Sunday, May 20, 2012

የወሮታን ዋጋ ለሚነግረኝ ወሮታውን እከፍላለው

እንደ ጀማሪ ወገኛነቴ ለሲኒየር ወገኞች ወይም ባጠቃላይ ለፀሃፊዎች አንድ ጥያቄ አለችኝ፣ የአምስት መቶ ብር አልላችሁም፣ ምክንያቱም ለአንድ ጥያቄ አምስት መቶ ብር ካወጣሁ እንደኔ ጥያቄ አወዳደድ በጥያቄ ውዝፍ ዕዳ ልጠየቅ ነዋ፡፡ ለማንኛውም እጅ ሳታወጡ የምትመልሷት አንድ ጥያቄ እነሆ፤ "ውድ ወገኞች፣ እንዲሁም ፀሃፊያን፣ ስለ አንድ ነገር ለመፃፍ ስትነሱ መጀመሪያ የሚመጣላችሁ ምንድን ነው?" ርዕሱ ወይስ የፅሁፉ ሀሳብ(idea)?"

በበኩሌ የሆነ ወሬ ስሰማ ወይም ክስተት ስመለከት ጉዳዩን በምን መልኩ አልያም ከምን ዕይታ መፃፍ እንዳለብኝ ከማሰብ ይልቅ በቀጥታ ጉዳዩን የሚገልፅ ርዕስ ከተፍ እያለብኝ ተቸግሬያለው፤ በቃ ምን አለፋችሁ ምርጥ ምርጥ ቀልብና ልብ የሚገዙ ርዕሶች ከች ይሉልኛል፤ ከዛ ፅሁፉ ይጀመራል፡፡
ኤጭ! ‘ልብ የሚገዙ ርዕሶች’ የምትለው ሀረግ ምሬቴን አስታወሰችኝ፣ የምን? አትልኙም፣ ኑሮ እንዲህ ሰማይ ሳይሆን ጠፈር በነካበት በአሁኑ ወቅት ሁሉን ነገር ገዝተን እንዴት እንደምንዘልቀው ማሰቡ እንቆቅልሽ፤ ሂሳቡ ደግሞ እንቁልልጭ ሆኖብኛል፡፡ እውነቴን እኮ ነው፤ እንጀራ ገዝተን፣ ዳቦ ገዝተን፣ ውሃ ገዝተን፣ ጋዜጣ ገዝተን፣ ልብ ገዝተን፣ ቀልብ ገዝተን፣ ፀባይ ገዝተን፣ አደብ ገዝተን… ይሄ ሁሉ ሳያንስ ደግሞ እንደገና በስንቱ ተገዝተን እንደምንዘልቀው እንጃ፡፡   
ለማንኛውም ከግዢና ገዢ ርዕሴ ልውጣና ጥያቄ እንድጠይቅ ወዳስገደደኝ ጉዳዬ ልመለስ፤ እንዳልኳችሁ ይሄ ዝምብሎ ርዕሶች ከች የሚሉብኝ ልክፍት ከጀማመረኝ ቆይቷል፤ እንደውም ስገምት የፀሃፊነት ሞራሌ ከች ካለ ጊዜ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ በሽታ ይመስለኛል፤ እናም ይሄ ልክፍት ወይም እስካሁን ስሙን በውል ያላወኩት ደዌ በጣም እያሳሰበኝ በመምጣቱ ጉዳዩ ከሥነ-ልቦና ጋር ተያያዥነት ካለው ብዬ አንድ የሥነ-ልቦና ባለሙያ የሆነ ጓደኛዬን አማከርኩት፤ ሲያቀብጠኝ፡፡ ቅብጠትን ምን አመጣው አትሉኝም? ይሄ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ጓደኛዬ ሁሉ ነገር ከሥነ-ልቦና ጋር ይያያዛል የሚል አጉል ብሂል አለው፡፡
እንደሱ አመለካከት ሳይንስ ከሥነ-ልቦና ጋር ግንኙነት አለው፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ትዳር፣ ዕድር፣ ብድር፣ ድርድር… በቃ ምን አለፋችሁ ለእርሱ ሁሉ ነገር ምንጩ ሥነ-ልቦናዊ ነው፤ ልክ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪዎች man is a political animal (ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው) እንደሚሉት አይነት፡፡
ታዲያ በዚያች በተለመደች በምሁራዊ ሙከራ -1- -2- -3- አኳኋን ጉሮሮውን ካፀዳዳ በኋላ "ባይ ዘ ዌይ, ይሄ ጉዳይ ሥነ-ልቦናዊ ሂደት ነው፤ ነገርዬው ጥልቅ ሥነ-ልቦናዊ ዕውቀት ስለሚጠይቅ ላንተ የሚገባህ አይደለም ግን እንደው ባጠቃላይ ለማስቀመጥ ያህል…" ይህቺን አረፍተነገር ተናግሮ  በአፍንጫው በኩል በፍጥነት አየር ወደ ውስጥ ከሳበ በኋላ ለአፍታ ዝም ካለ እሱ እራሱ በውል ስለማያውቀው ነገር እየፈጠረ ሊቀበጣጥር እንደሆነ ስለምረዳ ንግግሩን አላስጨርሰውም፡፡ "አይ! እንዲገባኝ አሳጥረው" እለዋለው፤ "ኦኬ! እእእ… ይህን አይነቱን አእምሯዊ የሥነ-ልቦና ሂደት ርዕሰ-ቃርሞ እንለዋለን፤ ርዕስ መቃረም፣ መፈለግ፣ መሻት እንደማለት ሲሆን፤ ይህም የሚያሳየን የአስተሳሰብ ጅማሯችንን ነው፤ ግማሹ ከቁንፅል በመጀመር ሰፋ ወዳለው ነገር የማሰብ ሂደት ሲከተል ሌላው ሰፋና ብትንትን ካለ ሃሳብ በመጀመር…" ወሬውም እንደ ሃሳቡ የተበታተነና ምሁር ለመምሰል በሚፈጣጥራቸው አዳዲስ ጥንድ ቃላቶች የተሞላ ነው፤ ልክ እንደ ርዕሰ-ቃርሞ አይነት፡፡
ብዙውን ጊዜ ወሬው እንደ ካስትሮ ለሰአታት ስለማይቋረጥ ፍሬ ሃሳቡ ሳይገባኝ በሃሳብ ሽው እላለው፤ እንደውም እሱ አማራሪ ምሁራዊ ዲስኩሩን እየደሰኮረ አንድ ሶስት ቀሽት ቀሽት ርዕሶች ሁላ ከች ይሉልኛል፤ ታዲያ በዚህ የተነሳ እኔና ሌሎች ጓደኞቼ ይሄን ጓደኛችንን የሥነ-ልቦና ባለሙያ ሳይሆን የሥነ-ልቦና ካውያ እያልን ነው በድብቅ የምንጠራው፡፡  
ለዚህም ነው፣ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ማለቴ ካውያው ጓደኛዬ ምክርና ትንተና ብዙም ስላልገባኝ፤ እንዲሁም የጓደኛ ምክር ከመስማት ከባለሙያ ጋር በዋጋ መስማማት ብዬ የሙያ አጋሮቼን በሚገባኝ ቋንቋ ለ‘ርዕሰ-ቃርሞ’ በሽታዬ ማብራሪያ እንዲሰጡኝ በሚል ዋጋው ያልተጠቀሰ ጥያቄ ለወጊያን ወይም ፀሀፊያን የሰነዘርኩት፡፡
ባይሆን የሙያ አጋሮቼ ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ በቋሚነት የምሰራበት ቢሮ ያለ አንድ የስራ ባልደረባዬ ዘውትር የሚለንን ነገር ላጫውታችሁ፣ ልጁ የሙዚቃ ተሰጥዖ የለው በመሆኑ እንደ ሙያው የሚያየው ሙዚቃን ነው ታዲያ እኛን የቢሮ ባልደረቦቹን ሲጠራን የመዋያ አጋሮቼ እያለ ነው፤ ምክንያቱም እሱ ሙያዬ ብሎ የሚያስበው ሙዚቃን በመሆኑ የሙያ አጋሮቹ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ እኔም ፀሃፊያንን የሙያ አጋሮቼ ስል ታዲያ ከላይ ባጫወትኳችሁ አይነት ትርጉዋሜ ነው፡፡
እርግጥ ነው በአሁኑ ሰዓት ሰዉ በአረንጓዴኛ ማሰብ ስለመጀመረ (በብር ማለቴ ነው፤ በመቶ) የጥያቄዬን ዋጋ ከመናገር እንዲያው በደፈናው ሁነኛ ምላሽ ለሰጠኝ ወረታውን እከፍላሁ ብል ሳይሻል አይቀርም፡፡
በነገራችን ታች (ሁሌ በነገራችን ላይ ስለሚባል ለለውጥ ብዬ ነው) የመጨረሻዋ አረፍተነገር ወደ ዛሬዋ ወግ ትወስደናለች፤ አንከባላ፡፡ መቼም አንደርድራ አልላችሁም እስከሁን በረባ ባልረባ ወሬ ስነተርካችሁ ቆይቼ፡፡
የዛሬው ወጌ በዋናነት ርዕሱን የቃረመው ከመጥፋት ጋር በተያያዘ የምንጠቀምበትን ዋጋው በውል ያልታወቀ ወዘልማዳዊ የብር ኖትን (‘ወሮታ’) በተመለከተ ነው፡፡ ስለ ወሮታ እያሰብኩ ብዙ ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ ተመላለሱብኝ፤ ግን ‘ወሮታ’ ምን ማለት ነው? ዋጋውስ ስንት ነው? (ማሳሰቢያ፡- እነዚህ ጥያቄዎች ምናባዊ በመሆናቸው ሙሉ ለሙሉ ከክፍያም ሆነ ከወሮታ ነፃ ናቸው፡፡)
አስተውላችሁ ከሆነ፣ ይህችን ቃል በተደጋጋሚ የምንጠቀምባት ወይ ሰው አልያም ዕቃ ሲጠፋን በአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ነው፤ ብዙዎቻችን በቃላችን እስክንሸመድዳቸው ድረስ በየግድግዳው ተለጥፈው ወይም በሬዲዮኖች እየተነገሩ፤ እንደዚህ፡ "አቶ/ወ/ሪት/ወ/ሮ እገሌ የተባልኩ የመንጃ ፈቃዴ፣ ፓስፖርቴና ሌሎችም በጣም አስፈላጊ ዶክመንቶች ስለጠፉብኝ ዶክመንቶቹን አግኝታችሁ ለምትደውሉልኝ ‘ወሮታ’ውን እከፍላለሁ" አልያም ደግሞ "አቶ እገሌ የሚባሉ ሰው በእንትን ቀን እንትን ለብሰው እንደወጡ ስላልተመለሱ፣ ያሉበትን የሚያውቅ ወይም የሰማ በሚከተሉት ስልክ ቁጥሮች ደውሎ ቢያሳውቀን ወሮታውን እንከፍላለን፤ ፈላጊ፡ አፋላጊ ዶት ኮም፡፡" (በነገራችን ላይ ሰሞኑን በአንዳንድ ፎቆች ላይ አፋላጊ የሚሉ የኤቲም ማሽን የሚመስሉትን የቁም ሳጥኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይ ዕቃና የጠፋ ሰው አፋላጊ በወሮታ የሚሰሩ ማሽኖች መስለውኝ ነበር፤ በዚህ አጋጣሚ አሪፍ የቢዝነስ አይዲያ ጠቆምኳቸው አይደል? መቼም ይሄ ስራ ከተጀመረ ፓተንቱን በእናንተ በአንባቢዬቼ ምስክርነት ለግሌ በማድረግ ቁጭ ብዬ እንደምጦር ነው፡፡)
ቆይ ግን ለመሆኑ ከወሮታ ላይ መንግስት ግብር ይቆርጣል እንዴ? የወሮታ-ግብር ምናምን የሚባል ነገር እስካሁን አልሰማችሁም? በሉ ከአሁን በኋላ ትሰማላችሁ፤ መንግስት ጆሮው ብዙ ነው ይባል የለ፤ አይኑም እንደ ጆሮው ብዙ ከሆነ ይህች ፅሁፍ ከተነበበች ቀን ጀምሮ ይታሰብበታል ማለት ነው፤ ከሰሞኑ አዋጅ ጠብቁ፡፡ እንደው ያድርገውና/አያድርገውና/ የወሮታ-ግብር ከተጀመረ የወሮታ-ግብር አጭበርባሪዎች ፍ/ቤቶቻችንን ሊያጨናንቁት ነው ማለት ነው፡፡ ለነገሩም ወሮታ ዋጋው ስንት እንደሆነ በውል ባለመታወቁ ለማጭበርበር ያመቻል፡፡
ቆይ ግን አቶ እገሌን (እንደውም ለምሳሌ እንዲመች አቶ ወሮታው የሚባሉ የጠፉ አዛውንት) አግኝቼ  ወሮታዬን ልቀበል ሄድኩኝ፤ መቼም ወሮታው በአርንጓዴኛ ነው የሚከፈለኝ ብዬ በማሰብ፤ ይሄኔ አፋላጊዎቹ አቶ ወሮታውን አቅፈውና ስመው ተቀብለው እኔንም ቤታቸው ወስደው በሻይና በምርቃት ቢያሰናብቱኝ ወሮታዬን አልሰጡኝም ብዬ መክሰስ እችል ይሆን? ወይስ ልክ እንደ ደሞዝ በስምምነት ወሮታም በስምምነት ነው?
የሚገርመው ነገር ይቺ ርዕስ ከተፍ እስክትልልኝ ድረስ እኔም እራሴ የወሮታ ቀንደኛ ተጠቃሚ የነበርኩ መሆኔ ነው፤ እንደውም በቅርብ የማስታውሰው አንድ አጋጣሚዬን ላጫውታችሁ፡ ለብዙ አመታት ስጠቀምበት የነበረውን የፖስታ ሳጥን ኪራዬን ለመክፈል ወደ ፖስታ ቤት አቀናሁ፤ ከረጅም ጊዜ በኋላ፤ ኮራ-ቀብረር ብዬ፣ ቱታ ለብሼ (ፈታ ብዬ ለማለት ነው እንጂ እሱስ ጅንስ ነበር የለበስኩት፤ በነገራችን ላይ ይህቺ ቃል ሰሞነኛ ናት ‘ቱታ ልበስ’ ፈታ በል እንደማለት ነው ትርጉሟ)
እናላችሁ የሳጥን ኪራይ ሰብሳቢውን ቀረብ ብዬ የመጣሁበትን ጉዳይ ስነግረው የሳጥን ቁጥሬንና መታወቂያዬን ጠየቀኝ፤ እንደተለመደው ኮራ ቀብረር ብዬ ቁጥሬንና መታወቂያዬን ሰጠሁት፡፡ ሰውዬው ፋይሌን ከብረት መሳብያው ውስጥ ፈልጎ ካወጣ በኋላ "አዝናለው የሳጥን ኪራይህን በወቅቱ ባለመክፈልህ ለሌላ ደንበኛ አከራይተነዋል፤ ሌላ ሳጥን የምትፈልግ ከሆነ ክፍት ሳጥኖች ስላሉ እዛ ጋር ያለውን ፎርም ሞልተህ አምጣ" በማለት ወደ ስራው ተመለሰ እኔም በሳጥን ደንበኝነት እድሜዬ ልክ ካጉረመረምኩና ከተነጫነጭኩ በኋላ ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ የአዲስ ሳጥን ፎርም ሞልቼ ቁልፍ ከተቀበልኩ በኋላ ለቀድሞው እኔ ለአሁኑ እገሌ/ሊት (የቀድሞው ሳጥኔ አዲሱ ባለቤት) የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፍኩ፡
፡ አዲሱ የቀድሞ ሳጥኔ ባለቤት
፡ ቀድሞው የሳጥንህ ባለቤት
ለተከበርከው አዲሱ የቀድሞ ሳጥኔ ባለቤት እኔ ከሞቀችው ከቀድሞ ሳጥኔ ሃሳብና ናፍቆት በስተቀር በጣም ደህና ነኝ፤ አንተስ የቀድሞ ሳጥኔን ካገኝህ በኋላ ጤናህ እንዴት ነው? የሞቀችው ሳጥኔ ተስማምታህ ይሆን?
ወደ ፍሬ ሃሳቤ ስገባ አሁን እየተጠቀምክበት ያለውን ሳጥን ከዚህ ቀደም እኔ በስስትና በጉጉት እየዳበስኩ ስከፍተው የደብዳቤዎች ናዳ ወደ መሬት ይጎርፍ ነበር፡፡ እናም ይህ አንዳችም ሳላጋንን ያቀረብኩት የደብዳቤ ፍሰት በቀጣይ ወደ አንተ መጉረፉ የማይቀር ነውና አዲሱ ሳጥኔ እስኪለምድና እስኪሞቅ ድረስ በቀድሞ ሳጥኔ የሚላኩ ደብዳቤዎችን በሙሉ ወደዚህኛው ሳጥኔ(አዲሱን ቁጥሬን በመግለፅ) ብትልክልኝ ወሮታውን እከፍላለሁ፤ በማለት፡፡
ከዛም ትንሽ ከረምረም ብዬ በአዲሱ ሳጥኔ ከቀድሞው ሳጥኔ መልክቶች እንደተላኩልኝ ለማዬት ወደ ፖስታ ቤት ጎራ ብልም አዲሷ ሳጥኔ ኦና ሆና አገኘኋት፡፡ ግን እንደው ያድርገውና/አያድርገውና/ አዲሱ የቀድሞ ሳጥኔ ባለቤት በቀድሞው ሳጥኔ የተላኩትን ፖስታዎች ወደ አዲሱ ቁጥሬ ልኮልኝ ቢሆን ኖሮ ምን አይነት ወሮታ ነበር የምከፍለው? የማውቀው ነገር ቢኖር እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ወሮታ ምን እንደሆነ በአግባቡ አለማውቄን ነው፡፡ እንደኔ ደብዳቤ ይዘት ከሆነ ልክ ደብዳቤ ተፅፎ ሲያልቅ ከሰላምታ ጋር ከማለት ባልተናነሰ ሁኔታ ነው ወሮታውን እከፍላለሁን የተጠቀምኩበት፡፡ ለማንኛውም፣ ትርጉሙ ሲገባኝ የምከፍለው ወሮታ ስላለበኝ ፅሁፌን በዚህ ላብቃ፤ ከሰላምታ ጋር!   
       
     

No comments:

Post a Comment