍ አልቻልኩም፡፡
“… ህይወት ሙከራ ናት፤ አዎ! የሙከራ ፈተና! ህይወት የእውነት ብትሆን ኖሮ የት መሄድ፣ መቼ፣ ምን፣ ለምን፣ ማድረግ እንዳለብህ ይነገርህ ነበር…” እውነትም! አልኩ ውስጤ ላለው የ‘ገሃዱ አለም’ አውነተኝነት ጥርጣሬና ነቀፌታ ምላሽ ያገኘው መሰለኝ፤ ደስ አለኝ! ለሰው ልጅ ያሰበው ወይም የተናገረው ነገር ልክ ሆኖ እንደማየት የሚያስደስተው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ አላልኩህም/ሽም! ለማለት፡፡ በተመሳሳይ ስሜት እኔንም በጣም ደስ አለኝ፡፡


ንባቤን ቀጠልኩ “…ህይወት በተከታታይ ፈተናዎች የተሞላች ናት፣ ተፈትነህ ትወድቃለህ፣ እንደገና ታጠናና ታልፋለህ፣ ከውድቀትህ ትነሳለህ፣ ደረጃህ ከፍ እያለ በመጣ ቁጥር በሌላ ፈተና ትወድቃለህ፣ አሁንም ከውድቀትህ ትማርና አሻሽለህ ታልፋለህ… ይህ የማይቀር መንገድ ነው፤ የማይቀር የህይወት ጉዞ፡፡ ታዲያ የዚህ ጉዞ አጓጊነትና ጣፋጭነት የሚወሰነው በምትመርጠው መንገድ ነው፤ የትኛውን መንገድ ነው የመረጥከው? ብዙሃኑ የሄደበትና የተሰለፈበትን ወይስ ሌላው ልብ ያላለውን፣ ያልተሄደበትን መንገድ? የህይወት ጣዕሟና አጓጊነቷ እዚህ ላይ ነው እያንዳንዱ መንገድ የራሱ የሆነ መልስና ውጤት አለው፡፡ ተነሳ! ውጣ! ሂድ! ህይወትህን ሞክራት! ፈተናውን ስትሞክር ለመሳትፍ ሳይሆን ለማለፍ፣ ለመብለጥ ሳይሆን፣ ለመላቅ ይሁን፤ ያልተሄደበትን መንገድ ሞክር! ምናልባትም ታዕምር ታገኝ ይሆናል፣ ማን ያውቃል ታሪክ ትሰራ ይሆናል… ማን ያውቃል! ለነገሩስ ህይወት ሙከራ አይደለችምን?


ጀምበር እያዘቀዘቀች ነው፤ አይኖቼን ከመፅሃፉ ላይ መንቀል አቃተኝ፤ ለአፍታ እንኳን፤ ቀልቤን ገዝቶታል፣ ውስጤ ገብቷል፣ ፊደል በፊደል፣ ቃል በቃል እየለቀምኩ ነው የማነበው፤ በሚገባኝ ቃላት፣ በምረዳው አገላለፅ ለእኔ የተፃፈልኝ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ በቃላት ጠግባችሁ ታውቃላችሁ? አንድ ነገር ከመጠን ሲያልፍ እንደሚያቅለሸልሸው ነው የሆነብኝ፣ የሆነ የማስታወክ ስሜት ተሰማኝ፣ በቃላት ቁንጣን ተወጠርኩ፣ የፊደላት ህቅታ፣ ወደ ላይ ሊለኝ ሆነ… እንደ ምንም ብዬ መፅሃፉን ከአይኔ ላይ መነጨኩት፡፡


ሲጋራዬን ለኩሼ በረጅሙ ወደ ውስጥ ከመጠመጥኩት በኃላ ኡፍፍፍፍፍ! ብዬ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡ ከዛም የመፃፍቱን ቃላቶች በተመስጦ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡ በቃላቶቹ ያ ጎርናና ድምፅ ያለው ሰውዬ እየደጋገመ የሚገስፀኝ መሰለኝ፣ በሚቆጣ ትዕዛዛዊ ድምፅ፡፡ ማንነቴን ወደ ኋላ ዞር ብዬ መገርመም ጀመርኩ፣ በሂሳዊ አይን፡፡ “ህይወቴን በጥርጣሬና በነቀፌታ ሞልቻት ኖሬያለሁ፤ በዚህም ምክንያት ችሎታዬንና አውቀቴን አውጥቼ እንዳልጠቀም ሆኛለው፣ እውቀቴ የመመፃደቅና የትችት ነበር፤ በራሴ ድብርታም አለም ውስጥ ስሽከረከር ጊዜዬን ፈጅቼዋለሁ…  እራሴን ጠዘጠዝኩት፤ አቤት ግለ-ሂስ!” 


ውስጤ ሲታደስ ተሰማኝ፤ በሀሴት ተሞላሁ፡፡ “…ምናልባትም ህይወት እኔ እንደማስባት ጨለማ ላትሆን ትችላለች፣ ምናልባትም ብሩህ መንገድ ይኖራታል፤ እይታዬን የማስተካከያ ጊዜዬ አሁን ነው…” አልኩኝ፣ ለራሴ ይሁን ለባለ ጎርናናው ድምፅ ሰውዬ ሳላውቀው፡፡
ወደ ውጪ መውጣት ፈለ’ኩ፣ የህይወትን ሌላ ጎን ለማየት ጓጓሁ፣ ባልተሄደበት መንገድ ለመሄድ ፈለኩ፤ ዳሩ ምን ዋጋ አለው ቀኑ አርጅቶ ነበር፤ ምሽት፡፡


ግንቦት 14 (ለመጀመሪያ ጊዜ ሳልሰርዝ ሳልደልዝ ቀን የፃፍኩበት ቀን)
አይናችሁን መጀመሪያ ገልፃችሁ ነው ከዛ የምትነቁት ወይስ ነቅታችሁ ነው አይናችሁን የምትገልፁት? እኔ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቴ በፈገግታ በርቶ ከእንቅልፌ ተነሳሁ፤ አይኔን ገለፅኩ፤ ነቃሁ! በሬን ከፍቼ እስክወጣ አላስችል አለኝ፣ ባልተሄደበት መንገድ ጉዞዬን ለመጀመር አሀዱ አልኩ፤ ደስ ሲል!  


No comments:

Post a Comment